አዲስ አበባ፡- በመጪዎቹ 10 ቀናት በአንዳንድ ስፍራዎች የሚዘንበው ዝናብ የደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ኢንስቲትዩቱ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በላከው መግለጫ፤ በመጪው አስር ቀናት በአብዛኛው በምዕራብ አጋማሽና በመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡ ይህም ለግብርናው እንቅስቃሴ አዎንታዊ ሚና የሚፈጥር ምቹ የእርጥበት ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
ሆኖም በአንዳንድ ስፍራዎች ላይ አልፎ አልፎ ከባድ ዝናብ ሊኖር ስለሚችል የሚጠበቀው እርጥበት በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አስቀድሞ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡
የሚኖረው እርጥበት ቀደም ብለው ለተዘሩና ፍሬ በማፍራት ላይ ለሚገኙ፣ እንዲሁም ዘግይተው ተዘርተው በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ላሉ ሰብሎች፣ ለቋሚ ተክሎች እንዲሁም ለፍራፍሬ ተክሎችና ለጓሮ አትክልቶች የውሃ ፍላጎትን ለማሟላት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ ጠቅሷል፡፡
የእርጥበት ሁኔታው በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሚስፋፋ በመሆኑ ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ገልጾ፤ በባሮ አኮቦ፣ ዓባይ፣ ኦሞ ጊቤ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ የላይኛው እና የመካከለኛው አዋሽ፣ ዋቤ ሸበሌ እና የገናሌ ዳዋ ተፋሰሶች ላይ እስከ ከፍተኛ የእርጥበት መጠን ያገኛሉ፡፡ ይህ ሁኔታ የከርሰ ምድር እና የገፀ ምድር የውሃ ሀብትን ከማጎልበት አንጻር የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተመላክቷል፡፡
በአንጻሩ ግን ባለፉት የክረምት ወራት ከተገኘው ከፍተኛ መጠን ያለው እርጥበት ጋር ተያይዞ አሁናዊ የውሃ መጠናቸው በጣም በጨመረባቸው እንደ ተንዳሆ፣ ከሰም፣ ቆቃ፣ ርብ፣ ጣና በለስ እና ፊንጫ ግድቦች በሚገኙባቸው የታችኛው የተፋሰስ ክፍሎች ላይ ከመጠን በላይ የግድብ መሙላት እንዳያስከትል የቅርብ ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግም ኢንስቲትዩቱ አስጠንቅቋል፡፡
በሌላ በኩል መስከረም የክረምት የመጨረሻ ወር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚገኘውን እርጥበት በመጪው የበጋ ደረቅ ወራት ጥቅም ላይ ለማዋል በሚያስችል አግባብ መሰብሰብና ማከማቸት ያስፈልጋል ሲል መግለጫው አመልክቷል፡፡
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም