አዲስ አበባ፡- በሆሳዕና ከተማ የተጀመረው የ2 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ ከአንድ ወር በኋላ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡
የከተማው ከንቲባ አቶ ዳዊት ጡምደዶ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ከተማ አስተዳደሩ 200 ሚሊዮን ብር በመመደብ የ2 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ እያከናወነ ነው፡፡ ይህንን የኮሪደር ልማት ሥራም ከአንድ ወር በኋላ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል፡፡
እንደ አቶ ዳዊት ገለጻ፤ ከተማ አስተዳደሩ ሰባት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ሥራ ለማከናወን ዕቅድ ይዟል፡፡ ከዚህ ውስጥ በ200 ሚሊዮን ብር 2 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር እየተሠራ ይገኛል፡፡ ከዚህ ውስጥ ቀሪውን 4 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ስራ በ500 ሚሊዮን ብር ወጪ በቅርብ ጊዜ እንደሚጀመር ጠቁመዋል፡፡
ከአዲስ አበባና ከሌሎች ትላልቅ ከተሞች ልምድ በመውሰድ ሰፋፊ የከተማ ውበት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኮሪደር ልማት ሥራው አሁን ላይ የቴራዞ ንጣፍ ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡
የኮሪደር ሥራው የውሃ፣ የቴሌ ኬብል፣ የመብራት ዝርጋታ፣ የትራፊክ መብራትና የደህንነት ካሜራ ገጠማ፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የመንገድ ዳር አረንጓዴ ልማት፣ የጎርፍ መቀልበሻና ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ በከተማው የሚገኙ የመንገድ ዳርቻዎችን የማስዋብና ለእግረኞች ምቹ የማድረግ ዓላማ ያለው ነው ያሉት አቶ ዳዊት፤ ከኮሪደር ልማቱ ጋር የተገናኘ ሁለት ዘመናዊ መፀዳጃ ቤቶች ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ተጨማሪ አምስት መፀዳጃ ቤቶች እየተገነቡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
የመንገድ ዳርቻ አረንጓዴ ልማት ሥራና ሌሎች ግንባታዎች ለከተማዋ አዲስ ገጽታ የሚያጎናጽፍና ለነዋሪዎቿ ብሎም ለእንግዶቿ ምቹ እንዲሁም ተስማሚ የማረፊያ ሥፍራን ስለሚፈጥር በልዩ ትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ አቶ ዳዊት ተናግረዋል።
በተጨማሪ በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ በከተማው 102 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሁለገብ የሕዝብ መዝናኛ ፓርክ ግንባታ የመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራ መጀመሩን አመላክተዋል፡፡
እየተገነቡ ያሉ መሠረተ ልማቶች ለከተማው ውበት ከመስጠት ባሻገር ለብዙ ሰዎች ሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸው፤ የተጀመሩ ሥራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለኅብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች ሲጠናቀቁ ማኅበረሰቡ በባለቤትነት ስሜት ሊንከባከበውና ሊጠቀምበት እንደሚገባ አቶ ዳዊት አስረድተዋል፡፡
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም