አዲስ አበባ፡- በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገባውን የቢራ ገብስ ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የቢራ ገብስን በዘመናዊ ግብይት ሥርዓቱ ለማገበያየት እየሠራ መሆኑን አስታወቀ፤ በተጨማሪም ተቋሙ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ባቄላ፣ ኑግና ሽምብራን እንደሚያገበያይ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የስትራቴጂ መምሪያ ኃላፊ የሆኑት አቶ ባየልኝ ዘርዓይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ መንግሥት ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሲገቡ የነበሩትን የኢንዱስትሪ ግብቶችን በሀገር ውስጥ ግብዓት ለመተካት ግልጽ የፖሊሲ አቅጣጫ አስቀምጦ እየሠራ ነው። ለዚህም በዓመት እስከ 283 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ሊያስወጣ የሚችልን የቢራ ገብስ በሀገር ውስጥ አምርቶ በመተካት የውጭ ምንዛሪ ማደጉ አንዱ ማሳያ ነው።
የነፍስ ወከፍ የቢራ እና ተዛማጅ ምርቶች ፍላጎት ማደጉን ተከትሎ የቢራ እና የብቅል ፋብሪካዎች በፍጥነት እየተስፋፉ በመሆኑ ከቢራ ገብስ ፍላጎት ዕድገት ጋር አብሮ የሚሄድ የግብይት አማራጭ እንደሚያስፈልግ በጥናት መለየቱን የገለጹት ኃላፊው፤ አሁን እየተሠራበት ካለው የቢራ ገብስ የውል እና ኢንቨስትመንት እርሻ ትስስር በተጨማሪ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የቢራ ገብስን በዘመናዊ ግብይት በማገበያየት በቢራ ገብስ የእሴት ሠንሠለት እየተስተዋሉ ካሉ ተግዳሮቶች መካከል በግብይት ረገድ ያለውን ማነቆ ለማቃለል እየሠራ እንደሆነ አስረድተዋል።
አቶ ባየልኝ እንደሚሉት፤ የቢራ ገብስ ወደ ዘመናዊ ግብይት ሲገባ የምርቱ ዋጋ በፍላጎት እና አቅርቦት እንዲወሰን፤ ግብይቱ የምርት ጥራትን መሠረት አድርጎ እንዲከናወን፤ የቢራ ገብስ አምራች አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል። በተጨማሪም አርሶደሮች ለምርት ጥራት እና ምርታማነት ትኩረት እንዲሰጡ ያግዛል። በተመሳሳይ የብቅል እና ቢራ ፋብሪካዎች አስተማማኝ የግብዓት አቅርቦት እንዲኖራቸውም የመፍትሔ አቅም ይሆናል።
የቢራ ገብስ የግብይት ኮንትራትን በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በአማራጭነት ለማገበያየት የግብይት ኮንትራት በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መፅደቁን በመግለጽ፤ በቅርቡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የቢራ ገብስን ማገበያየት እንደሚጀምር ጠቁመዋል።
ከ25 ሺህ በላይ ደንበኞች ያሉት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ2017 ዓ.ም ከቢራ ገብስ በተጨማሪ ለውጭ ገበያ የሚያቀርባቸው ሰብሎች እንዳሉ የጠቆሙት አቶ ባየልኝ፤ ባቄላ፣ ሽምብራ እና ኑግ ምርቶችን የሚያገበያይ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት 16 ዓመታት ቡናን ጨምሮ ከ24 የሚበልጡ የጥራጥሬ፣ የቅባት እና የቅመማቅመም ሰብሎች ግብይት እየተፈጸመባቸው እንደሆነ የሚያነሱት ኃላፊው፤ ከነዚህ ውስጥም በዓመት ከ30 ሚሊዮን በላይ የጥራጥሬ እና ከስምንት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የቅባት ሰብሎችን የምታመርተው ሀገር ወደ ውጭ የትልከው የጥራጥሬ እና የቅባት ሰብሎች ድርሻ ከ25 በመቶ እንደማይበልጥ አመላክተዋል።
ባቄላ፣ ሽምብራ እና ኑግ ወደ ዘመናዊ ግብይት እንዲገቡ የማድረጉ ሥራም ይህንን ችግር መፍታትና የምርት አቅርቦት ፍሰቱን ከማሻሻል ጋር የተያያዘ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ በዚህ መልኩ ማሳደግ እንደምትችልም አብራርተዋል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም