-የነዳጅ እጥረት የተፈጠረበትን ምክንያት የማጣራት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ባለሥልጣኑ አስታውቋል
አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ በማደያዎች ላይ ቤንዚን እጥረት ምክንያት ለእንግልት መዳረጋቸውን የከተማዋ አሽከርካሪዎች ገለጹ። የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን በከተማው ሚስተዋለውን የነዳጅ እጥረት ምክንያት የማጣራት ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስታውቋል።
አሽከርካሪ አቶ ሚኪያስ ሰይፉ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በከተማው ከፍተኛ የነዳጅ ሰልፍ ይታያል። በርካታ አካባቢዎች የሚገኙ ማደያዎች ላይ ቤንዚን የለም እየተባለ ነው።
ከመርካቶ ተክለሃይማኖት አካባቢ ቤንዚን ለመቅዳት ከሁለት ሰዓታት በላይ በወረፋ ማሳለፋቸውን ገልጸው፤ ይህም በሥራቸው ላይ ተጽእኖ የፈጠረባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።
አሽከርካሪ ወይዘሮ መዓዛ አሰግድ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ በአብዛኛው አካባቢ በሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ቤንዚን እንደማይገኝ ማስተዋላቸውን ተናግረዋል። ቤንዚን በሚገኝባቸው የነዳጅ ማደያዎችም ረዥም ሰልፍ መኖሩን አንስተዋል።
በቀበና አካባቢ ከአመሻሹ አስራ አንድ ሰዓት የተሰለፉት ሰልፍ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ድረስ ጠብቀው እንደቀዱ በምሬት ተናግረዋል።
በነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የነዳጅ ውጤቶች ስርጭት እና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሞኜ ለኢፕድ በሰጡት ምላሽ በከተማው በነዳጅ ማደያዎች አካባቢ የመኪኖች ሰልፍና ቤንዚን የለም የሚል ምልክቶች የሚስተዋል መሆኑን አምነዋል።
የተከሰተው የቤንዚን እጥረት ምክንያት የማጣራት ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ለአዲስ አበባ ከተማ በተመደበ ኮታ መሠረት ለመዲናዋ በቀን እስከ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን ወይም ወደ 30 መኪና ቦቲ ቤንዚን ይገባላታል ያሉት ኃላፊው፤ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከጅቡቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ጋር በመነጋገር በከተማው በተለይም የቤንዚን አቅርቦት ለማሟላትና በየጊዜው እንዲስተካከል እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከጅቡቲ ወደ አዲስ አበባ እየገባ ያለው አቅርቦት ከፍላጎቱ ጋር የተቀራረበ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም በፊት የሚገባው የአዲስ አበባ ኮታ አሁንም ከጅቡቲ ነዳጅ አቅራቢ ጋር በመተባበር እየቀረበ ያለ ቢሆንም እንዲሁም በከተማው ከፍተኛ የቤንዚን ተጠቃሚ የሆኑት የባጃጅና ሞተር እንቅስቃሴ በተገደበበት ወቅት በማደያዎች የቤኒዚን እጥረት ለምን ተከሰተ የሚለውን ለማጣራትም ሥራ እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።
በቅርቡ ሕገወጥ እንቅስቃሴን በመቆጣጠር አዲስ አበባ ላይ 20 ሺህ ሊትር በላይ ቤንዚን ከከተማ ሊወጣ ሲል መያዙን አቶ ጌታቸው አስታውሰው፤ አሁንም ተመሳሳይ የክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎች እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ምንም እንኳን በከተማው የተመደበ የቤንዚን ኮታ በተመጣጣኝ ሁኔታ እየገባ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን የቤንዚን እጥረት ለመቀነስ ከሱሉልታ መጠባበቂያ ዲፖ 20 ቦቲ ቤንዚን በአዲስ አበባ ከተማ ሁሉም አካባቢዎች መከፋፈሉን ገልጸዋል።
ባለሥልጣኑም ከሚያደርገው የክትትልና የዳሰሳ ሥራ በተጨማሪ ነዳጅ የሚደብቁና በሕገወጦች ላይ ርምጃ የሚወስድ መሆኑን ጠቅሰው፤ ማደያዎች የገባላቸውን ነዳጅ በሥርዓት እንዲሸጡ አቶ ጌታቸው አሳስበዋል።
ማኅሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም