አዲስ አበባ፦ በቱሪዝም ዘርፍ በስፋት እየሠራች ካለችው ኢትዮጵያ ጋር ሁለንተናዊ ትብብር በማድረግ ለጋራ ተጠቃሚነት እንሠራለን ሲሉ በኢጋድ አባል ሀገራት የቱሪዝም ጉባኤ ላይ የተሳተፉት የደቡብ ሱዳን እና የጅቡቲ ልዑካን አባላት ተናገሩ።
በአዲስ አበባ በተካሄደው በዚሁ ጉባኤ ላይ ከተገኙት የአባል ሀገራቱ ተወካዮች መካከል የደቡብ ሱዳንና የጅቡቲ ልዑክ አባላት ዘላቂ የቱሪዝም ፍኖተ ካርታው ለቀጣናው ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት መልካም ዕድል ይዞ የሚመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
በቱሪዝም ዘርፍ በስፋት እየሠራች ካለችው ኢትዮጵያ ጋር ሁለንተናዊ ትብብር በማድረግ ለጋራ ተጠቃሚነት በቁርጠኝነት የሚሠሩ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በደቡብ ሱዳን የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ጉዳዮች ሚኒስቴር የንግድና ኢንቨስትመንት ተቆጣጣሪ ኒጎር ጆሴፍ አኮክ፤ የቱሪዝም ፍኖተ ካርታው ለቀጣናው ሀገራት የቱሪዝም እምርታ መልካም አጋጣሚ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ደቡብ ሱዳን በዘርፉ ልማትና ተጠቃሚነት ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ይበልጥ ተቀራርባና ተባብራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኗንም ገልጸዋል።
በጅቡቲ የአስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት መሐመድ ጋላብ፤ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ተመጋጋቢ የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማት ለጋራ ተጠቃሚነት የጀመረው ጥረት ጥሩ ጅምር መሆኑን ገልጸዋል።
በዘርፉ ልማትና የጋራ ተጠቃሚነት የኢትዮጵያን የልማት ጥረቶች አድንቀው በዚህ ረገድ አብሮነትና ትብብራችን ይቀጥላል ብለዋል።
የቀጣናው ሀገራት እምቅ የቱሪዝም ሃብታቸውን በጋራ አልምቶ ለመጠቀም የጀመሩት ጥረትም ትልቅ ተስፋ የሰነቀ መሆኑን ተናግረዋል። የሁለቱም ሀገራት ተወካዮች የኢትዮጵያን የቱሪዝም ልማት ጥረት በማድነቅ በትብብር ለመሥራት ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በቱሪዝም ዘርፍ በተለይም በፓርኮች ልማት በትብብር መሥራት የሚችሉባቸው ዕምቅ አቅም እንዳላቸው ኒጎር ጆሴፍ ገልጸዋል።
በጅቡቲ የአስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት መሃመድ ጋላብ በየብስ፣ በባቡር እና በአየር ትራንስፖርትና በቱሪዝም ልማት ኢትዮጵያና ጅቡቲ በጋራ ቢሠሩ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል። ይህም ጎብኚዎች ሁለቱንም ሀገራት ለመጎብኘት ምቹ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በተለያዩ ችግሮች እየተፈተነ ቢሆንም በእምቅ የተፈጥሮ ሃብት፣ ባሕላዊና ታሪካዊ ፀጋዎች የታደለ መሆኑ ይታወቃል።
በመሆኑም በቀጣናው ያለውን እምቅ ሃብት በጋራ አልምቶ ለመጠቀም የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን /ኢጋድ/ አባል ሀገራትን ማዕከል ያደረገ የ10 ዓመታት የዘላቂ ቱሪዝም ፍኖተ ካርታ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2017 ዓ.ም