እያንዳንዱ ሰው የዘር፣ የቀለም፣ የፆታ፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት ፣የፖለቲካ ወይም አስተሳሰብ ልዩነቶች ሳይለይ ለሁሉም የተሰጠው እኩል መብት እና ግዴታ አለው፡፡
በመሆኑም ያለአንዳች ልዩነት በነፃነትና በሠላም የመኖር፣ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ እንዲሁም የትምህርት፣ የሕክምና እና የመሳሰሉት አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳለው ሁሉ የሕግ የበላይነትን ወይም ሕገመንግሥቱን የማክበር፣ ግብር በአግባቡ የመክፈል እና ያሉ ልዩነቶችን የማክበር ግዴታ አለበት፡፡
መብት እና ግዴታ የማይነጣጠሉ ነገሮች ሲሆኑ ግዴታውን ሳይወጣ ለመብት መከራከር ተገቢ አይደለም፡፡ ታዲያ ሰዎች መብትና ግዴታቸውን ምን ያህል ይገነዘባሉ፤ ምን ያህሉንስ ይጠቀሙበታል ሲል ኢፕድ የሕግ ባለሙያዎችን አነጋግሯል፡፡
በተፈጥሮ የሚገኝ መሠረታዊ የሆኑ የሰብዓዊ መብቶች እና በሕግ እውቅና የሚሰጣቸው መብት እና ግዴታዎች አሉ ያሉት የሕግ ባለሙያው አቶ ደበበ ኃይለገብርኤል ናቸው፡፡
አቶ ደበበ እንደገለጹት፤ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ስለሰብዓዊ መብት ይናገራል፤ እውቅና ይሰጣል፡፡ ይህም ዜጎች ሀሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ፣ የፈለጉትን እምነት የመከተል፣ የመሰብሰብና ሠላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት እንዳላቸው በሕግጋት እውቅና እና ጥበቃ ይደረግላቸዋል ፡፡
እነዚህ ለእያንዳንዱ ዜጋ በእኩልነት የተሰጡ መብቶችም በባሕሪያቸው ልቅ አይሆኑም ያሉት አቶ ደበበ፤ የሌላውን መብት ለመጠበቅ ሲባል በመብቶች ላይ የሚጣሉ ገደቦች እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡
ለምሳሌም ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ምንም እንኳን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት ቢሆንም መብቱ ሊከበርና ሊጠበቅ የሚችለው በሌላው ላይ ጉዳት እስካላደረሰ ብቻ ሲሆን መሆኑን አንስተው፤ ስለዚህም ሰዎች የሌሎችን መብት የማክበር ግዴታ ይኖርባቸዋል ይላሉ፡፡
በመሆኑም ዜጎች ላይ በዋነኝነት የሚወድቀው ግዴታ የሚሆነው የራሳቸውን መብት በሚጠቀሙበት ወቅት በተመሳሳይ የሌላውን መብት የማክበር ግዴታ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ከዜጎች በተጨማሪም መንግሥት ሦስት ዋና ዋና ግዴታዎች አሉበት፡፡ ከእነዚህም ሕግ በማውጣትና ተቋማትን በመመሥረት መብትን የመጠበቅ ግዴታ እና ለወጡት መብትና ግዴታዎች እውቅና የመስጠት ኃላፊነት እንዳለበት ይጠቅሳሉ፡፡
እንዲሁም በባሕሪያቸው መንግሥት እንዲያሟላቸው የሚጠበቁ ለዜጎች እንደመኖሪያ ቤት እና የመሠረተ ልማት ማሟላት መብቶችን አቅሙ በፈቀደ መጠን እንዲያሟላ መንግሥት ይጠበቅበታል፡፡
በኢትዮጵያ እስካሁን ከ1400 በላይ አዋጆች ያሉ ሲሆን ዜጎችም ሆነ ስለአዋጁ የሚመለከታቸው አካላት በአዋጁ ላይ ስለሰፈረው መብት እና ግዴታ ያላቸው ግንዛቤ አናሳ መሆኑን አቶ ደበበ ይናገራሉ፡፡
እንዲሁም የተሰጣቸው መብት ገደቡ የት ድረስ እንደሆነ እና የሚጠበቅባቸው ግዴታ መኖሩን እንኳን ካለመገንዘብ ሰዎች በየአካባቢው ለተለያዩ ግጭቶችና ችግሮች ሲዳረጉ ይስተዋላል፡፡
ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም ያሉት አቶ ደበበ፤ ለዚህም መንግሥት ላይ ከወደቁ ግዴታዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ዜጎች መብት እና ግዴታቸውን እንዲያውቁ የማድረግ ግዴታና ኃላፊነት መወጣት አለበት ብለዋል፡፡
በመሆኑም መንግሥት የሚያወጣቸውን ሕጎች ሕዝብ እንዲያቅ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በቂ ስላልሆነ በተለያዩ ቋንቋዎችና አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ እንዳለበት ጠቅሰዋል ፡፡
እንዲሁም መንግሥትን በማገዝ የሚሠሩ እንደ የሲቪል ማኅበራት፣ ሕግ ባለሙያዎች እና ሚዲያ አካላት ዜጎች መብታቸውን እንዲያውቁ የማስተማርና ግንዛቤ የመፍጠር ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል፡፡
ዜጎችም ስለተሰጣቸው መብትና ስለሚጠበቅባቸው ግዴታ በማንበብ እና ከሚመለከታቸው የሕግ አካላትን በመጠየቅ በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል፡፡
ሌላው የሕግ ባለሙያ አቶ ገመቺስ መኮንን በበኩላቸው፤ መብትና ግዴታ ሕግን መሠረት ባደረገ ሕገመንግሥትና ከሕገመንግስቱ በታች ተፈጻሚነት ያላቸው እንደአዋጅ፣ መመሪያና ደንብ የመሳሰሉት የራሳቸው የሕግ አወጣጥ ሥርዓት ባላቸው አካላት የሚቀመጡ ሰነዶች ናቸው ይላሉ፡፡
ሰነዶቹ የተወሰኑ ሰዎች ሀሳብ ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰቡ እሴትና ሀሳብ ነፀብራቅ ሲሆኑ ሥልጣን ባለው አካል እንደመብትም እንደግዴታም የተቀመጡ ነገሮች ናቸው፡፡
ለሰዎች ከተሰጡት ከሕግ የሚመነጭ ሕገመንግሥታዊና ከሰብዓዊ መብትና ግዴታዎች በተጨማሪም በግለሰቦች፣ በተቋምና በማኅበራት ስምምነትና ከውል ሊመነጩ እንደሚችልም ይገልጻሉ፡፡
አቶ ገመቺስ እንደገለጹትም፤ እያንዳንዱ ሰው በመብቶቹና በግዴታዎቹ አፈጻጸም ዙሪያ የማወቅ እኩል መብት አለው፡፡ መብቱ የተነካበት ሰው የውስጥ አሠራርና ደንቦች ከመጠቀም ጀምሮ የግልግል ሂደቶችን በመከተል መብቱን ሊያስጠብቅ ይችላል፡፡
በፍርድ ቤት ውስጥም የፍታሐ ብሔር ሥነሥርዓት ሕግ እና በወንጀል ሥነሥርዓት ሕግ በተደነገገ አካሄድ ላይ መብትና ግዴታን ማስጠበቅ የሚቻል መሆኑን አንስተው፤ ሁሉም ሰው ሕጉ ደህንነቱ እንዲጠበቅለት እኩል የሆነ መብት አለው፡፡
“አብዛኛው ማኅበረሰብ መብትና ግዴታን በተመለከተ ብዙም ግንዛቤ የለውም፤ በመተግበር ላይ ክፍተት አለ” ያሉት አቶ ገመቺስ፤ በመጀመሪያ ግዴታችንን ስንወጣ መብታችን መጠየቅ እንችላለን ይላሉ፡፡
በመሆኑም ሰዎች መብትና ግዴታዎችን በማንበብ፣ የሕግ ባለሙያዎችን በማማከር ማወቅ፤ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትም ውስጣዊ ሕጎችን ለሚመለከታቸው ሁሉ ማሳወቅ እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡
ማሕሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም