የአብሮነት እሴት ነፀብራቅ

ዜና ሐተታ

ጠዋት 12 ሰዓት በመስቀል አደባባይ የእስልምና፣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እና የሌላ እምነት ተከታዮች የጋራ ዓላማ ይዘው ተሰብስበዋል። ዓላማውም በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የመስቀል ደመራ በዓል የማክበሪያ ሥፍራን ለማፅዳት ያለመ ነው።

በዚህ ተወዳጅ ሥፍራ ላይ የተለያዩ እምነት ተከታዮች መጥረጊያ እና የፅዳት ዕቃዎች ይዘው በአንድነት አካባቢውን እያፀዱ ነው። ትብብራቸው እና አንድነታቸው በተግባራቸው ጎልቶ ይታያል። አቶ አደም አብደላ በፅዳት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከተሳተፉ የእስልምና እምነት ተከታዮች አንዱ ናቸው።

አቶ አደም አብደላ ለኢፕድ እንደተናገሩት፤ በክርስትና እምነት ተከተዮች ለሚከበረው የመስቀል በዓል ድምቀት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርና የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን በደስታ እንዲያከብሩ የአጋርነት ሚናቸውን ለመወጣት የማክበሪያ ሥፍራውን እያፀዱ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በዓሉ የሚከበርበትን ስፍራ በማፅዳት የበኩላቸውን ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን የገለጹት አቶ አደም አብደላ፤ ከክርስትና እምነት ተከታዮች ጋር ያለንን የአብሮነትና የመቻቻል ባሕል አጠናክረን ለመቀጠል በዓሉ የሚከበርበትን ስፍራ አፅድተን ለበዓሉ ዝግጁ አድርገናል ብለዋል።

የሁሉም እምነት ተከታዮች በኅብረት ጠንክረን በመሥራት ድህነትን ከሀገራችን ማጥፋት ይጠበቅብናል ያሉት አቶ አደም አብደላ፤ በሀገሪቱ የሚከበሩ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ በዓላትን በሠላም፣ በፍቅርና በአንድነት የማክበር ልማድን ማስቀጠል እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

የመስቀል በዓል የሚከበርበትን ስፍራ በማፅዳት የእስልምና እምነት ተከታዮች ያሳዩት አኩሪ ተግባር የአብሮነት እሴታችን ነፀብራቅ ነው ያሉት አቶ አደም አብደላ፤ የመስቀል ደመራ በዓል ከኢትዮጵያም አልፎ የዓለም ቅርስ በመሆኑ ለጋራ ሀብታችን በጋራ ልንቆም ይገባል ነው ያሉት።

አቶ ታለግን ተማም በበኩላቸው፤ “እኛ የእስልምና እምነት ተከታዮች ያፀዳነው የክርስትና እምነት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በዓል መሆኑን በመረዳት ነው። ይህ በጎ ተግባር ዘመን ተሻጋሪ የአንድነትና የአብሮነት ፅናት ማሳያ በመሆኑ ሊጠበቅና ሊጠናከር ይገባል ይላሉ።

የተካሄደው የፅዳት ዘመቻ የእስልምናና የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘመን የዘለቀ ኅብረትና አንድነት መገለጫ ነው ያሉት አቶ ታለግን ተማም፤ በዚህም አዲስ አበባ የተለያዩ እምነት ተከታዮችና ብሔር ብሔረሰቦች መዲና የመሆኗን እውነታ ለትውልድ ለማስተማር በተግባር አጋርነታችንን እና ወንድማማችነታችንን አሳይተናል ነው ያሉት።

የፅዳት ዘመቻ መርሐ ግብሩን ያስጀመሩት የከተማ አስተዳደሩ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ፤ “እኛ ኢትዮጵያውያን አንድነታችን የጥንካሬያችን መሠረት፣ መከባበራችን የአብሮ መኖራችን ምስጢርና መለያችን ሆኖ ዘመናትን ተሻግረናል። ትውልዱም ይህንን ድንቅ ጥበብና ምስጢር ይዞ እንዲቀጥል እንሠራለን ”ብለዋል።

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በበኩላቸው የመስቀል በዓልን የምናከብረው በመስቀሉ የተሠራልንን ድንቅ ተዓምር ለመግለጽ ነው። ቤተክርስቲያኗ በመስቀሉ የምታስተምረው ሠላምን ነው። ይህንን ሠላም በትብብር ማፅናት የሁላችንም ኃላፊነት መሆኑን ይገልጻሉ።

የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዋና ፀሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ የመስቀል በዓል ከሃይማኖት መገለጫነቱ ባሻገር በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በቅርስነት የተመዘገበ በመሆኑ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኩራት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዓሉ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ሲከበር ኢትዮጵያውያውያንን በዓለም አደባባይ በማንገሥ አንድነታችንን ያጠናክራልና በልዩ ትኩረት ልናከብረው ይገባል ሲሉ ይናገራሉ።

በዓሎቻችን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድምቀቶች፣ ኩራቶች እንዲሁም ኅብረብሔራዊ አንድነታችንን የምናጎለብትበት በመሆናቸው የሚከበሩበትን ስፍራዎች በጋራ በማፅዳትና በማስዋብ አብሮነታችን የመቻቻልና የመተሳሰብ በባሕላችን ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በመርሐግብሩ ላይ ተገልጿል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You