ዜና ትንታኔ
ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የአየር ንብረትና የከባቢ አየር ፖሊሲዎች ቀርጻ ወደ ሥራ ገብታለች። በተለይም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ቀርጻ ላለፉት ስድስት ዓመታት እየተገበረች ተገኛለች። በዚህ መርሃ ግብርም ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 2011 ዓ.ም ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ በ2015 ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል። በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ችግኝ ተከላ ከኢትዮጵያ አልፎ ጎረቤት ሀገራትም እየተሳተፉ ነው።
መርሃግብሩ ከኢትዮጵያውያን አልፎ የዓለምን ቀልብ መግዛት ችሏል። በዚህም በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ አድናቆት ተችሮታል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን አረንጓዴ ዐሻራን ጨምሮ የአካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ኢኒሸዬቲቮች ላይ እየወሰደች ያለውን የአመራርነት ሚና ማድነቃቸው እንደ አንድ ማሳያ ሊወሰድ የሚችል ነው።
የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራሙ አረንጓዴ ዐሻራ የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቅርቡ ይፋ ያደረጉት የ 10 ዓመት ብዝሃ ሕይወት ዳግም ወደ ሕልውናው የመመለስ እቅድ ጋር ለማጣጣምና ለማስተሳሰር ፍላጎት እንዳለውም ገልጸዋል።
የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ ዋና ፀሐፊ ሳይመን ስቲል በበኩላቸው ኢትዮጵያ እየተገበረቻቸው ያሉ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ እቅዶች በመተግበር እያሳየች ያለው ቁርጠኝነት ከፍተኛ ነው።
ኢትዮጵያ ለእቅዶቹ ተፈጻሚነት የሚያስፈልጋትን ሀብት ለማፈላለግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸው፤ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሠሩም ጠቅሰዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ ተቋማትን ጨምሮ አጋር አካላት የሚያደርጉት ድጋፍ የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ለውጥና ከባቢ አየር ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውጤታማ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሯ አመላክተዋል።
10ኛውን የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ልዩ ጉባዔ አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡት በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የአካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ስምምነትና ስትራቴጂክ አጋርነት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንሱር ደሴ እንዳሉት፤ በጉባዔው ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥና በአካባቢ ጉዳዮች እያከናወነቻቸው ያሉ ተጨባጭ ተግባራትን ለአፍሪካ አባል ሀገራትና ሌሎች ለስብሰባው ተሳታፊዎች አጋርታለች። በውጤቱም በርካቶች የኢትዮጵያን ተግባር አድንቀው ከሀገራችን ጋር አብሮ በትብብር ለመሥራት ፍላጎታቸውን አሳይተዋል ብለዋል።
ከተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ሚስ ኢንገር አንደርሰን ጋር በተደረገ ውይይት በኩል ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችውን የአረንጓዴ ዐሻራ በተባበሩት መንግሥታት የሥርዓተ ምህዳር ኢኒሼቲቭ ተካቶ እንዲያዝ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ይህን ተከትሎም በመጪው 16ኛው የተባበሩት መንግሥታት የብዝህ ሕይወት ጉባዔ የኢትዮጵያ ተሳትፎ የተጠናከረ እንደሚሆን ጠቅሰው፤ ለጉባዔው ውጤታማነት በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱንም ጨምረው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥና በአካባቢ ጉዳዮች እያከናወነቻቸው ያሉ ተጨባጭ ተግባራትን ከአፍሪካ አባል ሀገራትና በሌሎችም አጋር አካላት አድናቆት እየተቸረው መሆኑን አስታውሰው፤ ሀገራችን ጋር አብሮ በትብብር ለመሥራት ፍላጎት ማሳየታቸውንም አመላክተዋል።
እንደ ኃላፊዎቹ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥና በአካባቢ ጉዳዮች ላይ እየሠራችው ያለው ሥራ ለብዙ ሀገራት ምሳሌ መሆን የሚችል ነው። አረንጓዴ ዐሻራ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የምግብ ሥርዓትን ለመለወጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ ተቋማትን ጨምሮ አጋር አካላት የሚያደርጉት ድጋፍ የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ለውጥና ከባቢ አየር ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውጤታማ ለማድረግ ወሳኝ መሆናቸውም ተመላክቷል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም