መስከረምና ቱሪዝም

ዜና ሐተታ

ወርሐ መስከረም ለኢትዮጵያውያን ልዩ ትርጉም አለው። የክረምቱ ዝናብ አልፎ አበቦች የሚያብቡበትና ወንዞች የሚጎድሉበት ወር ነው። ከዚህ አልፎም በክረምት ዝናብ የተለያየ ቤተሰብ የሚገናኙበትና የሚጠያየቁበት ነው። አሮጌው ዘመን ተሰናብቶ አዲሱ ዘመን የሚተካውም በዚሁ ወር ነው።

በወርሐ መስከረም በርከት ያሉ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው የአደባባይ በዓላት ይከበራሉ። የዘመን መለወጫ፣ ደመራ፣ ኢሬቻ፣ መሳላ፣ መሽቃሮ፣ ያሆዴ ከሚከበሩት በዓላት ጥቂቶቹ ናቸው። በዓላቱ የኢትዮጵያውያን ባሕል፣ ወግ፣ እሴት፣ ማንነትና አንድነት ለሌሎች የዓለም ሀገራት አጉልተው የሚያሳዩ ናቸው።

በወርሐ መስከረም የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከርና የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ምን ፋይዳ አላቸው? ብለን ላነሳቸው ጥያቄዎች የዘርፉ ምሑራን ምላሽ ሰጥተዋል።

ዐቢይ ንጉሴ ይባላሉ። በቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት የቱሪዝም አሠልጣኝ መምህር ናቸው። በኢትዮጵያ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት የሀገሪቱን ባሕል ለሌሎች ሀገራት ለማስተዋወቅና ለተተኪ ለትውልድ ለማስተላለፍ፣ ለኢኮኖሚያዊ እድገት፣ የማኅበረሰብን አንድነት ለማጠናከርና ቱሪስቶችን ለመሳብ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረክታሉ ሲሉ ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት አካባቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ሳይሆን፤ ባሕልን፣ ማንነትን፣ እሴትን፣ ትውፊትን፣ አንድነትንና እምነትንና አጠናክሮ ለትውልድ በሚያሻግር መልኩ ነው። በመሆኑም የበዓላቱን እሴትና ትውፊት በጠበቀ መልኩ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ሲሉ ያብራራሉ።

የአደባባይ በዓላትን ለመታደም ለሚመጡ እንግዶች በዓሉ በሚከበርባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻዎችን ማስጎብኘት ይገባል። በዚህ ደግሞ ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ማስተዋወቅ እና የቱሪስት የቆይታ ጊዜን በማራዘም ለአካባቢው ተጨማሪ ገቢ ማስገኘት ይቻላል ይላሉ።

ኢትዮጵያ እምቅ የቱሪዝም ሀብት አላት የሚሉት አሠልጣኙ፤ እነዚህን የቱሪዝም ሀብቶች ለማስተዋወቅ በአደባባይ የሚከበሩ በዓላት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ በመሆኑ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ያስረዳሉ።

የቱሪዝም ጋዜጠኛው ሄኖክ ስዩም በበኩሉ፤ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከበሩት የአደባባይ በዓላት የኢትዮጵያውያን ሃይማኖት፣ ባሕል እና ትውፊት በስፋት የሚንፀባረቁበት በመሆኑ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች መሳብና ማቆየት የሚችሉ ናቸው ይላል።

ይህም ለቱሪዝም እድገትና ለአካባቢው ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ፤ ሁሉም በዓላቶች በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡና እንዲታወቁ ማድረግ እንደሚገባ ይገልጻል።

የአደባባይ በዓላቱ በሚከበሩበት አካባቢዎች የበዓሉ ተሳታፊዎች የሚደምቁባቸውን አልባሳት፣ ጌጣጌጥ እና የአካባቢውን ባሕላዊ ምግቦች አዘጋጅቶ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆንና ማስተዋወቅ እንደሚገባም ይናገራል።

በኢትዮጵያ የአደባባይ በዓላትን ወቅቱን ጠብቆ ከማክበር ባለፈ፣ ባሕላዊ እሴቱን ለማጎለበት፣ በቅርስነት ለመጠበቅ፣ ለሌሎች ሀገራት ለማስተዋወቅና ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ይላል።

የአደባባይ በዓላት ከቱሪዝም ዕድገት በተጨማሪም ለኪነጥበብ እድገትና ለከያኒዎች መፈጠር ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ይናገራል።

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት ማኅበረሰብን ከማኅበረሰብ ለማገናኘት፣ ባሕልን ለማስተዋወቅ፣ አብሮነትን ለማሳደግ፣ በጎ እሴቶችን ለተተኪ ትውልድ ለማስተላለፍ ጉልህ ሚና አላቸው የሚሉት ደግሞ በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የባሕል ጥናት መምህርና የአዲስ ዓለማየሁ የባሕል ጥናት ተቋም ዳይሬክተር መስፍን ፈቃዴ (ዶ/ር) ናቸው።

የአደባባይ በዓላት የአንድን ማኅበረሰብ ምንነት፣ ባሕል፣ ታሪክና አመጋገብ ለሌላው አጉልተው ያሳያሉ። የበላይና የበታች ሳይኖር እርስ በእርስ ተከባብረውና ተዋደው እንዲኖሩም ያስችላል ሲሉ ይናገራሉ።

መስፍን (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ የአደባባይ በዓላት ሲከበሩ የሀገር በቀል አልባሳትንና ጌጣጌጦችን በማድረግ ሊሆን ይገባል። ከሀገሪቱ ባሕል ውጪ ያሉ አልባሳትና ጌጣጌጦች ኢትዮጵያን ሊገልጹና ሊያስተዋውቁ ስለማይችሉ ሁሉም እንደ እድሜ ደረጃቸው የአካባቢያቸውን የባሕል አልባሳት በመልበስ ማክበር ይገባል።

ሌሎች ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር በባሕል፣ በኢኮኖሚ፣ በቱሪዝም፣ በፖለቲካውና ፍልስፍና ሊተሳሰሩ የሚችሉት እኛ እኛን ሆነን ስንቀርብ ነው ይላሉ።

አንድ ማኅበረሰብ ከባሕል ወጣ ማለት ዓሣ ከባሕር ወጣ እንደማለት ነው የሚሉት መስፍን (ዶ/ር)፤ ዓሣ በባሕር ውስጥ ሕልውናው እንደሚጠበቀው ሁሉ ሀገርም በባሕል ሲደገፍ ሕልውናው ይቆያል። ባሕል የሀገር ሕልውና እና የማኅበረሰብ መንፈሳዊና ቁሳዊ መገለጫ በመሆኑ እሴቱን ጠብቆ ለትውልድ ማሻገር ይገባል ሲሉ ያመላክታሉ።

በራሱ ባሕል የሚኮራ ትውልድን ለማፍራት መንግሥት፣ ወላጆችና መምህራን ድርሻቸው ከፍተኛ ነው የሚሉት መስፍን (ዶ/ር)፤ ወላጆች ለልጆቻቸው በሀገሪቱ የሚከበሩ የሃይማኖታዊና ባሕላዊ በዓላትን አንድምታ በቤታቸው ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል።

መንግሥትም የበዓላቱን ትርጉም በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ በማካተት ልጆች በትምህርት ቤት እንዲማሩት በማድረግ ከሀገሪቱ ባሕል፣ እምነት፣ ወግና ሥርዓት ጋር የሚጻረሩ መጤ ባሕልን መከላከል ይቻላል ይላሉ።

አንድምታቸው በቃል ብቻ እየተነገረ ያለ ባሕልና ታሪኮችን በጽሑፍና በምስል በማደራጀት የውጭው ማኅበረሰብ በሚያውቁት ቋንቋ ተርጉሞ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በማቅረብ ቱሪስቶችን መሳብ ይቻላል ሲሉ ያስረዳሉ።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው፤ በመስከረም ወር የሚከበሩ የተለያዩ በዓላት ለቱሪዝም ገቢ ዕድገት ያላቸውን ሰፊ ጠቀሜታ በመረዳትና ከክልሎች ጋር በመነጋጋር ሚኒስቴሩ የተለያዩ የጉብኝት ጥቅሎችን አዘጋጅቶ እያስተዋወቀ ይገኛል ይላሉ።

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የቱሪስት መስሕቦችን በመለየትና በማስተዋወቅና የገቢ ምንጭ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተጠናከረ እንቅስቃሴ ሊያደርጉ እንደሚገባ ያስረዳሉ።

በመስከረም ወር የሚከበሩ በዓላቶች ከሃይማኖታዊና ባሕላዊ ትውፊት ባለፈ ቱሪዝሙንና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያላቸው ናቸው። በዓላቱን ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን በሚሄዱበት አካባቢ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥልጠና መሰጠቱን ይናገራሉ።

በዓላቱ በሚከበሩበት ወቅት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ዜጎች በልዩ ሁኔታ ማስጎብኘት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You