“ኢትዮጵያ በጀመረችው ፈጣን እድገት ልክ ለመጓዝ ለሙያና ሙያተኞች ተገቢው እውቅና ይሰጣል”  – ሙፈሪያት ካሚል የሥራና ክሂሎት ሚኒስትር

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ከጀመረችው ፈጣን እድገት እኩል ለመጓዝ ለሙያና ሙያተኞች ተገቢውን ክብርና እውቅና እንደሚሰጥ የሥራና ክሂሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ። በኢትዮጵያ በልምድ ለተገኘ ክሂሎት እውቅና መስጠት ተጀምሯል።

ሚኒስትሯ “በልምድ ለተገኘ ብቃት” የእውቅና አሰጣጥ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ትናንት በተካሄደበት ወቅት፣ በትኛውም መንገድ የተገኘ ክህሎት እውቅና ሲሰጠው በውጤት የታጀበ ትልቅ ማህበረሰብ ለመገንባት ያስችላል ብለዋል።

እንደ ማህበረሰብ የተፈጠረው አቅም ተመልሶ እንደ ሀገር ኢኮኖሚው ያለውን ፍላጐትና አቅርቦት ለማጥበብና በሂደትም ለመፍታት ትልቅ አቅም እንደሆነ ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ከጀመረችው ፈጣን እድገት እኩል ለመጓዝ ለሙያና ሙያተኞች ተገቢውን እውቅና እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

ብዙ ክህሎት ያላቸው ዜጐች ለኢኮኖሚው እድገትና ተወዳዳሪነት ያላቸው ሚና ትልቅ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፣ ለሙያ ክብር መስጠት ሀገራዊ ተወዳዳሪነትን እና ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ አኳያ ፋይዳው የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለኢ መደበኛ ክህሎት እውቅና የመስጠቱ ሥራ እድሜ፣ ጾታ፣ የአካል ጉዳት፣ ሃይማኖትና ሌሎች ጉዳዮችም ድንበር ሳይኖራቸው መላው ኢትዮጵያውያንን ተደራሽ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። በተለይም በኮንስትራክሽን፣ በእደ ጥበብ፣ በኤሌክትሮኒክስና መሰል ዘርፎች በኢ-መደበኛ መንገድ ለተገኙ ክህሎቶች እውቅና መስጠትና ወደ መደበኛ ክህሎት ማሻገር እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

ወደ መደበኛው ኢኮኖሚ የሚመጣው የሰው ሃይል ከእነዚህ ዜጐች የተውጣጡትንም ይጨምራል ሲሉ ተናግረዋል።

በኢ መደበኛ መንገድ ክህሎት ያገኙትን ዜጐች ብቃት ለመገምገም እና እውቅና ለመስጠት የማስተግበሪያ መመሪያ መዘጋጀቱን ተናግረው፣ ይህም ለነባር እውቀታቸው፣ ችሎታቸው እና ልምዳቸው እውቅና እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ነው ያሉት። የማስተግበሪያ መምሪያው ኢትዮጵያ ለጀመረችው ልማት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም ጠቅሰዋል።

ክህሎት ያለው ዜጋ ቁጥር ሲጨምር ምርታማነትም በዛው ልክ እያደገ ስለሚመጣ ይህ አይነቱ አሠራር ሙያተኞችንና የግል ዘርፉን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት ነው ብለዋል።

ዜጐች በራስ የመተማመን ብቃታቸው እያደገ እንዲመጣና የመደራደር አቅማቸውን እንዲያድግ ትልቅ ሚና ያለው እንደሆነም ተናግረዋል

እንደ ሚኒትሯ ገለጻ፣ ኢትዮጵያ የጀመረችው ጉዞ ፈጣን፣ ፋታ የማይሰጥ፣ አካታች ሲሆን፣ ሁሉንም ዜጋ በተሳትፎው ልክ ተጠቃሚ ማድረግ ከሚያስችለው የኢኮኖሚ እድገት ጋር መጓዝ ካልተቻል፣ እንዲሁም ያሉ አቅሞችን በአግባቡ ማምጣት የሚያስችል እድል መፍጠር ካልተቻለ፣ ሀገር ያላትን አቅም በሙሉ አሟጦ ማልማት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እውን ማድረግ ያስቸግራል። ስለዚህም ኢትዮጵያ ከጀመረችው ፈጣን እድገት እኩል ለመጓዝ ለሙያና ሙያተኞች ተገቢው እውቅና የመስጠቱ ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You