እሥራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ ቀጥላለች

– የእሥራኤል የሕክምና ልዑክ ለልብ ሕሙማን ሕክምና እየሰጠ ነው

አዲስ አበባ፡- የእሥራኤል መንግሥት በሕክምናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ። የእሥራኤል የሕክምና ልዑክ ቡድን በኢትዮጵያ ለሚገኙ 200 የልብ ሕሙማን በትናንትናው እለት ሕክምና መስጠት ጀምሯል።

በኢትዮጵያ የእሥራኤል ምክትል አምባሳደር ቶመር ባርላቪ በወቅቱ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፤ እሥራኤልና ኢትዮጵያ በሕክምናው ዘርፍ መልካምና ለረጅም ጊዜ የቆየ ግንኙነት አላቸው። በአሁኑ ጊዜም ከተለያዩ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ጋር በመሆን በአዲስ አበባ እንዲሁም በሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች ሕክምና ለመስጠት የሕክምና ልዑክ አስገብቷል ብለዋል።

የሕክምና ልዑክ ቡድኑ በልብ ሕመም ለሚሰቃዩ ሕጻናት ብቻ ሳይሆን በአራት የሕክምና ዘርፍ ሕክምና እንደሚሰጥ ገልፀው፤ በቀጣይም የእሥራኤል መንግሥት በሕክምናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።

እሥራኤል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እያለፈች እንደምትገኝ የገለጹት ምክትል አምባሳደሩ ሆኖም እሥራኤል የዜጎቿን ደኅንነት ከመጠበቅ ጎን ለጎን እነዚህን የመሰሉ ንቅናቄዎች ላይ የመሳተፉን ሥራ አጠናክራ እየቀጠለች ሲሆን ይህ ንቅናቄም በኢትዮጵያና በእሥራኤል መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ጠቁመዋል።

የሴቭ ዘ ቺልድረን ተወካይ ሪኪ ሮዘንቤል በበኩላቸው፤ ግብረሠናይ ድርጅቱ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት ለ200 ከፍተኛ የልብ ችግር ላለባቸው ሕጻናት ሕክምና ለመስጠት አቅዷል ብለዋል።

የሕክምና ልዑክ ቡድኑ በትናትናው እለት የሕክምና ሥራውን መጀመሩን ገልጸው እስካሁንም 50 የልብ ችግር ያለባቸውን ሕጻናት መለየት መቻሉን ተናግረዋል።

የሕክምና ልዑክ ቡድኑ 200 ከፍተኛ የልብ ችግር ያለባቸው ሕጻናትን ለይቶ ሕክምና ካደረጉ በኋላ ብዙዎቹን ወደ እሥራኤል ሃገር ወስዶ ለማከም እቅድ እንዳለው የገለጹት ተወካዩዋ አምስት የቀዶ ሕክምና ማሽን ይዘው መግባታቸውን ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አንዱዓለም ደነቀ፤ በኢትዮጵያና እሥራኤል መካከል በሕክምናው ዘርፍ የቆየ ወዳጅነትና ትብብር እንዳለ ገልጸው በተለይም የእሥራኤል መንግሥት ላለፉት ዓመታት የልብ ታማሚዎችን ወደ እሥራኤል ሀገር በመውሰድ እንዲሁም በሀገር ውስጥ በማከም ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ የሕክምና ልዑክ ቡድኑ የልብ ሕክምናን እንዲሁም ሌሎች ሕክምናዎችን ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ለብዙ ታማሚዎች እፎይታ የሚሆን ነው። በቀጣይም ከውጪ የሚመጡ ድጋፎች እንዲጠናከሩ በመሥራት ለታካሚዎች የተሻለ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You