አዲስ አበባ፦ በአዲስ አበባ ከተማ የተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ሳቢና አስደናቂ መሆኑን በበዓሉ ላይ የተገኙ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ተናገሩ።
በመስቀል ደመራ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው ካናዳዊው ፕራንክ ዊችባግ፤ በዓሉ በሰዎች ብዛትና ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሲከበር መመልከቱ አግራሞት እንደፈጠረበት ገልጿል፡፡
እንደ ፕራንክ ገለጻ፤ በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን ተመልክቻለሁ። በዚህም ኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት እያስመዘገበች ነው።
በዓሉ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውንና ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን የሚገልጹበት እንደሆነ መረዳቱን የገለፀው ፕራንክ፤ ስለመስቀል ደመራ በዓል ከጓደኞቹ ሰምቶ እንደመጣና ከጠበቀው በላይ አስደሳች ሆኖ ማግኘቱን ጠቁሟል።
ከቱርክ የመጣችው ግዩልዳን አምቢን በበኩሉዋ፤ በኢትዮጵያ የመስቀል በዓልን፣ የአክሱም ሃውልትን፣ ላሊበላንና ሌሎች አብያተ-ክርስትያናትን ለመጎብኘት መምጣቷን በመግለፅ፤ በአዲስ አበባ የተከበረው የደመራ በዓል ከጠበቀችው በላይ ደማቅና አስደሳች መሆኑን ተናግራለች።
ግዩልዳን አምቢን፤ በመስቀል ደመራ በዓል ላይ ባህላዊ አልባሳቶች፣ መዝሙሮች፣ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችና የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ታሪካዊ ዳራ መመልከት አስደሳች መሆኑን ነው የገለጹት።
ባዩት ሃይማኖታዊ ሥርዓት እጅጉን መደሰታቸውን ያነሱት ግዩልዳን አምቢን፤ ኢትዮጵያ እንደሚነገረው ሳይሆን ፍፁም ሰላማዊና ኢኮኖሚዋን በፍጥነት እያሳደገች መሆኑን እንደተመለከቱ ተናግረዋል።
‘’በኢትዮጵያ ያለው የክርስትና እምነት በእጅጉ ይለያል’’ በማለት ባዩት ነገር መደሰታቸውን የተናገሩት የመስቀል በዓልን ለመታደም ከቱርክ የመጡት ሴሁን ካርታ ናቸው።
ሴሁን ካርታ በመስቀል በዓል አከባበር ላይ በርካታ ወጣቶችን መመልከታቸውና ይህም ለበዓሉ የተለየ ድምቀት መስጠቱን ነው የተናገሩት።
የመስቀል ደመራ በዓል ሁሉም ሊያከብረው የሚገባና አስደማሚ ሃይማኖታዊ ትውፊቶችን የያዘ መሆኑን በመግለፅ፤ ወደሀገራቸው ሲሄዱም በሚገባ ለማስተዋወቅ ዝግጁ መሆናቸውን አመላክተዋል።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም