በኢትዮጵያ የገጠር እናቶች የቤተሰባቸውን የዕለት ጉርስ ለማብሰል፤ ምሽቱን ለማድመቅ የማገዶና የእንስሳት ቅሬት አካልን ይጠቀማሉ፡፡ ማገዶንና የእንስሳት ቅሬት አካላትን ለምግብ ማብሰያነትና የተለያዩ የቤት ውስጥ ሥራዎች ለመሥራት በባህላዊ ምድጃ መጠቀማቸውም ለበሽታ ተላልፈው እንዲሰጡ፤ ጊዜና ጉልበታቸው አላግባብ እንዲባክን እያደረገ ነው፡፡ ህፃናት በጭስ ምክንያት ለጤና ችግር እንዲወድቁ፤ ሴቶችና ልጃገረዶች ማገዶ ለቀማ ሲወጡ ለፆታዊ ጥቃት እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል፡፡
መንግሥት የገጠሩ ማህበረሰብ ለጤናና ለኢኮኖሚ ጉዳት፤ ልጃገረዶችን ለፆታዊ ጥቃት የሚያጋልጠውን፤ ሀገርንም ለከፍተኛ ሃይል ብክነት የሚዳርገውን ባህላዊ ምድጃን በተሻሻለ ንጹህ የማብሰያ ኢነርጂ ቴክኖሎጂ በመተካት በጤና፤ በኢኮኖሚ ትልቅ ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡
የገጠር ማህበረሰብ ጤንነት ለመጠበቅና የሃይል ብክነትን ለመቆጣጠር ሃይል ቆጣቢና ንፁህ የማብሰያ ኢነርጂ ቴክኖሎጂን ተደራሽ የማድረግ ሥራ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ በተሠራውም ሥራ 20 ነጥብ አምስት ሚሊዮን የተሻሻሉ የማብሰያ ቴክኖሎጂዎች ተሠራጭተዋል፡፡
የማህበረሰቡን ፍትሐዊ የኢነርጂ ተጠቃሜነት ለማረጋገጥ ኤሌክትሪክ፤ የሶላር፤ የባዮማስ ሃይልን የማልማት፤ የተሻሻሉ ንፁህ ምድጃዎችን ተደራሽ የማድረግ፤ የግንዛቤ ማስጨበጫ የመስጠት ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ እየተሠራ ያለውም ሥራ በነጋ በጠባ የቤተሰባቸውን የዕለት ጉርስ ለማብሰል ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውን አለፍ ሲልም ጤናቸውን የሚነሳቸውን ባህላዊ ምድጃ በዘመናዊ ምድጃ የመተካት፤ ጤናማ ሕይወት እንዲመሩ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ ነው፡፡
የገጠር እናቶች ጤናማ ሕይወት እንዲኖሩ ንፁህ የማብሰያ ኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ የማድረግ፤ አነስተኛ ወንዞችን ለሃይል ምንጭነት የመገንባት ሥራ እየተሠራ ነው፤ እንደ እ.ኤ.አ እስከ 2030 አንድ መቶ 50 ወንዞችን ገንብቶ ለአገልግሎት ለማዋል፤ 30 ነጥብ አምስት ሚሊዮን የተሻሻሉ ንፁህ የማብሰያ ኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን ለማሰራጨት ሰፊ ክንውን እየተደረገ ነው፡፡
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር ሥራ አስፈፃሚ ብርሃኑ ወልዱ ለኢፕድ በሰጡት አስተያየት፤ የገጠሩን ማህበረሰብ የንፁህ የማብሰያ ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ያለው ሥራ፤ እናቶች በጭስ ምክንያት የሚደርስባቸውን የጤና ችግር በመቅረፍ ጤናማ ሕይወት እንዲኖሩ እያስቻለ ነው፡፡
ማህበረሰቡ እየተጠቀመባቸው ያሉ የማብሰያ ኢነርጂ ቴክኖሎጂዎች ከፍተኛ ሃይልን የሚያባክኑ ናቸው፤ የሃይል ብክነትን ለመከላከል የተሻሻሉ ዘመናዊ ምድጃዎችን ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው፤ የተሠራውም ሥራ የማህበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ማገዶንና የእንስሳት ቅሬትን በባህላዊ ምድጃ መጠቀም የጤና ችግር ያደርሳል፤ ለማገዶ ፍጆታ የሚውል እንጨት ለመልቀም ጫካ የሚሄዱ ልጃገዶችንም ለፆታዊ ጥቃት ያጋልጣል፤ ህፃናትን ለበሽታ ይዳርጋል፤ማህበረሰቡን ከተለያዩ ችግሮች ተጋላጭነት ለመታደግ የተሻሻሉ ንፁህ ማብሰያ ኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
እየተሠራ ባለውም ሥራ 20 ነጥብ አምስት ሚሊዮን የተሻሻሉ የንፁህ የማብሰያ ኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን የማሰራጨት ሥራ ተሠርቷል፤ እንደ እ.ኤ.አ እስከ 2030 31 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዘመናዊ ምድጃዎችን ለማሠራጨት፤ አንድ መቶ 50 አነስተኛ ወንዞችን ለሃይል ማመንጫነት ለመገንባት ታቅዶ እየተሠራ ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
የተሻሻሉ የንፁህ ምግብ ማብሰያ ኢነርጂ ቴክኖሎጂን ለገጠሩ ማህበረሰብ ተደራሽ ማድረግ የእናቶችን ጤንነት ከመጠበቅ ባለፈ በቤት ውስጥ ሥራ 70 በመቶ የሚባክነውን ኢነርጂ ለማስቀረት ያስችላል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
የገጠሩን ማህበረሰብ የኢነርጂ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ እንዲቻል የሶላር ስርጭትን ያለበትን ከባቢ ዲጂታል መተግበሪያ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፤ መተግበሪያው ተግባራዊ መደረጉ የሶላር ኢነርጂ ስርጭትን ለማሳደግ ይጠቅማል ይላሉ፡፡
የተሻሻሉ ንፁህ የማብሰያ ኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን ባለመጠቀም ብዙ ሃይል በቤት ውስጥ ይባክናል፤ የሚባክነው ኢነርጂ ለብዙ ፋብሪካዎች ማስተናገድ የሚችል ነው፤ የሃይል ብክነትን ለመከላከል ሃይል ቆጣቢ ምድጃዎችን የማበልፀግ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የገጠሩ ማህበረሰብ የኢነርጂ እኩል ተጠቃሚነት ለማስፈን እየተሠራ ባለ ሥራ በ2016 ዓ.ም 14 የሶላር ሚኒግሪዶች ተገንብተዋል፤ በ2017 በጀት ዓመትም ሁለት ሚሊዮን የተሻሻሉ ንጹህ ምድጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡
የተበታተኑና ከሃይል ማመንጫ መስመሮች ርቀው የሚኖሩ የገጠር ማህበረሰቦችን የኢነርጂ ተጠቃሜነታቸውን ለማሳደግ አነስተኛ ወንዞችን የመገንባት ሥራ እየተሠራ ነው፤ በ2016 ዓ.ም ሶስት አነስተኛ ወንዞችን ለሃይል ማመጫነት የመገንባት ሥራ ተጀምሯል፤ ከተጀመሩት ሶስት የአነስተኛ ወንዞች የሃይል ማመንጫ ግንባታ ውስጥ አንዱ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን ዝግጅት እየተደረገ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ጥላሁን ሽመልስ በበኩላቸው፤ የተሻሻሉ ንፁህ የማብሰያ ኢነርጂ ቴክኖሎጂዎች ለገጠሩ ማህበረሰብ ተደራሽ በማድረግ በኩል እየተሠራ ያለው ሥራ ዜጎችን በጤናና በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እያደረገ ነው፡፡
የገጠሩ ማህበረሰብ የንፁህ ማብሰያ ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ማድረግ የእናቶችና የህፃናትን ጤንነት ለመጠበቅ፤ ሴቶችን ከፆታዊ ጥቃት ለማዳን፤ የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ትልቅ አበርክቶ አለው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ማህበረሰቡ የንፁህ ማብሰያ ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆኑ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ያስችላል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
ለገጠሩ ማህበረሰብ ምን አይነት ቴክኖሎጂ እንደሚያስፈልገው ስትራቴጂ በመንደፍ አስፈላጊውን ቴክኖሎጂ የማልማትና የማሠራጨት ሥራ እየተሠራ ነው፤ እየተሠራ ያለውም ሥራ የሃይል ብክነትን ይከላከላል፤ እናቶች ጤናማ ሕይወት እንዲኖሩ ያስችላል፤ ልጅ ገርዶችን ከፆታዊ ጥቃት ለመጠበቅ ያግዛል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
እየተሰራጨ ያለው የንፁህ ማብሰያ ቴክኖሎጂ ከማህበረሰቡ ፍላጎት አንፃር ሲታይ በቂ አይደለም፤ በቂ ለማድረግ በሙያው የሠለጠነ የሰው ሃይል በብዛት ማሠማራትና ትልቅ የገንዘብ አቅም ይጠይቃል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በገጠር የሚኖረው 90 በመቶ ማህበረሰብ የባዮማስ ኢነርጂ ተጠቃሚ ነው፤ የባዮማስ ሃይልን ለመቆጠብ ማህበረሰቡ የተሻሻሉ ንፁህ የማብሰያ ምድጃዎችን እንዲጠቀም እየተደረገ ነው፤ ይህም በጤናው ላይ የሚደርሰውን ችግር እየቀረፈለት ነው ሲሉ በማከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ የአማራጭ ኢነርጂ ልማትና ሽግግር ዳይሬክተር ተከተል ማቲዮስ ይገልጻሉ፡፡
የተሻሻሉ ንፁህ የማብሰያ ምድጃ ቴክኖሎጂዎችን ለገጠሩ ማህበረሰብ ተደራሽ ማድረግ ደንን ከምንጣሮ፤ እናቶችና ህፃናትን ከጤና ሁከት ለመታደግ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፤ እስካሁን የተሠራውም ሥራ ትልቅ ውጤት አሳይቷል ብለዋል፡፡
የገጠሩ ማህበረሰብ በማገዶ ጭስ ለተለያዩ የጤና ችግሮች ይጋለጣል፤ ማህበረሰቡን የማገዶ ጭስ በጤናው ላይ የሚያደርሰውን ችግር በመከላከል ጤናማ ሕይወት እንዲመራ ለማድረግ ሃይል ቆጣቢና የተሻሻሉ ንፁህ የማብሰያ የኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ተበታትኖ የሚኖረውን ማህበረሰብ ፍትሕዊ የኢነርጂ ተጠቃሚ ለማድረግ በፌዴራልም ሆነ በክልል በጀት ተይዞ አነስተኛ ወንዞችን ለሃይል ማመንጫነት የመገንባት ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም