ኢትዮጵያን የማዳከም ስትራቴጂ እስከምን?

ግብፅ በቅርቡ ከሱማሌ እና ከኤርትራ ጋር ያደረገቻቸው ተደጋጋሚ ግንኙነቶች ኢትዮጵያን አጀንዳ ያደረጉ ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ ተግባርም ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገራት የመነጠል ዲፕሎማሲ እየተከተለች ስለመሆኑ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

ለመሆኑ ግብፅ በአፍሪካ ቀንድ ባለው ውስብስብ ጂኦፖለቲካዊ ትግል ውስጥ ጠንካራ ኢትዮጵያ እንዳትፈጠር ስትራቴጂካዊ ርምጃዎችን አስፋፍታ የመቀጠሏ ዓለማቀፋዊ አንድምታው ምንድነው? ዓለም አቀፉ የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ሙሳ ሸኮ ግብፅ በታሪክ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ መረጋጋት እና የኢኮኖሚ እድገት ለመናድ ያላሰለሰ ጥረት ማድረጓንና ይህ ስልት ኢትዮጵያ የዓባይን ውሃ እንዳትጠቀምና ጠንካራ ቀጣናዊ የበላይነት እንዳይኖራት ከመፍራት የመጣ መሆኑን ይናገራሉ።

ከታሪክ አኳያ ግብፅ ቢያንስ ለግማሽ ምዕተ ዓመት በኢትዮጵያ ውስጣዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ መግባቷን በማንሳት፤ ለዚህ በአብዛኛው የምትሰጠው ሰበብ ደግሞ የዓባይ ወንዝን ከመቆጣጠር ስጋት ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ።

ግብፅ የዓባይ ግድብ ግንባታ እንዳይከናወን በመቃወም ሰፊ ቀጣናዊ የበላይነት ስትራቴጂዋ የቅርብ ጊዜ መገለጫ ነው ያሉት አቶ ሙሳ፤ ግብፅ የህዳሴ ግድብን እንደ ስጋት ብታነሳውም ግድቡ የልማት ፕሮጀክት እንጂ የፖለቲካ ጉዳይ አለመሆኑን ይገልጻሉ።

ግድቡ የተገደበው የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ስለመሆኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንደሚያውቀውበማንሳት፤ ይህ ደግሞ ውሃው ተገድቦ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደማይቀር የሚያሳይ መሆኑን ያስገነዝባሉ። በአንፃሩ ግብፅ ግድቡ ከተሠራ በኋላ ዓመቱን ሙሉ ተመሳሳይ የሆነ ተጨማሪ የውሃ ፍሰት የምታገኝ መሆኗን ያስረዳሉ።

ሆኖም ግብፅ ይህንን በትክክል እያወቀች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን ስለሚጠቅም ብቻ ፖለቲካዊ ጉዳይ በማድረግና ከብሔራዊ ደኅንነቷ ጋር አያይዛ ዓለምን በመዞር የተለያዩ ጫናዎችን ለማሳደር ጥራለች ነው ያሉት።

እንደ አቶ ሙሳ ማብራሪያ፤ ግብፅ የግድቡን አሞላል እና ሥራ ለመገደብ ዓለማቀፋዊ እና አሕጉራዊ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን ለመጠቀም ጥረት አድርጋለች። ይህም የዓረብ ሊግን፣ የአፍሪካ ኅብረትን ማግባባት እና ጉዳዩን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ፊት ማቅረብን ያካትታል። የግብፅ አመራር ግድቡ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ደጋግሞ ሲያስጠነቅቅ ውዝግቡን የልማት ብቻ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ አድርጎታል።

ይህ ደግሞ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ልማት ለመገደብ እና የግብፅን የጂኦፖለቲካዊ የበላይነት በዓባይ ተፋሰስ ላይ ለማስቀጠል ትልቁ ስትራቴጂ አካል ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የግብፅ መሪዎች “ሁሉም አማራጮች በጠረጴዛ ላይ ናቸው” ሲሉ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል። ይህም የተከደነ ወታደራዊ ርምጃ ወይም የበለጠ ድብቅ የማተራመስ ዘዴዎችን ስለማካተቱ ሰሞናዊ እንቅስቃሴዋ በይፋ የሚናገር ነው ባይ ናቸው።

ቢቢሲን ጨምሮ የውጭ ሚዲያዎች በዘገባቸው እንዳመላከቱት፤ ግብፅም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ከኢትዮጵያ ቀጣናዊ ተቀናቃኞች ጋር ጥምረት ለመፍጠር እየሞከረች ትገኛለች። ይህም ከኤርትራ ጋር ያለውን የጠበቀ ግንኙነት እንዲሁም የግብፅ ወታደራዊ አባላትን እንደ ሶማሊያ ባሉ ሀገራት ማሰማራትን ያጠቃልላል። እነዚህ እርምጃዎች ግብፅ የኢትዮጵያን አለመረጋጋት በቀጥታ በመጋፈጥም ይሁን በክልላዊ የውክልና ግጭቶች ጠንካራና በኢኮኖሚ የበለፀገች ኢትዮጵያን ስጋት ለመመከት እንደ አንድ አዋጭ ስልት መመልከቷን ቀጥላለች ሲሉ አቶ ሙሳ ያብራራሉ።

ሆኖም ይላሉ አቶ ሙሳ፤ የዓባይ ግድብ ለእነዚህ ውጥረቶች መነሻ ይሁን እንጂ፤ ግብፅ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የምታደርገው ጥረት ግን ከግድቡ የዘለለ ሆኗል ሲሉ ያስረዳሉ።

ግብፅ በቅርቡ በሶማሊያ እና በኤርትራ የምታደርገው እንቅስቃሴ ታሪካዊ የጣልቃ ገብ ፖሊሲዋ መቀጠሉን ያሳያል ያሉት አቶ ሙሳ፤ በእነዚህ ጎረቤት ሀገራት ወታደሮቿን በማሰማራት እና ልዩ ሥራዎችን በመሥራት ግብፅ በኢትዮጵያ ድንበሮች ዙሪያ አለመረጋጋት ለመፍጠር ጥረት እያደረገች መሆኗን ይጠቅሳሉ።

አቶ ሙሳ፤ ግብፅ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ወደኢትዮጵያ ጎረቤት ሃገራት የገባችበት አካሄድ እንዲሁም ጎረቤት ሀገራትን መሠረት አድርጎ ስትራቴጂ መንደፍና ቀጣናውን ለማተራመስ መሞከር አዲስ አይደለም። ይህ የግብፅ ታሪካዊ የሆነ የዲፕሎማሲ ስህተት ጠላትነትን ይፋ የማድረግ አካሄድ ራሷን ግብፅን አደጋ ላይ የሚጥልና የሚያዋርድ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ግብፅ በሶማሊያ የሚገኙ አንጃዎችን በመደገፍ በኢትዮጵያ ላይ በጠላትነት የሚፈረጁ ቡድኖችን በመደገፍ፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አቅምን የሚገድብ አለመረጋጋት ለመፍጠር መጣሯ አግባብነት የጎደለው ነው ይላሉ አቶ ሙሳ።

አንዳንድ ጎረቤት ሀገራትም በግብፅ ስትራቴጂ ውስጥ ቁልፍ ተዋናይ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ የጎረቤት ሀገራት መንግሥታት ግብፅ ጥምረት ለመፍጠር የምታደርገው ሰፊ ጥረት አካል ሊሆኑ አይገባም ሲሉ አሳስበዋል።

ይህንን ለመቀልበስ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን ማጠናከር እንደሚገባ፤ የመከላከያ ሪፎርሙን ተከትሎ ወታደራዊ ዝግጁነቱም ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የምሥራቅ አፍሪካ ጂኦፖለቲካ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን ይናገራሉ።

በተለይም የዓባይ ግድብ እየተጠናቀቀ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ግብፅ ዓባይ ወንዝ የኛ ነው የሚል ታሪካዊ ትርክት በመያዝ ቀጣናውን ለማተራመስ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኗን ጠቅሰዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሱማሊላንድ ጋር ወደብን አስመልክቶ ያደረገውን ስምምነት ለማስጮህ ከሱማሊያ ጋር ግንኙነት በመፍጠር፤ ቀጥሎም ከኤርትራ ጋር ግንኙነት በመፍጠር አጠቃላይ ቀጣናው ላይ ችግር እንዲፈጠር ግብፅ ፍላጎቷን እያሳየች ነው።

ግድቡ ከተሠራ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ የበላይነት ይኖራታል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነቷ እያደገ ይመጣል በሚል ስጋትና፤ ይህንን ለማስቆም በሚደረግ ጥረት ውስጥ ኢትዮጵያ ሠላም እንዳትሆን፣ አንድነቷ እንዳይረጋጋ እየሠራች ትገኛለች ነው ያሉት።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኤርትራ የግብፅ የጦር ሰፈሮች መቋቋማቸውን የሚገልጹ ዘገባዎች እየወጡ መሆኑን አስመልክቶ አቶ ሙሳ በዚህ ዙሪያ እንዳሉት እነዚህ እንቅስቃሴዎች ከዚህ ቀደምም የነበሩ መሆናቸውን ጠቅሰው ግብፅ ኢትዮጵያን በጠላት ለመክበብ የምታደርገውን ታሪካዊ ጥረት ቀጣይነት ያመለክታሉ ይላሉ።

እርሳቸው እንደሚገልጹት፤ ግብፅ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የምታደርገው ጥረት የረዥም ጊዜ የጣልቃ ገብነት አካል ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ፅናት እንደሚያሳየው ግን አሁንም ከእነዚህ ፈተናዎች በላይ እንደምትወጣ ነው።

ሁለቱም ሀገሮች በዚህ ውስብስብ ጂኦፖለቲካዊ ምኅዳር ሲጓዙ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ዲፕሎማሲ የበለጠ ተባብሶ እንዳይከሰት ለመከላከልና ዓባይ ከግጭት ይልቅ የትብብር ምንጭ ሆኖ እንዲቀጥል መሥራት እንደሚገባም ተገልጿል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You