ሰብሎች ለማደግና ፍሬ ለመስጠት በአፈር ውስጥ የሚገኘውን ንጥረ ነገር ሁሉ ይመገባሉ፡፡ በሥራቸው አማካኝነት ያገኙትን ንጥረ ነገር ሁሉ ይመገባሉ። በዚህ ሂደት አላስፈላጊ ንጥረ ነገሮችንም ጭምር ወደ ውስጣቸው በማስገባት ለአደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ በሀገራችንም አንዳንድ አካባቢዎች ላይ በእድገታቸውና በፍሬማነታቸው ላይ ስጋት የደቀነ ክስተት እየተፈጠረ ነው፡፡ ለዚህ መነሻው ደግሞ የአፈር አሲዳማነት ነው፡፡
በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው የአፈር አሲዳማነት በግብርናው ዘርፍ ላይ ትልቅ ስጋት ደቅኗል፤ ከአራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በከፍተኛ አሲዳማነት ተጠቅቷል፡፡ በከፍተኛ አሲዳማነት ከተጠቃው አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ አንድ ሚሊዮን ሄክታሩ ምንም አይነት ምርት አይሰጥም፡፡
ምርት እየሰጠ ያለው መሬት በዝቅተኛ፤ በመካከለኛና በከፍተኛ አሲዳማነት እየተጠቃ ነው፤ በአጠቃላይም 12 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዝቅተኛ፣ በመካከለኛ፣ በከፍተኛ የአሲድ መጠን ተጠቅቷል፡፡ ይህም በግብርናው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል፡፡
የአፈር አሲዳማነት በማከም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ እየተሠራ ቢሆንም እስካሁን በአሲዳማነት ከተጠቃው 43 በመቶ መሬት ውስጥ 140 ሺህ ሄክታር ብቻ ነው የታከመው፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈፃሚ ፋኖሴ መኮንን ለኢፕድ በሰጡት አስተያየት፤ የአፈር አሲዳማነት በኢትዮጵያ ግብርና ምርትና ምርታማነት ትልቅ ስጋት ሆኗል፤ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በከፍተኛ አሲዳማነት ተጠቅቷል፤ በከፍተኛ አሲዳማነት ከተጠቃው አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ አንድ ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው ምርት ከመስጠት ሙሉ በሙሉ ወደ አለመስጠት ተሸጋግሯል፡፡
በኢትዮጵያ ለእርሻ አገልግሎት የሚውለው መሬት በከፍተኛ ዝናብ ጥርጊያ፣ በአፈር መሸርሸር፤ የሰብል ቅሪትን ሙሉ በሙሉ በማንሳት አፈሩ በከፍተኛ ሁኔታ ለአሲዳማነት እየተጋለጠ ነው፡፡ በየዓመቱ የአሲዳማነት መጠን ዝቀተኛ የነበረው አፈር ወደ መካከለኛ፤ መካከለኛው ወደ ከፍተኛ እያደገ ነው፤ በዝቅተኛ፣ በመካከለኛ፤ በከፍተኛ የአሲዳማነት መጠን የተጠቃው በአጠቃላይ 12 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ይሆናል፡፡ ይህም በሌሎች ሀገራት አንድ ራሷን የቻለች ሀገር የሚያህል ነው ይላሉ፡፡
በአፈር ውስጥ ያሉት “ካታላይኖች”ና ለተፈጥሮ ሀብት ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮች እንደ ካልሲየም፤ ማግኒዚየም፣ ፖታሽየም የመሳሰሉ ማዕድናት በዝናብ ውሀ በመታጠብ በአፈር ውስጥ የናይትሮጂን፣ የአልሙኒየም ንጥረ ነገር እየበዛ ሲመጣ አፈሩ አሲዳማ ይሆናል፡፡ አሲዳማ የሆነ አፈር የሰብል እድገትን በማቀጨጭ ሙሉ ለሙሉ ምርት እንዳይሰጥ ያደርጋል ሲሉ ይናገራሉ፡፡
የአፈር አሲዳማነት የሰብሎችን ስር ያቃጥላል፤ እድገታቸውን ይጎዳል፤ አየርና ውሀ ከመሬት ስር ለመውሰድ እንዲቸገሩ ያደርጋል፤ ለሰብሎች የሚያስፈልጉ ንጥረ ነገሮችን የሚያብላሉ ማይክሮ ኦርጋኒዝሞች ሥራ ላይ እንዳይውሉና ለአዝርዕቶች እድገት የሚጠቅመው የፎስፎረስ ንጥረ ነገር እንዳይደርስ ያደርጋል፤ የአፈር ማዳበሪያ 70 በመቶ ጥቅም ላይ እንዳይውል በማድረግ የሀገርን ግብርናና ኢኮኖሚ እየጎዳ ነው ሲሉ ያብራራሉ፡፡
በምዕራብ ኢትዮጵያ ምዕራብና ምሥራቅ ወለጋ በተለይ መንዲ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም፤ በአዊ ዞን፤ በደቡብ ጎንደር፣ ቤንሻንጉል ክልል አሶሳ፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሲዳማ አካባቢ ከፍተኛ በአሲዳማነት የተጠቃ አፈር እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ለግብርናው ዘርፍ ስጋት የሆነውን የአፈር አሲዳማነት የአፈርና የውሃ ጥበቃ በመሥራት የመከላከልና የተጠቃውን በግብርና ኖራ የማከም ሥራ እየተሠራ ነው፤ አንድ ሄክታር መሬትም በአማካኝ 30 ኩንታል የግብርና ኖራ ይፈጃል፤ በግብርና ኖራ የታከመ መሬትም ከአራት እስከ ስድስት ዓመት ከፍተኛ ምርት ይሰጣል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር በአፈር ሀብት ልማት የአፈር ጤንነትና ልማት ማሻሻያ ዴስክ ኃላፊ ሙሉጌታ አበራ በበኩላቸው፤ ከፍተኛ የዝናብ መጠን ባለባቸው አካባቢዎች የአፈር አሲዳማነት እየተስፋፋ ነው፡፡
በ1989 ዓ.ም በተጠና ጥናት በኢትዮጵያ ለአፈር አሲዳማነት የተጋለጠው የመሬት ከፍል 40 በመቶ ነበር፤ አሁን 43 በመቶ ሆኗል። ባለፉት 27 ዓመታት የአፈር አሲዳማነት ሦስት በመቶ ጨምሯል፤ ሦስት በመቶ የሚታረስ መሬት ብዙ ነው፤ ቀላል የሚባል አይደለም፤ የአፈር አሲዳማነት ለምርትና ለምርታማነት ትልቅ ስጋት መሆኑንም ያሳያል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
በተጨማሪም በ2014 ዓ.ም በተሠራ ሀገር አቀፍ ጥናት ሦስት ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት አሲዳማ መሆኑ ተረጋግጧል፤ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬትም በመካከለኛ አሲዳማነት መጠን እንደተጠቃ ጥናቱ አረጋግጧል ብለዋል።
በሀገሪቱ ከፍተኛ ዝናብ አፈሩ መሸርሸሩ፤ የማሳ ተረፈ ምርቶችን ሙሉ በሙሉ ማንሳት የአፈር አሲዳማነትን ሽፋን እየጨመረ ነው፤ ከዓመት ዓመት እየጨመረ የመጣው የአፈር አሲዳማነት ለምርታማነት ስጋት እየሆነ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
በአሲዳማነት የተጠቃ መሬት የአፈር ማዳበሪያም ሆነ ምርጥ ዘር መጠቀም ቢቻልም ምርት አይሰጥም፤ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራ በመሥራት፤ የተጠቃውንም በግብርና ኖሯ በማከም ከ50 እስከ 100 ፐርሰንት ምርት እንዲሰጥ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው፤ እየተሠራ ባለውም ሥራ ከ2006 እስከ አሁን ማለትም ከ2016 ዓ.ም አንድ መቶ 40ሺህ ሄክታር መሬት በግብርና ኖራ ታክሟል ሲሉ ተናግረዋል።
የአፈር አሲዳማነትን በመከላከል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የአፈር ማዳበሪያን በጥናት የመጠቀም፤ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራ መሥራት፤ የሰብሎችን ቅሬት ማሳው ላይ እንዲቀሩ የማድረግ፤ ወደ አሲዳማነት የተቀየረውን መሬት በግብርና ኖራ የማከም፤ ችግሩንም በዘላቂነት ለመፍታት የተፈጥሮን ማዳበሪያ የመጠቀም ሥራ እየተሠራ ነው ይላሉ።
በግብርና ኖራ የታከመ አሲዳማ አፈር በከፍተኛ ሁኔታ እስከ ስድስት ዓመት ምርት ይሰጣል፤ በ2017 ዓ.ም ሦስት መቶ ሺህ ሄክታር መሬት ለማከም እየተሠራ ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን መስከረም 15 ቀን 2017 ዓ.ም