አዲስ አበባ፡- ወጣቱ በልማት ሀገርን ወደፊት የማሻገር ትልሙን ለማሳካት በአመክንዮ መንቀሳቀስ እንዲሁም ከጦርነት ጎሳሚ ድርጊቶች እራሱን ሊያቅብ ይገባል ሲሉ የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ገለጹ።
የትግራይ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ወጣቱ በልማት ሀገር የማሻገር ትልሙን ለማሳካት በአመክንዮ መንቀሳቀስ ይኖርበታል።
ወጣቱ የነገዋን ሀገር መጻዒ ዕድል ለመወሰን በአመክኒዮ መንቀሳቀስ አለበት ያሉት ዶክተር አረጋዊ፤ ይህም ካለፉት ጊዜያት ተሞክሮዎችን በመውሰድ በሁሉም ዘርፎች እየተሳተፈ የሀገሪቱን ዕድገት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
ወጣቱ ዛሬ ላይ ያለው ድርሻ መወጣት የሚችለው ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ሲችል መሆኑን በመግለጽ፤ ጦርነት ሀገር ማረጋጋትም ሆነ ለችግሮች መፍትሄ መስጠት የማይችል በመሆኑ ከጨለምተኝነት እና ከመንጋ አስተሳሰብ በመውጣት የሃሳብ ልዕልናን ማጎልበት እንደሚገባ ተናግረዋል።
እንደ ዶክተር አረጋዊ ገለጻ፤ የእርስ በእርስ ጦርነት የሕዝብ እልቂት ከማስከተሉም በላይ የሀገርን ዳር ድንበር በማስደፈር ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ የሚጥል ነው። ወጣቱ ለጦርነት የሚቋምጡ እና ጦርነቱን ከፊት የሚመሩት አካላት የጦርነት ገፈት ቀማሽ ያለመሆናቸውን ቆም ብለው በማጤን በዚህም ገፈት ቀማሽ የሚሆነውን ሕዝብ መታደግ ይገባዋል።
ዶክተር አረጋዊ አክለውም፤ በሀገሪቱ ዘላዊ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት ማጎልበትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ተገቢውን ምላሽ መስጠት አለበት ብለዋል።
የሃሳብ ልዩነት በሰው ልጆች መካከል ሁሌም የማይጠፋ በመሆኑ የሃሳብ የበላይነት እንዲረጋገጥ ማድረግም ሌላው ለነገ የማይባል ርምጃ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
ይነስ ይብዛ እንጂ ሁሉም ዜጋ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ድርሻ አለው ያሉት ዶክተር አረጋዊ፤ ሽማግሌው የነበረው ተሞክሮ በማሳወቅ፤ ወጣቱም በሴረኞች ሃሳብ ሳይበገርና እኔ ብቻ ነኝ አዋቂ ከሚል አስተሳሰብ በመውጣት ተሞክሮ፣ ልምድ መውሰድ እንዲሁም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካልም ከፋፋይ የሆኑ ባህሎችና ታሪኮች በማጤን ተገቢውን መፍትሄ መስጠት እንዳለባቸው አመላክተዋል።
ወጣቱ በተለይ ሀገሪቷ ዓለም ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ለማድረስ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት ይበልጥ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅበት አብራርተዋል።
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም