ኢሬቻ – የኅብር ትዕምርት

የኢሬቻ በዓል በየዓመቱ በመስከረም ወር በድምቀት እንደሚከበር ይታወቃል፡፡ በተለይም በሆረ ፊንፊኔና በቢሾፍቱ ሆረ አርሰዲ በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ በተሰበሰበበት በድምቀት ይከበራል፡፡ ለመሆኑ የኢሬቻ በዓል ታሪካዊ መሠረትና አከባበር፤ በዓሉ ለኦሮሞ ሕዝብ ያለው ጠቀሜታ ምንድነው? ስንል የዘርፉን ምሑራን አነጋግረናል፡፡

በኦሮሞ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት የኦሮሞ ሥነ ጽሑፍ ፎክሎር ተመራማሪ ጌታቸው አበራ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኢሬቻ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ፈጣሪን(ዋቃ) ለማመስገን፣ ለመለመን ተሰባስቦ የሚወጣበት የምስጋና በዓል ነው፡፡

ኦሮሞ ባሕሉን፣ ቋንቋውን፣ ማንነቱን፣ የሚያንፀባርቅበት የራሱ የሆነ የገዳ ሥርዓት ያለው ሕዝብ ነው ያሉት ተመራማሪው፣ ኢሬቻ በገዳ ሥርዓት ውስጥ ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ከሚያንፀባርቁ ሥርዓቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ኢሬቻ በተለያዩ ስያሜዎች የሚጠራ ሲሆን በቱለማዎች ኢሬቻ፣ በመጫዎች ኢሬስ፣ በሐረርጌ ኢሬሳ፣ እንደሚባልና ሌሎች ስያሜዎችም እንዳሉት ጠቅሰው፣ በተለያዩ ስያሜዎች ይጠራ እንጂ የሚፈጸመው ሥርዓት ግን አንድ አይነት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ በምሥጋና፣ በጸሎት ፈጣሪን (ዋቃ) ለመለመን፣ ለማመስገን ተሰባስቦ የሚወጣበት መሆኑን በመግለጽ፣ በዓሉ የኦሮሞ ሕዝብ ለምሥጋና በፈጣሪ ፊት የሚቀርብበት እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

ኢሬቻ በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚካሄድ ቢሆንም በዋናነት በሁለት ኢሬፈናዎች እንደሚከበር ገልጸው፣ እነዚህም ኢሬቻ ቱሉና ኢሬቻ መልካ ተብለው ይጠራሉ ሲሉ አቶ ጌታቸው ይናገራሉ፡፡

ሕዝቡ ከቀበሌው ከመንደሩ ጀምሮ በአካባቢው በሚገኙ መልካዎች ላይ ተገኝቶ ኢሬፈና ያካሂዳል ያሉት ተመራማሪው፣ በመስከረም ወር አንድ ቦታ ላይ ተሰብስበው የሚያከብሩት ትልቁ ኢሬቻ በዓል መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

የክረምቱን ጨለማ፣ ጭቃ፣ ዝናብ አውጥቶ ለመስከረም አደይ ያሸጋገረውንና እርጥበትን ለሰጠ ፈጣሪ (ዋቃ) ምስጋና እንደሚቀርብ ጠቅሰው፣ ከፊታችን ያለው ጊዜ ብርሃን ነው በማለት አበባና እርጥብ ሣር በመያዝ ለምስጋና ወደ መልካ እንደሚወጣ ይገልጻሉ፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ እርጥብ ሣር፣ አበባ ይዞ ለምስጋና ወደ መልካ ሲወጣ የተለያዩ ትርጓሜዎች ሲሰጡ እንደሚስተዋል በመግለጽ፣ ነገር ግን ኢሬቻ በአንድነት ሆኖ ፈጣሪውን (ዋቃ) የሚያመሰግንበት፣ የሚገናኝበት፣ የሚወያይበት፣ ባሕሉን የሚያንፀባርቅበት፣ የእርቅ፣ የአንድነት የሠላም የምስጋና በዓል ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ኢሬቻ ከኦሮሞ ሕዝብ አልፎ በሀገሪቱ በሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችም ዘንድ በድምቀት የሚጠበቅ በዓል መሆኑን ገልጸው፣ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በደስታ መጥተው የሚሳተፉበትና የርስ በርስ ትስስር የሚፈጠርበት እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡

በኢሬቻ ዙሪያ የብሔር ብሔረሰቦች አመለካከት እየተቀየረ መጥቷል የሚሉት አቶ ጌታቸው፣ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን የሚፈጥር፣ የአንድነት፣ የፍቅር፣ ሠላም አስፋኝ መሆኑን ተረድተዋል ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ኢሬቻ ሠላም፣ እርቅ፣ ፍቅር፣ መረጋጋት የሚፈጠርበት ቦታ በመሆኑ ከጥንት ጀምሮ ኢሬፈና ሲካሄድ የመጣ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢሬቻ ቱሉና መልካ ከኦሮሞ ሕዝብ አኗኗር ጋር በቀጥታ የሚገናኝ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ኢሬቻ በውስጡ ከሚገኙ እሴቶች መካከል ግንኙነት ለመፍጠር፣ ሀገራዊ አንድነትን ለማምጣት፣ እርቅ ለማውረድ፣ ሠላምን ለማምጣት ከፍተኛ ቦታ እንዳለው ይገልጻሉ፡፡

በዓሉ እስካሁን ከተደረገበት ጥናትና ምርምር ባሻገር ለሀገር ጥቅም ላይ መዋል በሚችል መልኩ ሊሠራበት እንደሚገባ በመግለጽ፣ ኢሬቻን ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድም ምሑራን፣ ሚዲያ፣ የኦሮሞ ሕዝብና መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡

ኢሬቻ እርጥብ ሳር በመያዝ ፈጣሪ (ዋቃ) የሰጠውን ስጦታ የሚመሰገንበት ነው የሚሉት ደግሞ በጂማ ዩኒቨርሲቲ የኦሮሞ ሥነጽሑፍ ፎክሎር መምህር ደረጄ ፉፋ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ኦሮሞች በኢሬቻ ከክረምት ወደ መስከረም(ቢራ) ላሸጋገረው ፈጣሪ (ዋቃ) ነው በማለት ያመሰግናሉ ያሉት ደረጄ (ዶ/ር)፣ ሠላም፣ አንድነትን፣ አብሮ መኖርን አድለን በማለት ይለምናሉ ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ኢሬቻ ካሉት ጠቀሜታዎች መካከል ሠላምን ማውረድ፣ እርቅን ማምጣት፣ አብሮነትን፣ አንድነትን የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰው፣ ባሕሉን፣ ሥርዓቱን፣ እሴቱን፣ ሕጉን በጠበቀ መልኩ በኢሬቻ ሠላምን ማውረድ፣ አንድነትን ማምጣት የሚቻልባቸው ጉዳዮች ሊታወቁ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡

የኢሬቻን የአንድነት፣ ሠላም፣ የመተሳሰብ፣ እሴትና ባሕሉን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ፣ በዓመት ተሰብስቦ ማክበር ብቻ ሳይሆን የኢሬቻ እሴት የሆኑትን አንድነትን፣ ሠላምን በማውረድ በጋራ መኖር እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ፡፡

ኢሬቻ እንዴት ጀመረ፣ ከምን ተጀመረ፣ እንዴት መቀጠል አለበት፤ የሚለውን በትክክል ጥናት ሊደረግበት እንደሚገባ የገለጹት ደረጄ (ዶ/ር)፣ ኢሬቻ የሠላም፣ የአንድነት በዓል መሆኑ ከመሠረቱ ጀምሮ በትክክል ተጠንቶ ሕዝቡን ማስገንዘብ እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡

ኢሬቻን የኦሮሞ ብቻ አድርጎ ማየት ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ በኢሬቻ ሠላም፣ ምሥጋና፣ አንድነት የሚሰበክበት በመሆኑ ጉዳዩ የጋራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የኢሬቻን ሥርዓቱ፣ እሴቱን፣ የፈጣሪንና ፍጡርን ሕጎች ማወቅና ማክበር፣ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ፣ ይህን ማድረግ ሲቻል ሠላም፣ አንድነት፣ መግባባትን፣ መቀራረብን መፍጠር እንደሚችል ያስረዳሉ።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን መስከረም 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You