“እኛ ኢትዮጵያውያን ከተደመርን እንደ ደመራው ብርቱ እንሆናለን፤ ከፍ ብለን እናበራለን” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡- እኛ ኢትዮጵያውያን ከተደመርን እንደ ደመራው ብርቱ እንሆናለን፤ እንደ ደመራው ከፍ ብለን እናበራለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ2017 ዓመት የመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለመስቀል በዓል በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እንደገለጹት፤ መስቀል ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በሁለት መንገድ የሚያሳይ በዓል ነው፡፡

ደመራው ከእንጨት ወደ ችቦ፤ ከችቦ ወደ ደመራ የሚያድግበት መንገድ መደመር ምን ያህል ኃይልና ጉልበት እንዳለው ያሳያል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ በሌላ በኩል ደግሞ መስቀል በተለያየ መንገድ፣ በተለያየ ባህልና አከባበር በብዙ ብሔረሰቦች መከበሩ በኅብረ ብሔራዊነታችን ውስጥ ያለውን ነባር ትሥሥር፣ የወል ትርክትና አንድነት የሚያሳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ እንዲህ ዓይነት በዓላት ሃይማኖታውያን ብቻ አይደሉም፡፡ የኅብረ ብሔራዊ አንድነት መገለጫዎች ጭምር ናቸው፡፡ በመደመር ውስጥ ያለውን ጥንካሬና ጉልበት የሚያሳዩ እና ትውልድ ለእኛ ትምህርት ያቆማቸው ምልክቶች ናቸው፡፡

ደመራውን በደመርን ጊዜ፤ ደመራውን በለኮስን ጊዜ፤ እንደየባህላችን የመስቀልን በዓል ለማክበር በቤተሰብና በማኅበረሰብ ደረጃ በተሰባሰብን ጊዜ ኢትዮጵያን እናስባትም ብለዋል፡፡

የሁላችንም ዕሴቶች፣ ባህሎች፣ ወጎች፣ አቅሞች፣ ጸጋዎች፣ ሀብቶች፣ ቋንቋዎች እና ታሪኮች ተደምረው ኢትዮጵያን ታላቅ፣ የበለጸገችና የተከበረች ሊያደርጓት እንደሚችሉ እናስብ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ የእነዚህ ሁሉ ድምር መሆኗን እና ከድምሩም በላይ መሆኗንም እናስብ ብለዋል፡፡

ደመራውን እያሳየን ለልጆቻችን ከሃይማኖታዊና ባህላዊ ትርጉሙ በተጨማሪ “እኛ ኢትዮጵያውያን ከተደመርን እንደ ደመራው ብርቱ እንሆናለን፤ እንደደመራው ከፍ ብለን እናበራለን” በሏቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ገለፃ፤ የመስቀል በዓል የሕልም ጉልበት የታየበት በዓል ነው፡፡ ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉን ለማውጣት ባለመችበት ጊዜ መንገዶች ሁሉ ዝግ ነበሩ፡፡ ነገሮች ሁሉ አስቸጋሪ ነበሩ፡፡ ማንም በማያስበው ጊዜ፤ አይቻልም አይሞከርም በሚባልበት ወቅት፤ አንድ ቀን፤ ፈጣሪዋ ሲፈቅድ፤ መስቀሉን ከተቀበረበት ሥፍራ ለማውጣት ሕልም ነበራት፡፡ ከብዙ ውጣ ውረዶች በኋላ መስቀሉን ከተቀበረበት ሥፍራ ለማውጣት በቃች፡፡

በመሆኑም ደመራ ለሚታገል፤ ተስፋ ለማይቆርጥና እስከ መጨረሻው ለሚጸና ሰው ሕልሙ አንድ ቀን እውን እንደሚሆን የሚያሳይ ትእምርት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You