የአጼ ፋሲል አብያተ መንግሥት ቅርስ ጥገና ጥንታዊነቱን በጠበቀ አግባብ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፡- የአጼ ፋሲል አብያተ መንግሥት ቅርስ የጥገና ሥራ ታሪካዊነቱንና ጥንታዊነቱን በጠበቀ አግባብ እየተከናወነ መሆኑን የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የባህልና ቱሪዝም ቢሮው የማኔጅመንት አባላት የቅርሱ የጥገና ሥራ ያለበትን ሁኔታ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ወቅት የቢሮ ኃላፊው አቶ መልካሙ ጸጋዬ፤ የቅርስ ጥገና ሥራው የጎንደር ከተማን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

መንግሥት ለቅርሱ ጥገናና ልማት ሥራ የሰጠው ልዩ ትኩረት የሕዝቡን ታሪክና ባህል ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ባለው ቁርጠኝነት እንደሆነ ገልጸዋል።

የአጼ ፋሲል አብያተ መንግሥት ቅርስ የጥገና ሥራ ታሪካዊነቱንና ጥንታዊነቱን በጠበቀ አግባብ እየተከናወነ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ጠቁመው፤ ሲጠናቀቅ ከተማዋን ተመራጭ የቱሪስት መናኸሪያ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት እየተካሄደ ያለው የቅርሱ ጥገና በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የጎንደር ከተማ ሕዝብ እያደረገ ያለው ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

የጥገና ሥራው በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለጎብኚዎች ክፍት እንዲሆንም የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን የቅርብ ድጋፍና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የፋሲል አብያተ መንግሥት ቅርስ የጥገና ሥራ ዓለም አቀፍ የቅርስ ጥገና መርሆዎችን የጠበቀ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በቢሮው የቅርስ ጥገናና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ጋሻዬ መለሰ ናቸው።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ዮናስ ይትባረክ በበኩላቸው፤ የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት የቅርስ ጥገና ሥራው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ በልዩ ትኩረት እየደገፉ ናቸው ብለዋል።

ጥገናው ለአደጋ ተጋልጦ የቆየውን የቅርሱ ህልውና እንዲመለስ ከማስቻሉም በላይ ለአካባቢው ወጣቶችም የሥራ እድል በመፍጠር በኩል ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የከተማ አስተዳደሩና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ አመራር አባላት የተገኙ ሲሆን፤ ስለ ቅርስ ጥገናው ሂደትም በቅርስ ጥገና ባለሙያዎች ገለፃና ማብራሪያ ተሠጥቷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You