ከ16 ሺህ በላይ ወጣቶች የመስቀልንና የኢሬቻን በዓል በማስተባበር ይሳተፋሉ

አዲስ አበባ፡– የፊታችን ሐሙስ መስከረም 16 በሚከበረው የደመራ በዓል እንዲሁም መስከረም 25 ቀን 2017 በመዲናችን አዲስ አበባ በሚከበረው የኢሬቻ በዓል በማስተባበር ከ16 ሺ በላይ የማኅበሩ አባላት ከዝግጅቱ ጀምሮ በሂደቱ እየተሳተፉ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ገለጸ፡፡

የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ወጣት ፎሊ ንጉሤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፀችው፤ ማኅበሩ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል የማኅበሩ አባላትና የከተማው ወጣት በነቂስ ወጥቶ ሀገር አቀፍ በዓላትን በበጎ ፈቃድ እንዲያስተባብርና ለሠላም ዘብ እንዲቆም ማድረግ ነው፡፡

በያዝነው የበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ከራሱ ጀምሮ በአጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ የሠላም ማስከበር ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝበት ሁኔታ መኖሩን አመልክታለች፡፡

የፊታችን ሐሙስ የሚከበረው የደመራ በዓል እና በዚሁ ወር የሚከበረው የኢሬቻ በዓል የአደባባይ በዓል እንደመሆናቸው ለብዙ ነገር ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቁማ በሠላም ተጀምረው በሠላም እንዲጠናቀቁ ማኅበሩ፤ ከዝግጅቱ ጀምሮ እያስተባበረ እንደሚገኝ አስታውቃለች፡፡

ማኅበሩ በክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃ የራሱ አደረጃጀት ያለው መሆኑን ጠቁማ፤ ከሚመለከታቸው የሠላምና ፀጥታ አካላት፤ ከቢሮና ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሠላም የሚያስጠብቅበት ሁኔታ እንዳለም ገልጻለች፡፡ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ በበዓላቱ ላይ እንዲሳተፍ፤ ግንዛቤዎችን የመፍጠር፤ የማነቃቃት ሥራዎችን እየሠራ መገኘቱንም አስረድታለች፡፡

“ማኅበራችን የብዙኃን ወጣቶች ማኅበር ነው” ያለችው ምክትል ፕሬዚዳንቷ ወጣት ፎሊ፤ በተለይም ደግሞ በበጎ ፈቃድ በስፋት የሚሠራባቸው ሂደቶች ስላሉ በወጣቱ ከዚህ በፊት ሲፈጠር የነበረው ግንዛቤ ሄዶ አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ጋር የደረሰበት ሂደት መኖሩንም አብራርታለች። ይሄን የበጎ ፈቃድ ፅንሰ ሀሳብም ሁሉም ወጣት ወስዶና በነቂስ ወጥቶ የበጎ ፈቃድ ተግባር እንዲያከናውንም ጥሪዋን አስተላልፋለች፡፡

የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደ ከተማ አስተዳደር ለረጅም ዓመታት በዕቅድ ተይዞ እየተሠራበት መሆኑን የጠቆመችው ምክትል ፕሬዚዳንቷ፤ ባለፈው 2016 ዓ.ም  የተለያዩ በጎ ፈቃድ ተግባራትን ለማከናወን በዕቅድ ደረጃ ተይዞ የተገባበት ሁኔታ የነበረ መሆኑንም አስታውሳለች፡፡

ወጣት ፎሊ ንጉሤ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደ ከተማ አስተዳደር ለረጅም ዓመታት በዕቅድ ተይዞ እየተሠራበት መሆኑን ጠቁማ፤ ባለፈው 2016 ዓ.ም የተለያዩ በጎ ፈቃድ ተግባራትን ለማከናወን በዕቅድ ደረጃ ተይዞ የተገባበት ሁኔታ የነበረ መሆኑንም ተናግራለች፡፡

የማጠናከሪያ ትምህርት፤ የተለያዩ የአይሲቲና አጫጭር ኮርስ ሥልጠናዎችን፤ ደም ልገሳ፤ ቤት እደሳ፤ ማዕድ ማጋራት፤ ኮሪደር ልማት ያሉ ሰብዓዊ አገልግሎቶች በበጎ ፈቃደኛ ወጣቱ በነፃ ሲከናወኑ መቆየታቸውን አብራርታለች። በዚህም ማኅበሩ ለማከናወን ካቀደው ከ75 በመቶ በላይ ለማሳካት ስለመቻሉም ጠቅሳለች ፡፡

የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራው በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው ያልተዘጋና እየተከናወነ የሚገኝ መሆኑን ጠቁማም የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ትምህርት ቤት በመከፈቱና አንዳንድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች በመጠናቀቃቸው የተዘጉ መሆናቸውንም ተናግራለች፡፡

“ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ ከተማችን የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ የተለያዩ የልማት ሥራዎች በተለያዩ ወቅቶች ይሠራሉ” ያለችው ምክትል ፕሬዚዳንት ፎሊ፤ ከክረምቱ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሳይዘጋ በበጋውም የቀጠለው ይሄው የኮሪደር ልማት ስለመሆኑ አስታውቃለች፡፡

ሠላማዊት ውቤ

 አዲስ ዘመን መስከረም 15/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You