ከሻይ ቅጠል ምርት ከሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

አዲስ አበባ፡- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከአንድ ሺህ 142 ቶን በላይ የሻይ ቅጠል ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳሬክተር ሣሕለማሪያም ገብረመድኅን፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከተላከ የሻይ ቅጠል ምርት ሁለት ነጥብ 30 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፤ ከ2015 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ሲነጻጸር ከ292 ቶን በላይ ብልጫ አለው፤ በገቢም ሲነፃፀር 0 ነጥብ 33 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እድገት አሳይቷል ብለዋል፡፡

ለውጭ ገበያ የተላከው የሻይ ቅጠል ምርት ከ2015 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር የ50 ሺህ ቶን ብልጫ ቢኖረውም ሀገሪቱ ካላት አቅም አንጻር ብዙ መሥራት የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀደሙ ዓመታት በሀገሪቱ ተጠቃሽ የሆኑት የውሽውሽና ጉመሮ የሻይ ቅጠል ምርት በአምስት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ብቻ ያረፈ ነበር፤ የሚገኘውም የውጭ ምንዛሪ በዓመት ከሦስት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚበልጥ አልነበረም፤ ከሻይ ቅጠል ምርት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው፤ እየተሠራ ባለውም ሥራ በ2016 ዓ.ም 460 ሚሊዮን ችግኝ በማብዛት 30 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የማልማት ሥራ ተሠርቷል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በሻይ ቅጠል ልማት ላይ ባለሀብቶች በስፋት እየተሳተፉ አይደለም፤ ይህም ሀገሪቱም ማግኘት ያለባትን የውጪ ምንዛሪ እንዳታገኝ እንቅፋት ሆኖባታል ያሉት አቶ ሣሕለማሪያም፤ በዘርፉ ባለሀብቶች በስፋት ተሳትፈው ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ምንዛሪ እንድታገኝ መንግሥት በዘርፉ ለሚሳተፉ ባለሃብቶች የተለያዩ ማበረታቻዎች እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

የሻይ ቅጠል ምርት አሲዳማና ተዳፋት በሆኑ መሬቶች ላይ መብቀል የሚችልና ምርት የሚሰጥ በመሆኑ ምርታማነቱን ለማስፋት እየተሠራ ነው፤ የሻይ ቅጠል ምርትን ለማስፋት ከአርሶ አደሮች በተጨማሪ ባለሀብቶች በስፋት ሊሳተፉ ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

የሻይ ቅጠል ምርት አንድ ጊዜ ከተተከለ ለ30 እና 40 ዓመታት ምርቱ የሚቆይና በየ15 ቀኑ ምርቱን በመቅጠፍ ገቢ ማግኘት የሚያስችል ነው ያሉት አቶ ሣሕለማርያም፤ ዘርፉ አትራፊ በመሆኑ ባለሀብቶች በስፋት ሊሳተፉ ይገባል ብለዋል፡፡

የሻይ ቅጠል ምርት ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት ባለፈ ለበርካታ ሥራ አጥ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ በሁሉም ክልሎች ለማልማት እየተሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You