የቱሪዝም ልማት ፍኖተ ካርታ – ለዘርፉ ዕድገት

ኢጋድና አባል ሀገራቱ ዘላቂ የቱሪዝም ልማትን እውን ለማድረግ ያዘጋጁት የ10 ዓመት ዘላቂ የቱሪዝም ማስተር ፕላን ሰሞኑን ይፋ ሆኗል። ማስተር ፕላኑ እ.ኤ.አ ከ2024 እስከ 2034 ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፤ የቀጣናው የቱሪስት ሀብቶች በዘላቂነት ለማልማት በርካታ ገጸበረከቶችን እንደሚያመጣ ታምኖበታል።

በኢጋድ አባል ሀገራት በርካታ የቱሪስት ሀብቶች ያሉ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ከማስተዋወቅ እና አልምቶ ከመጠቀም አንጻር ክፍተት መኖሩ ይነገራል። ታዲያ ይህንን ክፍተት በማረም የቀጣናውን ሀገራት ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ ማስተር ፕላኑ ምን ፋይዳ ይኖረው ይሆን?

የኢጋድ ዋና ጸሀፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ በኢጋድ አባል ሀገራት በሚፈጠሩ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት የቀጣናውን ባህል፣ ወግ፣ ዕሴት እና የተፈጥሮ ሀብቶችን በሚፈለገው ደረጃ መጠቀምና ማስተዋወቅ አልተቻለም።

በመሆኑም በአባል ሀገራቱ ያሉትን የቱሪዝም ሀብቶች በጋራ ለማልማትና ለመጠቀም እንዲሁም የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከር የ10 ዓመት ዘላቂ የቱሪዝም ማስተር ፕላን መዘጋጀቱን ይናገራሉ።

የተዘጋጀው የ10 ዓመት ማስተር ፕላን በአባል ሀገራቱ መካከል ነጻ የቪዛ ሥርዓት፣ የመረጃ ልውውጥ፣ መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት፣ የዘርፉን ተግዳሮት ለመፍታት፣ ወጥ የሆነ የቱሪዝም ፖሊሲና አሠራር እንዲኖሮ እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን እንደሚያስገኝ ያብራራሉ።

ዶክተር ወርቅነህ እንደሚሉት፣ የቱሪዝም ዘርፉ በሀገራት መካከል ያለውን የእርስ በእርስ ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ወሳኝ ነው። በመሆኑም የቀጣናውን ሰላምና ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ አባል ሀገራቱ የቱሪዝም ሀብታቸውን በትብብር በማልማት መጠቀም አለባቸው ሲሉ ይናገራሉ።

በምስራቅ አፍሪካ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰት አለመረጋጋትና የሰላም እጦት ለዘርፉ ችግር መሆኑን አንስተው፤ በቀጣናው ሀገራት ሰላምን በማስፈንና የተጠናከረ የመንገድ፣ የአየር፣ የባህር መሠረተ ልማትን በማስፋፋት ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ይገልጻሉ።

የቀጣናውን ሀገራት ሰላም በማስፈንና መሠረተ ልማትን በማስፋፋት ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን እያንዳንዳቸው አባል ሀገራት በቅንጅት መሥራትን ባህል ሊያደረጉ እንደሚገባ በአጽንኦት ይናገራሉ።

ቱሪዝም በኢጋድ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር፣ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ፤ ኢጋድ በቀጣናው የተጠናከረና የተሳለጠ የቱሪዝም መሠረተ ልማት እንዲኖር የተለያዩ አጋር አካላት በመሠረተ ልማት ግንባታው ኢንቨስት እንዲያደርጉ የማግባባት ሥራ እንደሚሠራ ነው የተናገሩት።

የኢጋድና አባል ሀገራቱ ዘላቂ የቱሪዝም ልማት ማስተር ፕላን የቀጣናውን ሀገራት በቱሪዝም ዘርፉ ተወዳዳሪ ለማድረግ ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በኃላፊነት እንዲሠሩ ጠይቀዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው፤ በቀጣናው ያሉት የቱሪስት ሀብቶች በአግባቡ ካለመልማታቸውና ካለመተዋወቃቸው ባለፈም በተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች፣ ነፃ ቪዛ እና የሠለጠነ የሰው ኃይል ባለመኖሩ በዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ መሆን አለመቻሉን ይናገራሉ።

የቀጣናው ሀገራት ዘርፉን በማልማትና በማስተዋወቅ ተጠቃሚ ለመሆን የ10 ዓመት ዘላቂ የቱሪዝም ማስተር ፕላን ያዘጋጁ ሲሆን፤ ለማስተር ፕላኑ ተግባራዊነት ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር በቅንጅትና በቁርጠኝነት ትሠራለች ሲሉ ተናግረዋል።

የቀጣናው ሀገራት ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን የቱሪዝም መሠረተ ልማትን በማስፋፋት፣ መዳረሻዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ለመሳብ በትብብር መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፉን ከአምስቱ የልማት ምሰሶዎች ውስጥ በማካተት እየሠራች መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችንና የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት የማልማት፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እና ሌሎች በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል።

በተሠሩት ሥራዎችም ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻነቷ እያደገ የመጣ ሲሆን፤ የቀጣናው ሀገራት ያላቸውን ተሞክሮ መጋራትና ድንበር ተሻጋሪ የቱሪዝም ልማት ላይ በትብብር መሥራት እንደሚጠይቅ ያስረዳሉ።

የኢጋድ አባል ሀገራት የቱሪዝም ሀብታቸውን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል በቀጣናው ተወዳዳሪና ዘላቂ የቱሪዝም ልማትን እውን ለማድረግ በትብብር መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ።

የቱሪዝም ልማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ዘርፍ ቢሆንም በአፍሪካ ግን ዝቅተኛ ነው የሚሉት አምባሳደር ናሲሴ፤ ገቢው ዝቅተኛ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት የመሠረተ ልማት አለመሟላትና የሰላም እጦት መሆኑን ያስረዳሉ።

በዘርፉ ጠንካራ የልማት ትስስር በመፍጠርና ሰላምን በማስጠበቅ ከቀጣናው እምቅ ሀብት ተጠቃሚ ለመሆን በጋራ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመው፤ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You