የአደባባይ በዓላት ለቱሪስት ፍሰት መጨመር ያላቸውን አስተዋፅዖ አሟጦ መጠቀም ይገባል

አዲስ አበባ፡- የአደባባይ በዓላት ለቱሪስት ፍሰት መጨመር ያላቸውን አስተዋፅዖ አሟጦ መጠቀም ይገባል ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባሕል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የመስቀል ደመራ በዓል ሲምፖዚዬም “በኅብራዊ ብርሃኑ ዓለምን የሚጣራ፤ መስቀል የአንድነታችን ደመራ” በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት ተካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባሕል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃፍታይ ገብረእግዚአብሔር እንደገለጹት፤ የአደባባይ በዓላት ለቱሪስት ፍሰት መጨመር ከፍተኛ አስተዋፅዖ አላቸው። በዓላቱን ለቱሪዝም ዘርፍ ያላቸውን ዕድል አሟጦ መጠቀም ይገባል።

በመስከረም ወር ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት የመስቀል በዓል አንዱ መሆኑን አንስተው፤ በዓሉ የቱሪዝም መስሕብ እንዲሆን የበለጠ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በዓላቱን ለማክበር ከተለያዩ የዓለም ጫፎች የሚመጡ ጎብኚዎችን በዓላቱ በተመዘገቡበት ልዕልና ልክ አድርገን ማሳየት ይገባናል ብለውም፤ ይህም መዲናዋ እየሠራቻቸው ከምትገኘው የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን የማልማት ሥራ ጋር ሲደመር ቱሪዝምን ለማሳደግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

በየዓመቱ ቢሮው በዓሉን የሚዘክሩ ሁነቶችን እንደሚያዘጋጅ አንስተው፤ ይህን የምናደርገው በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበው በዓሉ ያለውን ዕሴቶች እና የነበረውን ልዕልና በአግባቡ ይዞ እንዲዘልቅ ለማስቻል ነው ብለዋል።

በዓሉ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር እንደየአካባቢው የሚለያዩ የአለባበስ እና የአጊያጌጥ ባሕሎች እንዳለው ጠቅሰው፤ እነዚህ ባሕሎች ሳይበረዙ ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገሩ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በዓሎቻችን የአንድነት እና የፍቅር እንጂ የመጠላላት ምንጭ እንዳይሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊሠሩ ይገባል ያሉት ኃላፊው፤ ለዚህ በተለይም የሃይማኖት አባቶች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ሲሉ ገልጸዋል።

አዲስ አበባ ከአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለመሆን ደፋ ቀና እያለች መሆኑን በማንሳት፤ እነዚህ የአደባባይ በዓላት ቱሪዝሙን በመደገፍ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ እና የከተማዋን ገፅታ የሚቀይሩ ናቸው ብለዋል።

በቢሮው የኪነጥበብ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሠርፀ ፍሬስብሃት በበኩላቸው የሰው ልጅ ሕይወትን ልዩ ትርጉም ከሰጠባቸው መንገዶች አንዱ በዓል ነው ብለው፤ ነገር ግን በዓላትን ስለፈለግናቸው ብቻ ልንፈጥራቸው አንችልም። በዓላቱ እንዲፈጠሩ የሚያደርጉ አመክንዮዎች አሉ ብለዋል።

በተለይም በአደባባይ በዓልነት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ይዘት ካላቸው በዓላት አንዱ መስቀል መሆኑን በመጥቀስ፤ በዓሉ የሚከበርበት ጊዜ ተከታታይ የአደባባይ በዓላት የሚከበሩበት በመሆኑ ለቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው አመላክተዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ 13 ቅርሶቿን በዓለም ቅርስነት አስመዝግባለች ያሉት ደግሞ በቢሮው የባሕል ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አስፋው ኩማ ናቸው።

ከተመዘገቡት ውስጥ አምስት ያህሉ የማይዳሰሱ ናቸው ያሉት አቶ አስፋው፤ የመስቀል በዓልም በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡት አንዱ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዓሉ ለዘመናት ሃይማኖታዊ ትውፊቱን እና ባሕላዊ ወጉን ጠብቆ እየተከበረ ነው ያሉት ኃላፊው፤ በቱሪዝም መስሕብነቱ ለኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።

ከዚህ በተሻለ መልኩ የገቢ ምንጭ እንዲሆን እና በዓለም እንዲታወቅ ቢሮው ሰፊ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

ውብሸት ሰንደቁ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You