አሜሪካ ለኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች

አዲስ አበባ፡- የአሜሪካ መንግሥት እና ሕዝብ ለኢትዮጵያውያን እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ ገለጹ።

የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የድጋፍ ፕሮግራም የተመዘገቡ ውጤቶችን በመግለፅና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የፓናል ውይይት በማድረግ የፕሮግራሙን የማጠቃለያ መርሀግብር ከትናንት በስቲያ አካሂዷል።

በማጠቃለያ መርሀግብሩ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ እንደገለፁት፤ የአሜሪካ መንግሥት እና ሕዝብ ለኢትዮጵያውያን እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከግጭት ጋር የተያያዙ ጉዳቶችን፣ የሠብዓዊ ድጋፎችን፣ ሰላማዊ እና ገንቢ ውይይቶችን በማድረግ ግጭቶችን ከማስቆም አኳያ ጉልህ ሚና ተጫውቷል።

የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት በግጭት ምክንያት በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድረጉንና በዚህም በኢትዮጵያ የድጋፍ ፕሮግራም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የጠቀሱት አምባሳደሩ፤ በርካታ ትምህርት ቤቶችንም በመገንባት በግጭቱ ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መመለስ መቻሉን ተናግረዋል።

እንዲሁም ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች በአእምሯዊ ጤና እና በሥነ-ልቦና ድጋፍ መርሃ ግብር አማካኝነት ለመፍታት የሥነ-ልቦና ባለሙያዎች ተሰማርተው እየሠሩ እንደሚገኝ የጠቆሙት አምባሳደር ኢርቪን፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ዜጎች ወደ መደበኛ ሕይወት እየተመለሱ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት በኢትዮጵያ በግብርና፣ በአገልግሎትና በተለያዩ መስኮች እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ድጋፍ ፕሮግራም ሲኒየር ፕሮግራም አማካሪ ሊዲያ ጌታሁን በበኩላቸው፤ ፕሮግራሙ የአምስት ዓመት ቆይታ የነበረው ሲሆን በቆይታውም 174 ከሚደርሱ አጋር አካላት ጋር መሥራት መቻሉን በመግለጽ፤ በአማራ፣ ኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች ላይ ቢሮዎችን በመክፈት ሴቶችንና ወጣቶችን ለማብቃት ከሚሠሩ ሀገር በቀል ድርጅቶች ጋር በጋራ መሥራቱን አንስተዋል።

እንደ ፕሮግራም አማካሪዋ ገለጻ፤ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በተለይም ግጭት በተካሄደባቸው አካባቢዎች እንደ ቤተ-መጽሀፍት፣ የወጣቶች ማዕከልና በሌሎችም ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ሥፍራዎች የማደስ ተግባር ተከናውኗል። ከእነዚህም መካከል የአምቦ፣ ነቀምት፣ መቀሌና ሌሎችም ቤተ-መጽሐፍት ይገኙበታል።

ባለፉት አምስት ዓመታትም 375 ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ በፕሮግራሙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ፕሮግራም አማካሪዋ ጠቁመዋል።

ከግጭት ጋር የተያያዙ ጉዳቶችን በአእምሯዊ ጤና እና በሥነ-ልቦና ድጋፍ መርሃ ግብር አማካኝነት ለመፍታት በተደረገው ጥረት በተገኙ ተሞክሮዎች ዙሪያ የፓናል ውይይት ተደርጓል።

በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች በአስደንጋጭ ገጠመኞች በመሰቃየት ላይ የሚገኙ በርካታ ዜጎች ይገኛሉ። በዚህም በዜጎቹ ላይ የደረሰውን የሥነልቦና ቀውስ ለማከም አመቺ ሁኔታዎች ባይኖሩም ኢትዮጵያውያን ያላቸውን ባህላዊና ሃማኖታዊ መስተጋብሮችን በመጠቀም ችግሮቹን ለመቀነስ ጥረት መደረጉ ተገልጿል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You