አዲስ አበባ፡- መሰቀል በዓልን የምናከብረው ኃይለ እግዚአብሔርን ለማሰብ፣ በእርሱ ያለንን እምነት ለማስጠበቅና ቃለ ድህነቱን ለማሥረጽ ነው ሲሉ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተናገሩ። የመስቀል ደመራ በዓል በመስቀል አደባባይ በትናንትናው ዕለት በድምቀት ተከብሯል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፓትሪያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በዓሉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ወልደ እግዚአብሔር በሥጋ በዚህ ዓለም ተገለጦ በለበሰው ሥጋም በእኛ ፈንታ ቤዛ ሆኖ በመስቀል ላይ ሞተ ብለዋል።
የመስቀሉ ቃል ሰውን ለማዳን የተደረገ የእግዚብሔር ኃይል እንደሆነ አምነው ለሚቀበሉና ለሚኖሩበት የመጨረሻ ዕድላቸው መዳን ነው ሲል ይገልጻል ብለዋል።
በከፍተኛ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት የምናከብረው የቅዱስ መስቀል በዓልም የመንፈሳዊ እና ቁሳዊ አካላት ግጭት የፈጠረው ክስተት ነው ያሉት ፓትሪያርኩ፤ መንፈሳዊው ሰው ከመስቀሉ በቀር ከፍዳ ኃጢአት እድንበታለሁ የምለው ሌላ ትምክት የለኝም ብሎ የመስቀሉን ዘላቂ አዳኝነትን ከፍ አድርጎ እንደሚዘምር ገልጸዋል፡፡
ቁሳዊው ሃይል ባለው አቅም ሁሉ ተንቀሳቅሶ መስቀሉን ከገጸ ምድር በማስወገድ በእሱ ላይ የተመሠረተውን አስተምህሮና እምነት እንዳይነሣም እንዳይወሳም በማሰብ መቅበሩን አንስተዋል፡፡
ቁሳውያን መስቀሉን ቢቀብሩትም የመስቀሉን ቃል ሊቀበሩ አለመቻላቸውን ገልጸው፤ የመስቀሉ ቃል ቁሳዊ ሳይሆን መንፈሳዊ፣ ውጫዊ ሳይሆን ውስጣዊ፣ ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ፣ ሠብዓዊ ሳይሆን መለኮታዊ፣ ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላለማዊ በመሆኑ ቁሳዊ የሆነው ዕፀ መስቀል ቢቀበርም እሱ የተሸከመው ቃለ ድህነት በረቂቁ የሰው አእምሮ ተቀርጾና ተዘግቦ ስለሚኖር ተቀብሮ ሊቀር አልቻለም ነው ያሉት።
በሂደትም ያልተቀበረው የመስቀሉ ቃለ ድህነት በንግሥት ዕሌኒ አእምሮ ውስጥ የእምነት ኃይል የተቀበረውን ዕፀ መስቀል በዛሬው ዕለት ከጥልቅ ጉድጓድ አውጥቷል። በዚህም አሸናፊነቱን አረጋግጧል፣ ዛሬ የምናክብረው በዓልም ይኸው ኃይለ እግዚአብሔር ለማሰብና በሱ ያለንን እምነት ለማስጠበቅና ቃለ ድህነቱን ለማሥረጽ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።
በዓለ መስቀሉን ከማንኛውም ክፍለ ዓለም በተለየ ሥነ ሥርዓት ብናከብርም የመስቀሉ ሰላም ግን በሀገራችንና በሕዝባችን እየተነበበ አይደለም ብለውም፤ ይህንን ለማስገንዘብ የሚተላለፈው መልእክትም እየተደመጠ አይመስልም፤ የመስቀሉ ቃል ማለት ሰዎች በነፍሳቸውም ሆነ በሥጋቸው የተሟላ ደህንነት ያግኙ ማለት ነው ብለዋል።
የመስቀሉ ቃል ማለት ሰዎች በዚች ምድር በእኩልነት በአንድነት በመተጋገዝ በመረዳዳት በፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል በሰላም በፍቅር በስምምነት በመተባበር ይኑሩ ማለት መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
ይህንን የመስቀል ቃል ዓለም ብትቀበለው ኖሮ በየጊዜው እያንዣበበባት ያለው ስጋት ሁሉ ቦታ አይኖረውም ነበር ያሉት ፓትሪያሪኩ፤ አሁንም በመስቀሉ ስም ለዓለም ሕዝብም ሆነ ለሀገራችን ዜጎች ሁሉ የምናስተላልፈው ዐቢይ መልእክት የመስቀሉ ቃል ሁላችንንም በእኩልነትና በፍቅር የሚያስተናግድ ነውና እሱን እንቀበል ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም