አዲስ አበባ፡- ትምህርት ከየትኛውም ፖለቲካ እንቅስቃሴ ጋር የማይገናኝ በመሆኑ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የመማር ማስተማር ሥራውን ከማስተጓጎል እንዲቆጠቡ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አሳሰበ፡፡
የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በክልሉ ለመመዝገብ ከታቀደው 7 ሚሊዮን ተማሪዎች ውስጥ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት አልተመዘገቡም፡፡
ከነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የተማሪዎች ምዝገባ እየተካሄደ ይገኛል ያሉት አቶ ጌታቸው፤ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ነባርም ሆነ አዲስ ተማሪዎች ምዝገባ እንዲያካሂዱ ለማድረግ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ እስካሁን የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር ካለፉት ዓመታት አንጻር ሲታይ ግን ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡
ከመስከረም 7 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮም በክልሉ የመማር ማስተማር ሥራው ተጀምሯል ያሉት ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል እንዲመዘገቡ ከሚጠበቁ ተማሪዎች 27 በመቶ የሚሆኑ እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ወደ 20 በመቶ የሚጠጉ ተማሪዎች ብቻ መመዝገባቸውን ጠቁመዋል፡፡ ምዝገባው አሁንም በመካሄድ ላይ በመሆኑ ቁጥሩ እየጨመረ ይሄዳል የሚል ተስፋ መኖሩን ገልጸዋል።
በክልሉ ያለው የፀጥታ ችግር ሁኔታ ተማሪዎች በሚፈለገው ልክ እንዳይመዘገቡ ማድረጉን ጠቁመው፤ የመማር ማስተማር ሥራዎች በአግባቡ አለመካሄድ ትውልዱ ላይ ከፍተኛ ስብራት የሚፈጥር ነው፡፡ በመሆኑም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎችም ትምህርት ከየትኛውም ፖለቲካ ጋር የማይገናኝና ትውልድ የሚቀረጽበት መሆኑን በመገንዘብ የመማር ማስተማር ሥራውን ከማደናቀፍ ሊታቀቡ ይገባል ብለዋል፡፡
ትምህርት ትውልድ የሚቀረጽበት ሂደት ነው ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ ትምህርት ቤቶችም ዜጎችን ለመቅረጽ የተቋቋሙ ናቸው፡፡ በመሆኑም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሄደው እንዲመዘገቡና ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡
በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ባለፈው ዓመት ከ4 ሺህ በላይ የትምህርት ተቋማት ተዘግተው መክረማቸውን ያመለከቱት አቶ ጌታቸው፤ በዚህም ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተለይተው ቆይተዋል፡፡ 12ኛ ክፍል መፈተን የነበረባቸው ተማሪዎችም ሳይፈተኑ ቀርተዋል ብለዋል፡፡
ይህ ሁኔታ ደግሞ ተማሪዎችና ወላጆች ላይ የሚፈጥረው የሥነ ልቦና እና በአጠቃላይ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የሚፈጥረው ችግር ከፍተኛ ስለሆነ ይህን ሁኔታ ለመቀየር መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ቢሮው አስፈላጊ ግብዓቶችን ለማቅረብና የመማር ማስተማር ሥራው በአግባቡ እንዲካሄድ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አስታውሰው፤ ከተፅዕኖ ባለፈ ግን ተማሪዎች ከመስቀል በኋላ ወደ ትምህርት ቤት የመምጣት ልምድ መኖሩም በተማሪዎች ቁጥር መቀነስ ላይ የራሱን አሉታዊ አስተዋፅዖ አበርክቷል ሲሉም ጠቁመዋል፡፡
ስለሆነም ከማኅበረሰቡ ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አወንታዊ ሚናቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን መስከረም 15 ቀን 2017 ዓ.ም