አዲስ አበባ፡– በትግራይ ክልል የተከሰተውን የወባ በሽታ ለመግታት ኅብረተሰቡ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በማፋሰስና አንጎበር በመጠቀም ራሱን ከበሽታው መከላከል ይጠበቅበታል ሲል የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተከሰተውን የወባ በሽታ ለመከላከልም ትኩረት እንደሚያስፈልገው ተጠቁሟል።
በቢሮው የበሽታ መቆጣጠር እና መከላከል ቡድን መሪ አቶ አረጋይ ገብረመድህን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ 70 በመቶ የክልሉ ማህበረሰብ የወባ በሽታ ተፅእኖ ውስጥ ይገኛል። ይህን ችግር ለመቅረፍ በአካባቢው የሚገኝ ውሃ ያቆረ ቦታ የትንኝ መራቢያ እንዳይሆን እያፀዳ ራሱን ከበሽታው መከላከል አለበት። በተጨማሪም ኅብረተሰቡ የወባ በሽታ ምልክት ሲታይበት በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ህክምና ማግኘት ይኖርበታል።
አስተባባሪው እንዳሉት፤ የወባ በሽታ በሁሉም የክልሉ ወረዳዎች እየተስፋፋ ይገኛል። በተለይ በአስር ወረዳዎች ተምቤን ቀይሕ ተኽሊ፣ ደቡብ ራያ ጨርጨር፣ ሰሜን ምዕራብ አስገደ፣ አድያቦ፣ዓዴት እና ሌሎች አካባቢዎች እየተስፋፋ ነው።
በጦርነቱ ምክንያት በክልሉ የሚገኙ የተጎዱት የጤና ተቋማት በሚፈለገው ደረጃ ማስተካከል ባለመቻሉ ፣በቂ መድኃኒት ባለመኖሩ እና በባለሙያ እጥረት በሽታው ከባድ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል ብለዋል። በተጨማሪም የመከላከያ አንጎበርና የሚረጭ የወባ መከላከያ ኬሚካል አለመኖሩን ጠቅሰዋል።
ኅብረተሰቡ በሽታውን መከላከል እንዲችል ቀደም ሲል አንጎበር የነበራቸው በአግባቡ እንዲጠቀሙ ተናግረዋል። ከቤት ውጪ ሲያመሹ የወባ ትንኝ ልትነድፋቸው ስለ ምትችል በጊዜ እንዲገቡ እና በተለይ እናቶች እና ሕፃናት በተገኘው ጨርቅ ሙሉ ሰውነታቸውን ተሸፍነው እንዲተኙ መክረዋል።
በመሆኑም ኅብረተሰቡ በጤና ዙሪያ መረጃ የሚያስተላልፉ ሚዲያዎችን በንቃት እንዲከታተል እና በአካባቢው የሚገኝ ውሃ ያቆረ ቦታ የትንኝ መራቢያ እንዳይሆን እያፀዳ ራሱን ከበሽታው እንዲከላከል
አሳስበዋል። በተጨማሪም ኅብረተሰቡ የወባ በሽታ ምልክት ሲታይበት በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ህክምና እንዲያገኘ አስረድተዋል።
በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተከሰተውን የወባ በሽታ ዘለቄታዊ መፍትሄ እንዲኖረው በመንግሥት እና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል ያሉት አስተባባሪው፤ በሽታውን ለመግታት የሚያስፈልጉ ግብአቶች አንጎበር፣የሚረጭ ኬሚካል እንዲሁም በቂ ባለሙያ እና የጤና ተቋም ለማሟላት እገዛ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም