አዲስ አበባ፦ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተሠራው ሥራ የሩዝ ልማት የመሬት ሽፋንን ከ180 ሺህ ሄክታር ወደ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር ማሳደግ መቻሉን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኢሳያስ ለማ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ ሩዝ እንደሀገር በተለየ ትኩረት እየተሠራባቸው ካሉ ሰብሎች ውስጥ አንዱ ነው። ከስንዴ ቀጥሎ ባለፉት ሁለት ዓመታት የሩዝ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጠንካራ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል። በዚህም የሩዝ ልማት የመሬት ሽፋንን ከ180 ሺህ ሄክታር ወደ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር ማሳደግ ተችሏል።
ቀደም ሲል ሩዝ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር አካባቢ፣ በኦሮሚያ ክልል እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ጉራፈርዳ አካባቢ እንደሚመረት የገለጹት አቶ ኢሳያስ፤ የዚህም የመሬት ሽፋን 180 ሺህ ሄክታር ያህል እንደነበር ተናግረዋል። ይህም እንደሀገር ካለው ፍላጎትና አቅም አንፃር በምርትም በመሬት ሽፋንም ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ከ180 ሺህ ሄክታሩ ሰባ በመቶ የሚሆነው በአማራ ክልል ብቻ ይመረት እንደነበር አንስተው፤ አሁን ላይ ሁሉም ክልሎች ልዩ ትኩረት (ኢኒሼቲቭ) በማድረግ ተግባራዊ እያደረጉት መሆኑን የገለጹት አቶ ኢሳያስ፤ በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት በተሠራው ሥራ የሩዝ ምርት የመሬት ሽፋንን ከ180 ሺህ ሄክታር ወደ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
ሩዝን በማምረት የአካባቢው አርሶ አደሮች ተጠቃሚ በመሆናቸው ደስተኛ ናቸው። በተለይ ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ ያልዋሉ መሬቶች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ የደስታቸው ሌላኛው ምንጭ መሆኑን የተናገሩት አቶ ኢሳያስ፤ መሬቶቹ ውሃ አዘል በመሆናቸው ለሩዝ ሰብል ምቹ እንደሆኑ ገልጸዋል።
በዘንድሮው የምርት ዘመን ዓመት አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በሩዝ ሰብል መሸፈን መቻሉ ትልቅ እምርታ መሆኑን የተናገሩት አቶ ኢሳያስ፤ ሩዝ ከሌሎች ሰብሎች የተለየ አሰባሰብ አለው። ለዚህም የሚያግዙ መሣሪያዎች ለአርሶ አደር የማሟላት ሥራዎች እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላው የሩዝ ልማት በሶማሌ ክልል ጎዴ አካባቢ፣ ሸበሌ ዞን፣ ሽንሌ እና ሌሎች አካባቢዎች ላይ የተጀመረ ሲሆን ይህም 500 ሄክታር መሬት ላይ ተግባራዊ ተደርጓል ያሉት አቶ ኢሳያስ፤ በክልሉ ያለው የሩዝ ሰብል ሽፋን ሦስት ሺህ ሄክታር መሬት እስኪደርስ ድረስ እየተደረገ ያለው ርብርብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በሶማሌና በአፋር ክልል የመስኖ ሩዝ ለማምረት እንዲሁም በሶማሌ ክልል ሁለተኛ ዙር ሩዝን ለማምረት ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኢሳያስ፤ የሩዝ ምርትን በሀገር ውስጥ የመተካት እቅድን ከማሳካት አንፃር ባለፉት ሁለት ዓመታት የተሰራው ሥራ አመርቂ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የሩዝ ሰብል የመሬት ሽፋን አድጓል። ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ ያልዋሉ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ተችሏል ያሉት አቶ ኢሳያስ፤ ከውጭ የሚገባውን የሩዝ ምርትን ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ.ም