ለትውልድ የሚተባበሩ ክንዶች

ዜና ሐተታ

ነገ ዛሬ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በመሆኑም ነገን የተሻለ ለማድረግ ዛሬ መሥራት የግድ ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ የሁሉም ናት፤ በተለይ የወጣቱ፡፡

ወጣቱ ትውልድ ዛሬ ላይ ሀገሩን ለመለወጥ የሚያስችል በቂ አቅም አለው፡፡ በከንቱ የባከነ የወጣትነት ዘመን ለነገ ከቁጭት የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ለዚህ ደግሞ ለትውልድ ግንባታ ትኩረት መስጠትና በኃላፊነት ስሜት መሥራት ተገቢ መሆኑን ለኢፕድ አስተያየታቸውን የሰጡ ምሑራን ይናገራሉ፡፡

የጋብቻና የቤተሰብ አማካሪ ፓስተር ቸርነት በላይ (ፓስተር ቸሬ) ሀገር ተረካቢ ብቁና ንቁ ዜጋ ለመፍጠር በመጀመሪያ ቤተሰብን መገንባት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

የሰው ልጅ መሠረቱ ቤተሰብ በመሆኑ ወላጆችም ለልጆቻቸው መንገድ ማሳየትና መምራት ይኖርባቸዋል የሚሉት ፓስተር ቸሬ፤ ወጣቱ ትውልድ ለሀገሩ ቀናዒነት አስተሳሰብ እንዲኖረው ማድረግ ከተፈለገ መጀመሪያ ሕጻናት ላይ መሥራት የግድ ይላል ባይ ናቸው፡፡

ሳይታረስ የሚያበቅል መሬት ሳይዘራም የሚያጭድ ገበሬ ባለመኖሩ ልጅነት አምክኖ ወጣትነት ላይ ፍሬ መጠበቅ ሞኝነት እንደሆነ ይመክራሉ፡፡

ቤተ እምነቶች፣ የትምህርት ተቋማት፣ የመገናኛ ብዙኃን እንዲሁም የተዛባውን ነገር የሚያርቁ የተለያዩ ምሑራን በጋራ በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ትምህርት መስጠት ሲችሉ ለሀገሩ ቀናዒ ትውልድ መፍጠር እንደሚቻል ያመላክታሉ፡፡

አለበለዚያ ወጣቱ ትውልድ እየተባለ የሚሠራው ነገርም ትክክለኛ አስተሳሰብ አይደለም፤ ትክክለኛ ሀገር ተረካቢና ብቁ ዜጋ ለማፍራትም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ልጅነት ላይ መሥራት አስፈላጊ ነው፡፡

“ልጅነት ላይ ያልተዘራ ዘር በወጣትነት ወቅት ሊገኝ አይችልም፤ ወጣትነት ላይ ያልተዘራም ሽምግልና ላይ ሊገኝ አይችልም”፤ የሚሉት ፓስተሩ፤ ልጆችን መሥራት ማለት ዛሬና ነገን በድምሩ እንደመሥራት እንደሆነ ያክላሉ፡፡

“ከዚህ በፊት የነበሩ የሃይማኖት አባቶች በሚገባ ሠርተዋል፤ ነገር ግን አሁን ላይ የቤተ እምነቶች ቁጥር ከማብዛት ውጪ በትውልድ ላይ ብዙም እየተሠራ አይደለም” የሚሉት ፓስተር ቸሬ፤ የርስ በርስ ግድያ፣ መፈናቀል፣ ከባሕል ከእምነት፣ ከወግና ልማድ፣ ያፈነገጡ እኩይ ድርጊቶች መበራከት ጥላቻና ጸያፍ ቃላት ለዚህ ማሳያዎች ናቸው ይላሉ፡፡

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በበኩላቸው ብቁና ንቁ እንዲሁም ለሀገሩ ቀናዒ የሆነ ዜጋ ለመፍጠር ብሎም ነገን የተሻለ ለማድረግ በተለይ ትምህርት ቤቶች ላይ ሰፋፊ ሥራዎች መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ማለት ትምህርት ቤት ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉ ዜጋ ቀዳሚ ኃላፊነት መሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡

ከአኗኗር ለውጥ ጋር ተያይዞ በቤተሰብ፣ በአካባቢ እንዲሁም በሀገር ሽማግሌዎች ለአዲሱ ትውልድ የሚሰጥ የነበረው ምክር ቀንሷል የሚሉት ልጅ ዳንኤል፤ ይህንን የተካው ትምህርት ቤት በመሆኑ ትምህርት ቤት ላይ ትኩረት ያደረገ ሥራ መሥራት አለበት፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም አሁን ላይ ዓለም በቴክኖሎጂው በፍጥነት እየተቀየረች ያለችበት ሰዓት ስለሆነ በቴክኖሎጂው ዘርፉ እንዲበቁ ማድረግና በተለይ ወደ ፈጠራውና ኢኖቬሽን ዘርፍ ላይ በሰፊው እንዲሳተፉ መድረግም ተገቢ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡

እንደ ልጅ ዳንኤል ገለጻ፤ ኅብረተሰቡም የቀድሞ መልካም ልማዱን በማነቃነቅ አዲሱን ትውልድ መገሰጽና መምከር አለበት፡፡ በተጨማሪም በየዘርፉ የሚገኙ ባለድርሻ አካላትም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለባቸው፡፡

የአርበኞችን የድል ታሪክና የአባቶችን ተጋድሎ እንዲሁም ለሀገር ዕድገትና አንድነት የሠሩትን በርካታ ሥራዎች የአሁኑ ትውልድ በሥራ፣ በትምህርት፣ የሀገርን አንድነትን እና ሉዓላዊነትን በማስጠበቅ እንዲሁም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች መድገም እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ደረጃ እንድትደርስ ጀግኖች አርበኞች ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለውባታል፤ ይህን ትውልድ በተገቢው መንገድ መገንዘብ እንዲችል መሥራት እንዳለበትም ምክረ ሃሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You