አዲስ አበባ የዓለም ሦስተኛ የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን በተጨባጭ የሚያረጋግጡ ዐሻራዎች

አዲስ አበባ መጠሪያ ስያሜዋን ያገኘችው እቴጌ ጣይቱ ኅዳር ፲፬ ቀን ፲፰፻፸፱ (1879) ዓ/ም ፍልውሃ፤ ፊል-ፊል ወደሚልበት መስክ ወርደው ሳሉ ከዚህ ቀደም አይተዋት የማያውቋት አንዲት ልዩ አበባ አይተው ስለማረከቻቸው ቦታውን ‹‹አዲስ አበባ!›› ሲሉ ጠርተውታል በሚል የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

ከእንጦጦ ተራራዎች ግርጌ የተቆረቆረችው አዲስ አበባ፤ ከባሕር ጠለል በላይ በ2500 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኝም ነች። ከአሜሪካዋ ኒዮርክና ከኒዘር ላንዷ ጄኔቫ ከተማ በመቀጠል ልዩ ልዩ ዓለም አቀፋዊ ውሳኔዎች የሚተላለፉባት ፤ የዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል ሆናም እያገለገለች ትገኛለች። የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ከመሆኗም ባሻገር የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ ፤ የባለ ብዙ የትብብር መድረክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ የዓለም የዲፕሎማቲክ ልዑካን መሰብሰቢያና መኖሪያም ጭምር ነች።

የከተማ አስተዳደር ማዕረግ እንዲኖራት ሆና አስቀድማ የተዋቀረች ቢሆንም ከአንድ ምዕተ-ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ በአዝጋሚ የለውጥ ሂደት ውስጥ መሰንበቷ በበርካቶች ይነገራል። ከምስረታዋ ጊዜ አንስቶ ከተማዋ፤ በአዝጋሚ የለውጥ ሂደት አልፋ አሁን ወደምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታ ላይ መድረሷ አጀንዳ ሆኖ የማያከራክረን ቢሆንም በወርሀ መጋቢት 2010 ዓ.ም በሀገሪቱ የተደረገውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ ወሳኝ የገፅታ ግንባታና ፈጣን የስማርት ሲቲ የሪፎርም ተግባራትን በጊዜ የለንም መንፈስ እያከናወነች ትገኛለች፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በርዕሰ መዲናዋ አዲስ አበባ፤ በመንግሥታት የለውጥ ሂደት ለዘመናት የልማት ሥራዎችን በሚፈለገው ፍጥነትና ጊዜ ጀምሮ መጨረስ፤ አዳዲስ የልማት ሥራዎችን ደረጃ በደረጃ መጀመርን ጨምሮ ቅንጅታዊ የፕሮጀክት አመራር ውስንነት በጉልህ የሚስተዋል ከመሆንም አልፎ በየአካባቢው የብሶትና የሕዝባዊ ቁጣም ምንጭ የነበረ መሆኑ አያጠያይቅም።

በተለያዩ ጊዜያት ብክነትና ምዝበራን ጨምሮ፤ ሌሎችም በተጓዳኝ የተስተዋሉ ችግሮች ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎችና ምሁራን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ተደጋጋሚ ወቀሳ የሰነዘሩባቸው ጉዳዮች መሆናቸውም የሚዘነጋ አይደለም። ለዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ፤ ሌሎችም ወሳኝ ሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች የገጠማቸው የፕሮጀክት አመራር ችግርና ምዝበራ በዋቢነት የሚጠቀስ ነው፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በከተማዋ ምዝበራና ብልሹ አሰራርን ጨምሮ ሌሎችም በፕሮጀክት አመራር ወቅት በጉልህ ሲስተዋሉ ከነበሩ ችግሮች ትምህርት በመውሰድና ማስተካከያ በማድረግም ጭምር በፕሮጀክቶች አመራር ላይ ጀምሮ መጨረስን ማዕከል ያደረጉ አበረታች መሻሻሎች በመታየት ላይ ናቸው፡፡

ከተደረገው የመንግሥት ለውጥ ወዲህ፤ ከተማ አስተዳደሩ የነዋሪውን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ጨምሮ በምርጫ ወቅት ለሕዝቡ የገባቸውን ቃል ደረጃ በደረጃ በተግባር ለመፈጸም እንዲያስችለው ዘርፈ ብዙ የከተማ ልማት ዕቅዶችን ፤ ጊዜ በወሰዱ ጥናቶች ለይቶ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል። በሁሉም ረገድ ከተማዋ ወደ ፈጣን የለውጥ ሂደት እንድትገባ ለማስቻል እየተወሰዱ ያሉ የሪፎርም ርምጃዎችን ተከተሎ ከ60ና 90 ቀናት ባጠረ ጊዜ በርካታ ወሳኝ የልማት ሥራዎች ባልተለመደ መልኩ በከተማዋ በተጨባጭ መ ታየት ጀምረዋል።

በአንድ የምርጫ ዘመን እንኳን፤ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ ተፈጽመው የማያውቁ የልማት ሥራዎች ከለውጡ በኋላ ከ60ና 90 ቀናት ባጠረ ጊዜ ተፈጽመው፤ ለታለመላቸው ሕዝባዊ አገልግሎት በየበጀት ዓመቱ ክፍት በመደረግ ላይ መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ2016 ዓ.ም አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን ለከተማው ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት አሃዛዊ መረጃዎችን በማነጻጸር አስረድተዋል፡፡

የከተማዋን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ገጽታና ደረጃ በሚፈለገው ልክ ማሻሻል እንዲቻል በሁሉም ረገድ እየተከናወኑ ያሉ የስማርት ሲቲ የከተማ ልማት የሪፎርም ተግባራት ፤ በጥብቅ የፕሮጀክት አመረር ዲስፕሊን ከ60ና 90 ቀናት ባጠረ ጊዜ ተጠናቀው ለታለመላቸው ሕዝባዊ አገልግሎት ክፍት በመደረግ ላይ መሆናቸው በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ በስፋት የሚታወቅ ነው፡፡

ከወትሮ በተለየ በከተማዋ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ የስማርት ሲቲ የከተማ ልማት ተግባራት፤ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ጨምሮ የሌሎች ሀገራትን የከተማ ልማት ልምድና ተሞክሮ ከከተማዋ አሁናዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር በማጣጣም የሚተገበሩ ከመሆናቸውም ባሻገር በሰው ተኮር የልማት መርህ የነዋሪዎችን ደህንነት በጠበቀ መልኩ የሚከናወኑም ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ በሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በኩል ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።

ለዚህም ከንቲባ አዳነች አቤቤ “ልማትን የምንሰራው ለሰው ነው ተግባራዊ የምናደርገውም ሰውነትን በሚያስቀድም መርህ ነው” በሚል የሚያደርጓቸውን ንግግሮች በዋቢነት መውሰድ ይቻላል። የሪፎርም ሥራው የከተማዋን የዲፕሎማሲ፤ የቱሪዝም፤ የኮንፍረስ፤ የኢንቨስትመንት፤ የጤና፤ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማዕከልነት በተጨባጭ ማረጋገጥን ቀዳሚ ኢላማ ያደረገ መሆኑም በተለያዩ ጊዜያት እየተነገረ ያለ ነው።

24/7 ባለፉት ጊዚያት ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች፤ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች ፤ ዓለም አቀፍ የኮንፈረንስ ማዕከላት፤ ማሻሻያ የተደረገባቸውን ጨምሮ እንደ አዲስ ተገንብተው ለሕዝባዊ አገልግሎት ክፍት በመደረግ ላይ ያሉ የጤና መሠረተ-ልማቶች ፤ የኢንቨስትመንት እና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እንዲሁም ሌሎችም መሰል ተግባራት በአጠቃላይ በከተማዋ የስማርት ሲት የከተማ ልማት ፕሮግራም ማዕቀፍ ተግባራዊ የሚደረጉ መሆናቸውን አስቀድሞ ከተማ አስተዳደሩ ይፋ ተደርጓል። አተገባበሩም ይህንኑ የተከተለ መሆኑ ለከተማዋ ነዋሪዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ሁሉ የሚታይ ነው።

የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በከተማዋ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ የከተማ ልማት ዕቅዶች አሁናዊ አፈጻጸም፤ ጀምሮ በጥብቅ ዲስፕሊን ተቀናጅቶ የመጨረስን አዲሰ የፕሮጀክት አመራር ልምድ በሀገር አቀፍ ደረጃ እያስተዋወቀ ያለ መሆኑ ተደጋግሞ በየደረጃው ባሉ የሥራ ኃላፊዎች ይነገራል። በሁሉም ረገድ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች በይበልጥ በጊዜ የለንም መንፈስ ተጠናክረው የሚቀጥሉ ስለመሆናቸው ከንቲባ አዳነች በተለያዩ ጊዜያት በተደጋጋሚ አጽንኦት ሰጥተው ሲናገሩም ተደምጠዋል።

ለዚህም ተጨባጭ ማሳያ የሚሆነው በአንድ የምርጫ ዘመን እንኳን በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ ተፈጽመው የማያውቁ የልማት ሥራዎች ከስልሳና ዘጠና ቀናት ባጠረ ጊዜ፤ ተጠናቀው ለታለመላቸው ሕዝባዊ አገልግሎት ክፍት መደረግ የመቻላቸው ጉዳይ ነው። ለአብነት ያክል በከተማ አስተዳደሩ በተከታታይ ዓመታት ተገንብተው ለአገልግሎት ብቁ የተደረጉ ወደ 30 ሺ ገደማ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች ፤ የነዋሪውን የኑሮ ጫና በዘላቂነት የሚያቃልሉ ናቸው ተብለው በአዋጪነት ጥናት ተለይተው ተግባራዊ የተደረጉ ስለመሆናቸው ብዙ ተብሏል፡፡

 

እነዚህ የልማት ሥራዎች የከተማዋን ጎስቋላ ገፅታ በሚፈለገው አግባብ እየለወጡ ያሉ፤ ከወትሮ በተሻለ ሰፋፊ የሥራ ዕድሎችን የፈጠሩ፤ ወሳኝ የመንግሥት አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ ያሳለጡ ከመሆናቸውም ባሻገር የከተማዋን ገቢ ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገሩ ስለመሆናቸውም ከንቲባ አዳነች ካለፉት ጊዜያት ጋር በማነጻጸርም ጭምር በከተማው ምክር ቤትና በተለያዩ መድረኮች ላይ ተናግረዋል።

በከተማዋ አዲስና እየዳበረ ያለውን አሁናዊ የፕሮጀክቶች የሥራ አፈጻጸምን በማስመልከት፤ ከንቲባዋ ለከተማው ምክር ቤት በተደጋጋሚ የሰጧቸውን ማብራሪያዎች በመንተራስ ያስገኟቸውን ውጤቶች በቀናነት በመመልከት ብቻ ከተማዋ፤ በሁሉን አቀፍ የለውጥ ሂደት ላይ መሆኗን በልኩ መረዳትና ማድነቅ እንዲሁም መደገፍ ለሚፈልግ አካል ሁሉ የሚቻል እንጂ አሻሚ የሚሆን አይሆንም። ይህንኑ ጀምሮ የመጨረስ አዲስና እየዳበረ የመጣውን የፕሮጀክት አመራር ልምድ ተከትሎ፤ ከንቲባ አዳነች የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራምን ጨምሮ በየዘርፉ ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራት ልዩ ልዩ የማበረታቻ ሽልማቶችን መቀበላቸውም ይታወቃል።

ከለውጡ ማግስት አንስቶ በተከታታይ በፕሮጀክቶች አመራርና አስተዳደር ረገድ በተጨባጭ የታየው ስኬትና ውጤት ሊመዘገብ የቻለው መንግሥት የመፈፀም አቅሙን በማሳደጉ፤ ብክነትን መቀነስ መቻሉን ጨምሮ የልማት አጋሮችን እና የነዋሪውን ሁለንተናዊ አቅም አስተባብሮ መጠቀም በመቻሉ የተገኘ ስለመሆኑ ከንቲባዋ ለከተማው ምክር ቤት የ2016 የሥራ አፈጻጸምን በማስመልከት በሰጡት ማብራሪያ ወቅት ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ ከተማን ዓለም አቀፍ ተቀባይነትና የነዋሪዎቿን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በሚፈለገው ልክና አግባብ እንደሚያሻሽል ታምኖበት በከተማዋ ተጀምሮ የነበረው የኮሪደር ልማት ሥራ፤ ሁለተኛውን ምዕራፍ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር በቅርቡ በይፋ አስጀምረዋል። በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት የማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራና በቅንጅት ለተገኘው ስኬት ለከተማዋ አመራሮች የማበረታቻ ዕውቅናና ሽልማት መስጠታቸውም እንዲሁ የሚታወስ ነው።

24/7 አስቀድመው በጥናት በተለዩ አምስት የኮሪደር ልማት መዳረሻዎች በጥብቅ የአመራር ዲስፕሊን ሲከናወን የነበረው፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳና ጥራት ተጠናቆ ለሕዝባዊ አገልግሎት ክፍት መደረጉ በየመዳረሻቸው ምርቃት ወቅት ይፋ ተደርጓልም።

በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር ሃሳብ አመንጪነት ፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ የከተማዋ የኮሪደር ልማት ሥራ በአዋጪነት ጥናት ተረጋግጦ አንድ ተብሎ መጀመሩ የተነገረው። በተገባደደው የ2016 በጀት ዓመት በከተማዋ ተግባራዊ የተደረገው የኮሪደር ልማት ሥራ ከመጀመሩ አስቀድሞ ፤ በከተማ ልማት ባለሙያዎች በኩል አስቀድሞ የተደረገው የአዋጪነት ጥናት አካታች ልማት ፣ በሁሉም ረገድ የሚገለጽ ዘላቂ ዕድገትና የነዋሪውን አዳጊ ፍላጎቶች ማዕከል ባደረገ አኳኋን የልማት ዕቅዶቹን ደረጃ በደረጃ መተግበር እንደሚገባም ነው በሪፖርታቸው ላይ በአጽንኦት የተጠቆመው። አተገባበሩም ይህንኑ የተከተለ እንዲሆን ከንቲባዋን ጨምሮ በየደረጃው በሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች ምሽቱን የሚያደርጓቸውን ጉብኝትና ክትትሎች በከተማዋ ማየት የተለመደ ነው።

የከተማዋ የኮሪደር ልማት ትግበራ፤ የጎረቤት ሩዋንዳ ኪጋሊ ከተማን ጨምሮ የሌሎችንም ዓለም አቀፍ ከተሞች ተሞክሮዎችን ዋቢ አድርጎ እንዲፈጸም ከመሆኑም ባሻገር፤ ከከተማዋ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም በከተማ ልማት ባለሙያዎች ጥናት ወቅት ተጠቁሟል። ከተማ አስተዳደሩ የኮሪደር ልማት በሚያልፍባቸው መዳረሻዎች በባለሙያዎቹ ምክረ-ሃሳብ መሠረት ካሳ ተለዋጭ ቦታና በየደረጃው የሚገኙ ቤቶችን አስቀድሞ እያቀረበ ያለ ስለመሆኑ የልማቱ ተነሽዎች በተለያዩ ጊዜያት ለሚዲያ አካላት ከሰጧቸው ምስክርነቶች መረዳት የሚቻል ይሆናል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ አጠቃላይ ግንባታቸው ተጠናቆ ለሕዝባዊ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ክፍት ተደርገው ከነበሩት አምስቱም የኮሪደር ልማት መዳረሻዎች መካከል ከአራት ኪሎ በመስቀል አደባባይ አድርጎ እስከ ቦሌ ድልድይ (7 ኪ.ሜትር)፤- ከቦሌ አየር መንገድ እስከ መገናኛ ዲያስፖራ አደባባይ (4.9 ኪ.ሜትር)፤- ከመገናኛ ዲያስፖራ አደባባይ በአራት ኪሎ አድርጎ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ድረስ (6.4 ኪ.ሜትር)፤ ከፒያሳ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ዙሪያ፣ በለገሃር ሜክሲኮ፣ በሳርቤት አድርጎ እስከ ወሎ ሰፈር (10 ኪ.ሜትር) ባለው የተከናወነው የልማት ሥራ በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው፡፡

በአምስቱም የኮሪደር ልማት መዳረሻዎች፤ ከ240 ኪ.ሜ በላይ መንገድ እና በተጓዳኝ በፕሮግራም ማዕቀፉ ተካተው የተከናወኑ መሰል መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ 70 የከተማዋን የውስጥ ውበት ከመልካም የአየር ንብረት ጠባይ ጋር አዳምረው መንፈስን የማደስ አቅም ያላቸው የሕዝብ መናፈሻዎች ተገንብተው የከተማዋ ነዋሪ ከቤተሰቡ ጋር ባመቸው ሰዓት ሁሉ እየተገለገለባቸው መሆኑ ይታያል፡፡

ከተማዋን በሁሉም ረገድ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ለማስቻል የተያዘውን ራዕይ ከማሳካት አኳያ፤ የከተማዋን ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚረዱ የፍሳሽ ማስተላለፊያዎች፣ በዓይነታቸው ልዩ የከተማዋን ሰላማዊነት የሚያፀኑ የደህንነት ካሜራዎች፣ የብልህ ትራንስፖርት ሥርዓት (intelligent transport system) በመሬት ውስጥ የመዘርጋት ሥራ ፣ ከ400 የሚልቁ ህንጻዎች ዕድሳትን ጨምሮ ወጥ የቀለምና የመብራት ሥራዎች እና ሌሎች ተያያዥ ተግባራት ዘመን ተሻጋሪ አገልግሎት እንዲሰጡ ሆነው በላቀ ጥራት እየተሰሩ ስለመሆናቸው ከተማ አስተዳደሩ የሚያወጣቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከከተማ አስተዳደሩ እንደተገኘው መረጃ በመጀመሪያው ምዕራፍ፤ ለኮሪደር ልማት ፕሮግራም ተነሺዎች 6.2 ቢሊየን ብር ካሳ ለመክፈል የተቻለም ሲሆን ፤ ለልማቱ ተነሺዎች በተቀላጠፈ አኳኋን ለ2,538 ቦታዎች (33.4ሄ/ር) ምትክ መሬት በከተማው የመሬት ልማት ማኔጅመት ቢሮ በኩል ማስተላለፍ ተችሏም ተብሏል። በሌላ መልኩ የልማት ሥራው ለከተማዋ ነዋሪዎች ይዞት በመጣው መልካም ዕድል ሳቢያ፤ እጅግ ጎስቁለው ለመኖር አመቺ ያልሆኑ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ በንግድ ቤቶች ውስጥ የነበሩ በርካታ የልማት ተነሺዎች ምቹ የመኖሪያ እና መሥሪያ ቦታ እንዲያገኙም አስቀድሞ ተደርጓል፡፡

በአገልግሎትና በአቅርቦት ሥራ ላይ የተሰማሩ ብዙሃን የንግዱ ማህበረሰብ አካላት፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በልማቱ ሳቢያ የተፈጠረው ሰፊ የገበያ ትስስር አካል በመደረጋቸው ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ተጠቃሚነትን በከተማዋ እንዲረጋገጥ እያስቻለ የሚገኝ የልማት ሥራም መሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ ሳያሻው በፍሬው የሚታይ ነው።

ከሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት መጀመር አስቀድሞ፤ በቅርቡ ተመርቆ ለሕዝባዊ አገልግሎት ክፍት የተደረገው የአፍሪካ፣ የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ መግቢያ በር ተደርጎ የሚታየው የቦሌ መንገዶች የልማት ኮሪደር ፕሮግራም ርዕሰ መዲናዋ አዲስ አበባ የንግድ፣ የቱሪዝም፣ የዓለም አቀፍ ኮንፈረንስና የልዩ ልዩ የስማርት ሲቲ አገልግሎቶች ማዕከል በተጨባጭ እየሆነች መምጣቷን ያረጋገጠም ሥራ መሆኑ በበርካቶች በምርቃቱ ወቅት የተነገረ ጉዳይ ነው። የቦሌ መንገዶች ፣ የልማት ኮሪደር ሥራ ወደ ቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ እና ወደ ሌሎችም የከተማዋ አካባቢዎች በትራንስፖርት የሚደረግን ጉዞ በእጅጉ የተቀላጠፈ እንዲሆን አስችሏል፡፡

በቦሌ መንገዶች የኮሪደር ልማት ፕሮግራም ማዕቀፍ የተገነቡ፤ ልዩ ልዩ የቢዝነስ ማዕከላት፣ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች እና ሱቆች የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ቀልብ በእጅጉ መሳብ ችለዋል። በዚህም በአካባቢው የሚከናወኑ ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የምሽቱን ክፍለ ጊዜ ጨምሮ፤ ከፍተኛ የኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲታይባቸው ከመሆኑም ባሻገር ፤ መጪው ጊዜ ለከተማዋ ብሩህ መሆኑን አመላካች ተደርጎ ተወስዷል፡፡

ከቦሌ ድልድይ እስከ መስቀል አደባባይ ድረስ ባለው በቦሌ መንገዶች የልማት ኮሪደር ፕሮግራም የሚከተሉትን ዐበይት ክንውኖች የያዘ ነው። 4.3 ኪሎ ሜትር የመንገድ ልማት፤ 10 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ ግንባታ፤ 13.2 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መንገድ ግንባታ ፤ 30,160 ካሬ ሜትር የግራናይት እና የአስፓልት ንጥፍ ሥራ፤ 30 የአውቶቡስ እና ታክሲ መቆሚያ አገልግሎት ፤ 10 የስማርት ፓርኪንግ አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች ፤ ከ10 የሚልቁ አነስተኛ የሕዝብ መዝናኛ ፓርኮች እና ማረፊያ ፕላዛዎችን ጨምሮ ከ500 በላይ በመንገድ ዳር የሚገኙ ሕንፃዎች እና ቤቶችን እድሳት አካቶ በልዩ ጥራት የተፈጸመ ስለመሆኑ በምረቃቱ ወቅት በአጽንኦት ማብራሪያ ተሰጥቶበታልም፡፡

በምርጫ ወቅት፣ ለከተማው ነዋሪ በመንግሥት ደረጃ ቃል የተገቡ የልማት ሥራዎችን ሁሉ ደረጃ በደረጃ እንደሚያስፈጽሙ ፤ በቦሌ የኮሪደር ልማት መዳረሻ የምርቃት መርሀ-ግብር ላይ የተናገሩት ከንቲባ አዳነች ፤ በሁሉም ረገድ ርዕሰ መዲናዋ አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ማሟላት እንድትችል ታስበው የሚከናወኑ የመሠረተ-ልማት ዝርጋታዎች በመጪውም ጊዜ በይበልጥ ተጠናክረው የሚቀጥሉ ስለመሆናቸው አንስተው ልክ እንደ ቀድሞው ሁሉ የብዙሃንን ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

“አርቆ ማሰብ ፤ ለየት አድርጎ ማቀድ እንዲሁም በመፍጠንና በመፍጠር መርህ ርዕሰ መዲናዋን አዲስ አበባንም ሆነ ኢትዮጵያን በሚገባና በሚፈለገው ልክ በሁሉም ረገድ ለመቀየር እንዲቻል እንደ አንድ ሰው ሆኖ በቅንጅት ተግቶ መሥራት እንደሚገባ፤ በኮሪደር ልማት መዳረሻዎች የምርቃት መርሀ-ግብር ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር)በተደጋጋሚ በአጽኖት ሲናገሩ መደመጣቸው የሚታወስ ከመሆኑም ባሻገር፤ ሀገራቸውን በሚወዱ ዜጎች ሁሉ ዘንድ ቅቡልነት የሚኖረውም ነው፡፡

በኮሪደር ልማት መርሀ-ግብር በከተማዋ ተግባራዊ ከሚደረጉ ዝርዝር የልማት ሥራዎች መካከል የመንገድ ኮሪደር ልማት፤ የወንዝ ዳርቻዎች አዋሳኝ የተፋሰስ ልማት ፣ የብስክሌትና ሞተር አልባ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ልማት ፣ ዘመናዊ የትራንስፖርት ተርሚናሎች ግንባታ፣ አገናኝ የኮሪደር ልማት ድልድዮች፣ ማሳለጫዎችና የመጋቢ መንገዶች ልማት፤ የመንገድ ዳር የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ፤ ፋውንቴይኖች እና የሕዝብ መናፈሻ ስፍራዎች፤ ወጥ የህንጻ ቀለምና የከተማ ማብራት፤ ደረጃቸውን የጠበቁ ፓርኪንጎች፣ የመኪና መጫኛና ማውረጃ አገልግሎቶችን ጨምሮ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን አካቶ ተግባራዊ እየተደረገ ያለ ከመሆኑም ባሻገር በተጨባጭ የታየም ነው።

“ ከተሞች ለወደፊቱ ለዜጎቻችን ክብር የሞላበት የኑሮ ዘይቤን ለማጎናፀፍ የሚመቹ እንዲሆኑ ማዘጋጀት ይኖርብናል። ከተሜነት በሁሉም ረገድ እየተስፋፈ የሚሄድ መሆኑ የሚታወቅ ነው። እኛም ዘላቂ እና ምቹ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የሚያሟሉ ከተሞችን በዘላቂነት ለመፍጠር ሁሉም መሳሪያዎች አሉንም” ሲሉ የተናገራት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) በከተማዋ እንደ ቀድሞው ሁሉ በተመሳሳይ ተግባራዊ የሚደረገውን ሁለተኛውን ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ በኢፌዴሪ ቤተ መንግሥት ባስጀመሩበት ወቅት ነው።

በመርሀ-ግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለከተማዋ አመራሮች እንዳስተላለፉት መልዕክት፤ የተደረገላችሁ ዕውቅና ሽልማት የተሻለ የከተማ ከባቢ ለመፍጠር ያሳያችሁትን ትጋት እና ጠንካራ ሥራ የሚያንፀባርቅና ለላቀ ሥራ እንድትነሳሱ ድርብ ኃላፊነት እንዳለባችሁ ለማሳሰብም ጭምር የተደረገ እንደመሆኑ አስቀድሞ የነበራችሁን ጥንካሬ ማላቅ ከሁላችሁም የሚጠበቅ ነውም ማለታቸው የሚታወቅ ነው። ከመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ ብዙ ትምህርቶችን ቀስመናል። አሁን ተግባራዊ ለምናደርገው ሁለተኛውን ምዕራፍ የኮርደር ልማት ባላሰለሰ የመሻሻል ሂደት እና የሥራ ሥነ ምግባር በቀደመው ያሳካነውን ተቀናጅተን ለማላቅ ተነስተናልም ብለዋል።

በርዕሰ መዲናዋ አስቀድመን የጀመርነውን ይህንን የሀገርን ሁለንተናዊ ገጽታ የማሻሻል መልካም ሥራ ፤ በመላ ሀገራችን ለማስፋፋት የምናደርገውን ጥረት በመደገፍ ተመሳሳይ ሥራ የጀመሩ አስራ አንድ ከንቲባዎች አብረውን ረዳት በመሆን ተቀናጅተው ይሰራሉም ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ። ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፡-በእርሶ ሃሳብ አመንጪነት እና ቀዳሚ መሪነት ከተማችን አዲስ አበባ እንደስሟ ውብ አበባ እንድትሆን ለማድረግ ከለውጡ ማግስት አንስቶ እስከ ኮሪደር ልማቱ ድረስ በርካታ የልማት ስኬቶችን በሁሉም ረገድ አስመዝግበናል።

በተለይም በኮሪደር ልማት ፕሮግራም ከሶስት እስከ አራት ወራት ባለው የተፈጸመው ግን የከተማችንን አጠቃላይ ገፅታ የቀየረ፣ አዲስ የሥራ ባሕልን ያዳበረ እና ለከተማችን ነዋሪዎች ምቹ መኖሪያ ከባቢን የፈጠረ ቅንጅታዊ የከተማ ልማት ሥራ እንደመሆኑ ከውስጥም ከውጪም የበርካቶችን ዕውቅና ያስገኘ ነውም ብለዋል። ይህ ዕውቅናና ሽልማት የከተማው አመራር ብቻ ያስገኘው ሳይሆን መላው የከተማችን ነዋሪዎች በተለይም በኮሪደር ልማት አካባቢ የሚገኙ ዜጎች ትብብርን ጨምሮ፣ ኮንትራክተሮችና ኮንሰልታንቾች እንዲሁም አብረውን በጋራ የመልካም ሃሳባችን ደጋፊ ሆነው ለቆሙ በሙሉ ማስታወሻ ሊሆን የሚገባ ነውም ሲሉ ከንቲባዋ መናገራቸውም ይታወሳል።

የአዲስ አበባ ከተማን ፣ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ተቀባይነትና የነዋሪዎቿን በሁሉም ረገድ የሚገልጽ አዳጊ ፍላጎቶች በሚፈለገው ልክና ፍጥነት ማረጋገጥ እንዲቻል ልክ እንደ ቀድሞው ሁሉ፤ የሁለተኛውን ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ 24/7 በከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተዋረድ በሚተገበር ቅንጅታዊ የሥራ እንቅስቃሴ ተፈጻሚ የሚደረግ መሆኑን በማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከንቲባዋ አዳነች በአንክሮ አረጋግጠዋል፡፡

በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ ሕዝባችን በምርጫ 2013 በፀሐይ እና ዝናብ ውስጥ ሆኖ ፓርቲያችንን በመምረጥ የሰጠንን መንግሥታዊ ኃላፊነት ወደ አመርቂ ውጤት የምንለውጥበት ነው ያሉት የከተማዋ አመራሮች፤ 2017 የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት፤ ለአዲስ አበባ አዲስ የተስፋ ብርሃን ጮራ ይዞ መምጣቱን በመግለጽም ጭምር ሁለተኛውን ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ በላቀ ደረጃና ጥራት ጀምሮ ለመጨረስ የሚያስችል ዝግጅት አስቀድሞ በከተማዋ ሲደረግ የነበረ መሆኑንም አመልክተዋል።

በጋዜጤኛና ሲኒየር የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ላንዱዘር አሥራት

አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You