‘’ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይሌ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ሕዝብ የወደፊት እድገት መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ከአሳባቸው አንቅተው መርቀው የመሠረቱትን ይህን ሕንጻ ጥር 29 ቀን 1953 ዓ.ም የአፍሪካ አዳራሽ ብለው ሰየሙት’’ የሚል ጽሑፍ በአዳራሹ ግድግዳ ላይ ሰፍሮ ይገኛል።
ከ62 ዓመታት በፊት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አዳራሹን መርቀው በከፈቱበት ወቅት’’ የአፍሪካ አዳራሽ ብለን የሰየምነው ይህ ሕንጻ የአፍሪካ ሕዝቦች ወደተከበረው ዓላማቸው እንዲደርሱ የሚረዳና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ መጀመሪያውን የሚይዝ በመሆኑ መንፈስን የሚያነቃቃ ቋሚ መታሰቢያ ሆኖ ይኖራል’’ ሲሉ ያደረጉት ትንቢታዊ ንግግር እውን ሆኗል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ማክሰኞ ጥር 30 ቀን 1953 ዓ.ም ይዞት በወጣው የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ንግግር ‘’በውስጡ የሚገኙ የስብሰባ አዳራሾችና የጽሕፈት ቤቶች የአፍሪካውያንን ዓላማና ምኞት ከፍጻሜው ለማድረስ ዓይነተኛ ግባቸውና ተግባራቸው አድርገው የሚደክሙ ወንዶችና ሴቶች የሚሠሩባቸው ይሆናሉ’’ ባሉት መሠረት፣ ዛሬም የአፍሪካ ብርቅዬ ልጆች ለአፍሪካ ጥቅም የሚደክሙበት ስፍራ ሆኖ በአዲስ ገጽታ ፈክቷል።
ሕንጻው እ.አ.አ 1963 ሠላሳ ሁለት የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በመምከር የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የመሠረቱበት ታሪካዊ አዳራሽ ነው። በዘመናት ውስጥ በርካታ ስብሰባዎችንና የአፍሪካ መሪዎችን ውሳኔዎች አስተናግዷል።
ስለአፍሪካ አዳራሽ ሲነሳ አብረው የሚነሱት በዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በአዳራሹ መስኮቶች ላይ የተሳሉት የመስታወት ስዕሎች የአፍሪካን የትናንት ጭቆና እና መጻኢ ተስፋ አመላካች መሆናቸው ይነገራል።
ይህ ታሪካዊ ሕንፃ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ በመንግሥታቱ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ዘመኑን የዋጀ ገጽታ እንዲላበስ ተደርጎ ጥገና እና ዕድሳት ተከናውኖለት በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። ዕድሳቱም በ2017 ዓ.ም ጥቅምት ወር አጋማሽ እንደሚመረቅ ተጠቁሟል።
በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአፍሪካ አዳራሽ አስተዳደር የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አንቶንዮ ባእዮ እንደሚገልጹት፤ እድሳቱ ከ61 ዓመታት በላይ የቆየውን አዳራሽ ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ዘመኑን የዋጀ ገጽታ እንዲላበስ እያስቻለው ይገኛል። በተለይም የአፍሪካን ታሪካዊ አመጣጥ፣ አሕጉሪቱ አሁን ያለችበትን እና የወደፊት ሁኔታዋን የሚያሳይ እንዲሆን ተደርጓል።
አዲሱ የሕንጻው ዲዛይን ዘላቂ፣ ማራኪ እና ጎብኚዎችን የሚስብ ሆኖ የተቀረጸ ሲሆን ብዛት ያለው የሕንፃው ክፍል በአዲስ መልክ ዕድሳት የተደረገለት ነው። የተሠራው የዕድሳት ሥራም ሕንጻውን የማደስ ብቻ ሳይሆን የማዘመን ተግባርንም እንደሚያጠቃልል የሚጠቁሙት አንቶንዮ ባእዮ፤ ዕድሳቱ የአወቃቀርና ቴክኖሎጂ ማዘመን፣ የተሻለና ምቹ አገልግሎት ያለው፣ ቅርሶችን የጠበቀ እና ሌሎች ታሪካዊ ይዘቶችን ያጎላ ሆኖ መከናወኑ የፕሮጀክቱ ትልቅ ስኬት እንደሆነ ነው የሚያነሱት።
ለእድሳት ሥራው 57 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ በጀት እንደወጣ፤ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ብቃት ያላቸው ሥራ ተቋራጮች (ኮንትራክተሮች) ዕድሳቱን በልዩ ትኩረት እያከናወኑት እንደሚገኙና ዕድሳቱ ከአፍሪካ ታሪክ እና ትዝታ ጋር የተያያዘ መሆኑንንም አንቶንዮ ባእዮ ይገልጻሉ።
ከሕንፃው ዲዛይን በስተጀርባ ካሉት ዋና ዋና መርሆዎች ውስጥ አንዱ የአፍሪካን ታሪክ ባከበረ መልኩ ዕድሳቱን ማከናወን ነው። የዕድሳት ሥራው ዓላማ ሕንጻውን ወደነበረበት በመመለስ አዳራሹን የላቀ የድምፅ ስርጭትና ፈጣን ትርጉም በሚሰጥ ቴክኖሎጂዎች መቀየር እንደሆነ አንቶንዮ ባእዮ ያስረዳሉ።
እድሳቱ በሥነ ሕንፃ፣ በባሕልና ታሪካዊ እሴትን በጠበቀ መልኩ እየተከናወነ ሲሆን፤ በጄኔቫና በኒውዮርክ ከሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር ተመሳሳይነት እንዲኖረው ለማድረግ ጥረት ተደርጓል ሲሉም ያብራራሉ።
የአፍሪካ አዳራሽ ፕሮጀክት የሲቪል እና አርክቴክቸራል ሥራዎች ሱፐርቫይዘር ኢንጂነር ጌታቸው አርዓያ በበኩላቸው፤ ሕንጻው በራሱ ቅርስ ነው። በውስጡ የእንጨት፣ የኪነጥበብና ሌሎችም ሥራዎች ይገኙበታል። ከዚህ ውስጥም የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የጥበብ ሥራ አንዱ ሲሆን ዕድሳቱም ይህንን ለማስጠበቅ ትልቅ ሚና አለው ይላሉ።
እንደ ኢንጂነር ጌታቸው ገለጻ፤ እድሳቱ አራት ዋና ዋና ዓላማዎች አሉት። እነዚህም የሕንጻውን መዋቅራዊ ደኅንነት በማረጋገጥ ለቀጣይ ተጨማሪ ዓመታት እንዲቀጥል ማድረግ፤ የኮንፈረንስ ሥርዓቱን ማዘመን፤ የሕንጻውን ቅርስነት ማስጠበቅ እና ሕንጻው ለማኅበረሰቡ ዕይታ ክፍት እንዲሆን ማስቻል ናቸው።
አዳራሹ ፓን አፍሪካኒዝም ተቋማዊ ቅርጽ የያዘበት ቦታ መሆኑንና አፍሪካውያን በጉዳዮቻቸው ዙሪያ የመከሩበት የመጀመሪያው ስፍራ እንደሆነ የሚገልጹት ኢንጂነር ጌታቸው፤ ዕድሳቱ የአዳራሹን የሥነ-ሕንፃ ውበት ወደነበረበት መመለስ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ አንድነት እና የእድገት ምልክት የሆነውን ቦታ ዘመናዊ እንዲሆን ማስቻል ነው ይላሉ።
የዕድሳቱ አካል የሆነውና በመቋቋም ላይ የሚገኘው ቋሚ የኤግዚቢሽን ማዕከል ከሕንጻው ታሪክ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ሚና ምን እንደሚመስል በቋሚነት የሚታይበትና የአፍሪካ የፖለቲካ ታሪክ የሚገለጽበት ክፍልን ጨምሮ በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ታሪክን የሚያሳዩ ሦስት ዋና ዋና ክፍሎች እንዳሉት ኢንጂነር ጌታቸው ያወሳሉ።
ኢንጂነር ጌታቸው እንደሚገልጹት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በመቋቋም ላይ ለሚገኘው ቋሚ የኤግዚቢሽን ማዕከል ለተሽከርካሪ ማቆሚያ የሚሆን ተጨማሪ መሬት ሰጥቷል። እንዲሁም ማሊ፣ ሲዊዘርላንድ፣ ፖርቹጋል እና ኔዘርላንድ ለግንባታው የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ.ም