አዲስ አበባ:- በአዲስ አበባ የመስቀል ደመራ በዓል ሃይማኖታዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን የመዲናዋ የሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዘንድሮውን የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ዝግጅትን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር ውይይት አድርጓል።
የአዲስ አበባ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ የመስቀል ደመራ በዓል ሃይማኖታዊ ትውፊቱንና ሠላምን በሚገልፅ መልኩ እንዲከበር ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።
የመስቀል ደመራ በዓል በሠላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁንም አመልክተዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው በዓሉ በሠላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ፖሊስ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል።
በዓሉ በሠላም እንዲከበር ፖሊስ በአዲስ አበባ ካሉ አድባራት ጋር በቅርበት እንደሚሠራም አመልክተዋል።
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ የባሕር ዳር እና ሰሜን ጎጃም አሕጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም በዓሉ ፍጹም ደማቅና ሠላማዊ ሆኖ እንዲከበር የከተማ አስተዳደሩ እያደረገ ላለው ሥራ ምስጋና አቅርበዋል።
የደመራ በዓል በታቀደው መንገድ ሠላምንና አንድነትን በሚገልፅ መልኩ ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ምዕመኑ ከፀጥታ አካላት ጋር በትብብር እንዲሠራ ጥሪ ማቅረባቸውን ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም