አዲስ አበባ፦ የ2017 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ መስከረም 25 ቀን በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ ፣ መስከረም 26 ቀን ደግሞ በቢሾፍቱ ሆራ ሃርሰዴ እንደሚከበር የኦሮሚያ ሕብረት አባገዳዎች አስታወቀ።
የመጫ አባገዳ እና የኦሮሚያ ሕብረት አባገዳዎች ሰብሳቢ አባገዳ ወርቅነህ ተሬሳ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የኦሮሞ ሕዝብ ከሚያከብራቸው የእርቅና የሰላም ክብረ በዓላት መካከል ኢሬቻ አንዱ ነው። በዓሉም ዘንድሮ መስከረም 25 ቀን በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ፣ መስከረም 26 ቀን ደግሞ በቢሾፍቱ ሆራ ሃርሰዴ ይከበራል፡፡
የ2017 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል መስከረም 25 ቀን በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ ፣ መስከረም 26 ቀን ደግሞ በቢሾፍቱ ሆራ ሃርሰዴ እንደሚከበር አመልክተው፤ በዓሉን ለመታደም የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የባህል ልብሳቸውን በመልበስ በዓሉን በፍቅር፣ በአንድነትና በሰላም ማክበር እንደሚገባ ተናግረዋል።
የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል በሆራ ፊንፊኔና በሆራ ሀርሰዴ በልዩ ሁኔታ ደምቆ እንዲከበር በርካታ የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ያሉት አባገዳ ወርቅነህ፤ በዚህም ለኢሬቻ በዓል አስተባባሪ ወጣቶች የስምሪት አቅጣጫ መስጠት እንዲሁም ከአባ ገዳዎች ጋር በመሆን ስለ ኢሬቻ በዓል ምንነትና እሴት ግንዛቤ መስጠት ይገኙበታል ብለዋል።
ከአባ ገዳዎች፣ ከሀደ ስንቄዎች፣ ከመንግሥት እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በዓሉ በሰላም፣ በፍቅር እና በደስታ እንዲከበር ለማድረግ ውይይት መከናወኑን ጠቁመው፤ በዓሉን ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር በመሆን እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህም ባለፈ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በዓሉን እንዲያከብሩ ጥሪ የተደረገ መሆኑን የገለጹት አባገዳ ወርቅነህ፤ ከቢሾፍቱና ከፊንፊኔ ከሚከበረው በተጨማሪ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እንደሚከናወን ተናግረዋል።
ቄሮዎች፣ ቀሬዎችና ፎሌዎች የበዓሉ ባለቤት መሆናቸውን በመግለፅ፤ ኢሬቻ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ማስቻል እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ሆረ ፊንፊኔና ሆራ ሀርሰዴ ጨምሮ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በሚከናወነው የኢሬቻ በአል ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በዓሉን ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
ሀደስንቄ ቱለማ ዘውዲቱ በበኩላቸው፤ የኢሬቻ በዓል የሰላም በዓል በመሆኑ የኦሮሞን ባህልና ሥርዓት በተከተለ መልኩ መከበር እንዳለበት ገልጸው ፤በዓሉ ባህልና እሴትን ተከትሎ እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የዘንድሮው ኢሬቻ በዓል የገዳ ሥርዓት እሴቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ሀደስንቄ ቱለማ፤ በዓሉ ያለምንም እንከን እንዲከበር ሁሉም በጋራ መቆም አለበት። በተለይም ወጣቱ ሚናውን በአግባቡ መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።
ከዚህም ውስጥ አንዱ በዓሉ የሚከበርበትን ቦታ የመጎብኘትና ጽዱ የማድረግ ሥራዎችን ተጠቃሽ መሆኑን ነው የተናገሩት ሀደስንቄ ቱለማ ዘውዲቱ።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም