በዞኑ ከመኸር እርሻ ከሰባት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል

ከ150 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል

አዲስ አበባ፡- በ2016/17 የምርት ዘመን ከመኸር እርሻ ከሰባት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የሀድያ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ። 150 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑም ተመላክቷል።

የዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ሀብታሙ ታደሰ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በዞኑ በመኸር እርሻ ሰብል ልማት ዘርፍ 149 ሺህ 828 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ከ150 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መሸፈን ተችሏል። ከዚህም ከሰባት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል።

በዘር ከተሸፈኑት ሰብሎች መካከልም ስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስና ባቄላ እንደሚገኙበት ጠቅሰው፤ በዞኑ በ344 ቀበሌዎች በ2 ሺህ 153 ክላስተሮች ከ51 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በስንዴ፣ በጤፍና በገብስ ዘር የተሸፈነ መሆኑን ተናግረዋል።

በክላስተር ልማቱ 74 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ አሁን ላይ ሥራው በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል።

እንደ ዞን ምርትና ምርታማነትን ለአደጋ ሊያጋልጥ የሚችል የበሽታና የአየር ሁኔታ አለመኖሩን አውስተው፤ የግብርና ባለሙያዎች በሁሉም ቀበሌዎች ተመድበው የሰብል ጥበቃና የአረም ቁጥጥር ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ ምርት በሚሰበስብበት ወቅት ለብክነት እንዳይዳረግ ፍላጎታቸውን መሠረት ባደረገ ሁኔታ በኮምባይነር በመታገዝ ምርቱን ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

በራስ አቅም ራስን በመቻል ተረጂነትን ለማስቀረት በአርሶ አደሮች ላይ የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በመኸር የታቀደውን ምርት ለማግኘት ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ እስከ እንክብካቤውና ድህረ ምርት ድረስ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ኃላፊው እንደገለጹት፤ የተለያዩ የዕፅዋት በሽታ መከላከያ ዘዴዎችን ለአርሶ አደሮች የማስተዋወቅ ሥራ ተከናውኗል።

ከስንዴ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ዋግና የተለያዩ በሽታዎች በምርታማነቱ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ቀድሞ የመከላከል ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የግብርና ግብዓቶችን በወቅቱ ለአርሶ አደሮች ተደራሽ በማድረግ የተቀናጀ የመኸር ወቅት ግብርና በታቀደው ልክ ለማሳካት በቅንጅት እየተሠራ እንደሚገኝ ሀብታሙ (ዶ/ር) አመላክተዋል።

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You