ዜና ሀተታ
ተማሪዎች የተሻለና ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በማግኘት በትምህርታቸው ስኬታማና ውጤታማ እንዲሆኑ የእያንዳንዱ መምህርና የትምህርት ዘርፉ አስተዳደር የማይተካ ድርሻ አለው፡፡ ለትምህርት ውጤት መረጋገጥ የመምህራን፣ የተማሪዎችና የትምህርት ሥራ ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑ ይገለጻል፡፡ የዛሬ ተማሪዎች የነገ ሀገር ተረካቢና ገንቢ ዜጎች እንዲሆኑ በዘርፉ የሚገኙ ተዋንያን ለአዲሱ የትምህርት ዘመን የተለያዩ ዝግጅቶችን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
መምህራንን የማጣቀሻ መጽሐፍትን ማዘጋጀት፣ ተማሪዎች እውቀትና ችሎታቸው እንዲጎለብት ትኩረታቸውን ንባብ ላይ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በ2017 የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ትምህርት ቤቶች፣ መምህራን እና ተማሪዎች ዝግጅት ምን እንደሆነ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡
በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የዝግጀት ሥራ መሠራታቸውን የደጅ አዝማች በላይ ዘለቀ 2ኛ ደረጃና የብሔራዊ ቤተ መንግሥት አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ገልጸዋል።
የደጅ አዝማች በላይ ዘለቀ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አዲስዓለም ታዬ እንዳሉት፤ በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ከወላጆች፣ ከመምህራንና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመወያየት የዝግጅት ሥራዎች ተከናውነዋል።
በትምህርት ቤቱ በባለፈው የትምህርት ዘመን 94 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች የክፍል ውጤታቸው ከግማሽ በላይ መሆኑን ገልጸው፤ በ2017 የትምህርት ዘመን ውጤቱን በማሻሻል 97 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎችን ለማሳለፍና ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ታቅዷል ይላሉ።
የመማር ማስተማር ሥራዎችን የሚያሳልጡ የተማሪዎች የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም)ና የትምህርት ቁሳቁሶችን የማሟላት ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመው፤ የተማሪ ወላጆች በትምህርት ቤት ሁለንተናዊ ልማት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ እቅዱ እንዲሳካ መሥራት እንደሚገባቸውም ይገልጻሉ።
ከትምህርት ባለፈ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ሥነምግባር የተላበሱ ዜጎች እንዲሆኑ እየሠራ እንደሚገኝ ርዕሰ መምህር አዲስዓለም ይናገራሉ። ትምህርት ቤቱ በባለፈው የትምህርት ዘመን የነበሩ ክፍተቶችን በማረም ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ እንደሚሠራ ያስረዳሉ። የተወሰኑ የትምህርት ግብዓቶች እጥረት መኖሩን ገልጸው፤ ለማሟላት ከትምህርት ቢሮ ጋር እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
የብሔራዊ ቤተ መንግሥት አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር መንግሥቱ ታደለ በበኩላቸው፤ ትምህርት ቤቱ በትምህርት ዘመኑ ከተማ አቀፍ ፈተና የሚወስዱ የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ በልዩ ትኩረት እየሠራ ይገኛል ይላሉ።
ለመማር ማስተማር ሥራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ቀደም ብለው ለተማሪዎች እንዲደርሱ ተደርገዋል ያሉት ርዕሰ መምህር መንግስቱ፤ በቀጣይ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠት ታቅዷል ።ለዕቅዱ ስኬታማነትም የትምህርት ጥራትን የሚያረጋግጥ ውጤት እንዲመዘገብ የትምህርት ቤት አስተዳደር፣ መምህራን፣ ተማሪዎች እንዲሁም ወላጆች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።
መምህር ደረጀ አባቡና መምህርት ኩሪ ለገሠ የትምህርት ቤቶቹ መምህራን ሲሆኑ፤ ተማሪዎች በዓመቱ መጨረሻ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ትምህርታቸውን በርትተው ማጥናትና በጥሩ ሥነ ምግባር መከታተል እንደሚገባቸው ይገልጻሉ። በተጨማሪም በመምህራኖቻቸው የሚሰጡትን እውቀቶች ወደ ውጤት ለመቀየር ወላጆች ልጆቻቸውን መደገፍና ማበረታታት ይገባቸዋል ነው ያሉት።
የትምህርት ቤቶቹ ተማሪዎች የሆኑት ተማሪ ቃልኪዳን ክብሩና ተማሪ ሀያት ዚያድ በበኩላቸው፤ በባለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ወደ ቀጣይ የክፍል ደረጃ ማለፍ እንደቻሉ ገልጸው፤ በዚህ ዓመትም ጠንክረው ለመማርና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መዘጋጀታቸውን ነው የነገሩን። ሌሎች ተማሪዎችም በየትምህርት ቤቶች ከሚገኙ ጎበዝ ተማሪዎች የሚከተሉትን መንገድ በመከተል ውጤታማ እንዲሆኑ ከወዲሁ ተግተው ትምህርታቸውን ሊማሩ ይገባል ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም