![](https://press.et/wp-content/uploads/2019/07/ታተተተ-2-11-2-2.png)
የክረምቱ መግቢያ ተማሪዎች የጥረታቸውን ፍሬ የሚያፈሱበት፤ ቤተሰቦች የልፋታቸውን ውጤት አይተው የሚደሰቱበት ወቅት ነው። እንደ ሀገርም የተለያየ ሙያና እውቀት ገብይተው፣ ሀገርና ወገንን ሊያገለግሉ የሚችሉ የተማሩ ወጣቶች ሀላፊነት ለመሸከም ተዘጋጅተው ወደ ገበያው የሚቀላቀሉበት ጊዜ በመሆኑ ደስታው ለሁሉም ነው።
በያዝነው ዓመት ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ 152 ሺ 463 ተማሪዎች ይመረቃሉ። ከግል ትምህርት ተቋማትም እንዲሁ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ይመረቃሉ ተብሎ ይጠበቃል ።
እነዚህ ምሩቃን በያዙት ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ተግተው ከሠሩ የወገኖቻችንን ሕይወት በመለወጥ፤ ሀገራችንን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ያሳልፋሉ የሚል ትልቅ ዕምነትም፣ ግምትም አለ። ይህንን ለማድረግ ታዲያ ከማን ምን ይጠበቃል የሚለውን በጉልህ ለይቶ ጠንካራ እንቅስቃሴ ማድረግ ይገባል ።
ከምርቃት በኋላ ተመራቂዎች በሕይወታቸው አዲስ ምዕራፍ የሚጀምሩበት በመሆኑም መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ሆኖም በተፈጠረው ዕድል ለመቀጠር ማለም ብቻ ሳይሆን በመረጃ እና በቴክኖሎጂ ዘመን እንደተፈጠረ ትውልድ ሁሉ የሥራ ፈጠራን በማዳበር ለራሳችሁ ብቻ ሳይሆን ለመሰሎቻችሁም የሚበቃ የሥራ መስክ ፈጣሪ መሆን ይጠበቅባችኋል።
በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከ11 ሚሊየን በላይ ስራ አጥ ወጣቶች ይገኛሉ። በየዓመቱም ከሁለት ሚሊዮን የማያንስ ወጣት ወደ ስራ አጥነት ይቀላቀላል ። ኢኮኖሚው እስከ አሁን በዓመት የሚፈጥረው የሥራ ዕድል ከአንድ ሚሊዮን አይዘልም። ስለዚህ መንግስት ምንም ያህል ጥረት ቢያደርግ ይሄንን ሁሉ ስራ ፈላጊ የስራ ባለቤት ያደርጋል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው ።
መንግስትም ያረጋገጠው በቀጣይ በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ሶስት ሚሊዮን ወጣቶችን በሀገር ውስጥ እና በውጪ የስራ ዕድል ተጠቃሚ የማድረግ ዕቅድ መኖሩን ነው። ከዚህ ውጪ ያለውስ ስራ ፈላጊ የሚለው ጥያቄ ደግሞ መመለስ ያለበት አንድም በባለሀብቱ ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በራሱ በስራ አጡ እና በቤተሰብ መሆኑ እንዳለበት ለአንድ አፍታም መዘንጋት የለበትም።
ምክንያቱም መንግስት አሁን ያለውን ስራ አጥ በሙሉ ወደ ስራ የሚያስገባ ኢኮኖሚ የለውም ፤ አልገነባም። ስለዚህ ትልቁ ተስፋ ያለው ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ዜጎች በባለሀብቶችና በግላቸው እንዲሁም በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው እንዲሰሩ ማድረግ ነው። ይሄንን ለማድረግም ሆነ መንግስት ባሰበው ልክ የስራ ዕድሉን እንዲያሰፋ ደግሞ ዋናው ጉዳይ የሀገር ሰላም መሆን ነው። ሀገር ሰላም እንዲሆን በዋነኛነት መስራትና መተባበር ያለበትም ህብረተሰቡ በተለይም ደግሞ ወጣቱ ነው።
በመንግስት በ2011 የበጀት ዓመት ለ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። በአብዛኛው የተፈጠሩት የስራ እድሎች የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማትን በመጠቀም ነው።
ይሄ ካለው የስራ አጥ ቁጥር አንጻር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። አሁንም ድረስ ያሉት የሥራ እድል መፍጠሪያ መንገዶች በመንግሥት ጥረት ላይ የተመረኮዙ፤ በሜጋ ፕሮጀክቶችና በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት እንዲሁም በመጠነ ሰፊ የሕዝብ አገልግሎትና መሠረተ ልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው።
የሥራ ዕድል ፈጠራ ምህዳር በመጪዎቹ ጊዜያት በግሉ ዘርፍ ተጨማሪ ሠራተኞችን መያዝ እንዲችል ማበረታታትና በውጭ ሀገር የሥራ ዕድል ፕሮግራም ያልሰለጠነ ሰው ከመላክ የሠለጠነ ባለሙያ ወደ መላክ መሸጋገር ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው። ከተለያዩ የአረብ ሀገራት ጋርም የስራ ውል ስምምነቶች እየተደረገ ይገኛል።
በመንግስት በኩል በዚህ ደረጃ ጥረቶች መኖራቸው የሚያበረታታ ቢሆንም አሁንም ስራ አጡን ወደ ስራ ማስገባት የመንግስት ብቻ ሀላፊነትም ግዴታም መሆን የለበትም። ስለዚህ በመጀመሪያ ተመራቂ ተማሪዎች ሀላፊነቱን መውሰድ እና የመንግስትን እጅ ከመጠበቅ ይልቅ በራሳቸው ስራ ፈጥረው የሚሰሩበትን የስነልቡና ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ሌላው ደግሞ ቤተሰብ ነው። በተለይ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው ቤተሰቦች ያስተሟሯቸውን ልጆቻቸውን እንዲሁም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ቤተሰብ አንጀቱን አስሮ ለሀገር ለወገን ይበቃሉ ብሎ ያስተማራቸው ምሩቃን እውቀታቸውን ጉልበታቸውን ይዘው በአልባሌ በታ እንዳይውሉ ፤ መቀጠርን ብቻ በማሰብ ጊዜያቸውን እንዳያባክኑ በተገኘው አጋጠሚ ሁሉ የስራ ባለቤት የሚሆኑበትን መንገድ ማመቻቸቱን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው።
ስራ አጥ ዜጎችን የስራ ባለቤት ማድረግ በመንግስት ላይ ብቻ የሚወድቅ ሸክም ሳይሆን የእያንዳንዱም ዜጋ ሀላፊነት እና ግዴታ መሆኑን በመገንዘብ መንቀሳቀስ ይገባል። በተለይ ደግሞ ምሩቃኑ ስራ ጠባቂ ከመሆን ወጥተው ስራ ፈጣሪ መሆን ይገባቸዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2011