ዜና ሐተታ
ሃይማኖታዊም ሆኑ ባሕላዊ በዓላት የጋራ ዕሴት የሚያዳብሩና ለማኅበራዊ መስተጋብር የቀኝ እጅ በመሆን ስለሠላም የሚሰብኩ ናቸው። ኢትዮጵያውያን ደግሞ በዚህ ብዙ ልምድ አላቸው፡፡ የተለያዩ ባሕላዊ፣ ሃይማኖታዊ ዕሴቶች፣ ወግና ልማዶች ለዚህ ማሳያዎች ይሆናሉ፡፡
ወርሐ መስከረም ኢትዮጵያውያንን በገመደው ባሕላዊና ሃይማኖታዊ እሴቱ በኩረ ወራት የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ከእነዚህም ባሕላዊና ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት፣ መስቀልና ኢሬቻ በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው።
በመስከረም ተስፋ፣ ልምላሜ፣ ቸርነት፣ ምሕረት፣ ይቅርታ፣ ቃልኪዳንና እምነት በሰው ልጆች ልቦና ሰፊ ቦታ አላቸው፡፡ ማኅበራዊ እሴቶች ለሰው ልጆች ጠንካራ ሥነልቦናዊ ውቅር ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ ከበዓላቱ ትሩፋት ለመቋደስና እኩይ ዓላማ ያነገቡ የሴረኞችን ሃሳብ ማምከን የሁሉም ኃላፊነት ቢሆንም ሴቶች በዚህ ጉዳይ ባለጥምር ድል ተጋሪዎች ናቸው፡፡
ሴቶች የማኅበረሰቡ ግማሽ አካል መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ባላቸው ተፈጥሯዊ ብልሃት የማኅበረሰቡን ሠላም ለማጽናት ልዩ ተሰጥዖ ተችሯቸዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮም ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት በሁሉም ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ የመዲናዋ ሴቶች ጋር “ሴቶች ለሠላም፣ ሠላም ለሴቶች” በሚል መሪ ሃሳብ በመስቀል፣ በዳመራና በኢሬቻ በዓላት አከባበር ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
በዓላቱ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ይዘታቸው ጠብቀው እንዲከበሩ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የበኩላቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን ለኢፕድ አስተያየታቸውን የሰጡ የመዲናዋ ሴቶች ይናገራሉ፡፡
ወይዘሮ እህታለም ዓለሙ በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ ስድስት ነዋሪ ናቸው፡፡ የሴትነት ብልሃትን በመጠቀም ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ መስጠት በአደባባይ በዓላቱ ከሴቶች የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው ይላሉ፡፡ በበዓላቱ ፀረ-ሠላም ኃይሎችን እንዴት መግታት ይቻላል የሚለው ከታችኛው የሴቶች መዋቅር ጀምሮ ሲሠራ መቆየቱን ያብራራሉ፡፡
ሠላም ለሰው ልጅ የመኖር ዋስትና ነው የሚሉት ወይዘሮ እህታለም፤ የመዲናዋ ሴቶችም ይህንን በመገንዘብ በነቂስ ወጥተው እየተሳተፉ እንደሚገኙ ይጠቁማሉ። ለሠላም ዘብ መሆን እና የሠላም ኃይላትም እጅ በእጅ በመያያዝ በአብሮነት መቆም እንደሚያስፈልግ መክረዋል፡፡
ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶች ሠላም ከማስጠበቅ በተጨማሪ መንገድ የጠፋቸው እንግዶች መንገድ የመጠቆም እንዲሁም ሆቴሎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ በየአካባቢው ክትትል እንደሚያደርጉ ይገልጻሉ፡፡
በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ አንድ ነዋሪ ወይዘሮ የውብዳር ከተማ በበኩላቸው በክፍለ ከተማው በተለይ ወንጀልን ከመከላከል አንጻር በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል ያሉ ሲሆን በመጪው በዓላትም ሠላም ለማስፈን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ይናገራሉ፡፡
እንደ ወይዘሮ የውብዳር ገለጻ፣ በክፍለ ከተማው ለስጋት ተጋላጭ የሆኑና ዳመራ የሚደመርባቸው ቦታዎች ተለይተዋል፡፡ ለበዓላቱ የሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ያለምንም እንግልት በሠላም እንዲያከብሩ የተለያዩ የትኩረት አቅጣጫዎች ተቀምጠው እየተሠራ ነውም ይላሉ፡፡
ሴት ልጅ በማኅበረሰብ ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ የመፍጠር ችሎታ አላት የሚሉት ወይዘሮ የውብዳር፣ ይህንንም ዕድል ወደ ውጤት በመቀየር ለበጎ ዓላማ ማዋል ይገባልም ባይ ናቸው፡፡
የአደባባይ በዓላቱ በሠላም ተከብረው የሚፈለገውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሴቶች ለሠላም ቅድሚያ ሰጥተው የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ ነው ያሉት ደግሞ የሠላም ሠራዊት አባል ወይዘሮ ወይንሸት ኬሜ ናቸው፡፡
በዓላቱ በተገቢው መልኩ ተከብረው እንዲጠናቀቁ ለፀጥታ አካላት የተደራጀ መረጃ መስጠትና ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ከመፍጠር ረገድ ከወዲሁ ወደ ሥራ መገባቱን ያስረዳሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው ከዚህ በፊትም በመዲናዋ ሴቶች ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው በመሥራታቸው ውጤታማ መሆን እንደተቻለም ይናገራሉ።
የከተማዋ የሠላምና ፀጥታ እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል የሚሉት ወይዘሮ ሊዲያ፤ በተለይ በከተማው የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ አስተዋፅዖ ማበርከቱን ያክላሉ፡፡
ሴት ልጅ በተሰማራችበት መስክ ሁሉ የፈጻሚነት አቅም፣ የማስተባበር ችሎታ እንዲሁም ማኅበረሰብ አቀፍ ውይይቶች በበላይነት የመምራት አቅም ያላት መሆኗ በሠላም ዙሪያ ያላት ሚና የላቀ እንደሚያደርገው ይጠቁማሉ፡፡
የመስቀልና የኢሬቻ በዓላት በቱሪዝሙ ዘርፍ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ እምር የሚያመጡና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ፍሰት የሚጨምሩ በመሆናቸው በዓላቱ በሠላም እንዲጠናቀቁ ሴቶች በንቃት መሳተፍ እንደሚጠበቅባቸው ያስገነዝባሉ፡፡
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2017 ዓ.ም