ምዕራባውያን ዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳይሎችን እንድትጠቀም ፈቃድ የሚሰጡ ከሆነ ከሩሲያ ጋር በቀጥታ እንደሚዋጉ ይወቁት ሲሉ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ተናገሩ፡፡
ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ምዕራባውያን ይህን ውሳኔ የሚወስኑ ከሆነ የጦርነቱ መዳረሻ የት ድረስ ሊሆን እንደሚችል መገመት ከባድ ነው ብለዋል፡፡
አሜሪካ ለዩክሬን የሰጠችው የረጅም ርቀት ሚሳይል በሩሲያ ውስጥ የሚገኙ ኢላማዎች ላይ ጥቃት ለመፈጸም እንዲውሉ ፈቃድ ለመስጠት እያጤነች እንደምትገኝ ከሰሞኑ ማስታወቋ ይታወሳል፡፡
ከአሜሪካ በተጨማሪ ብሪታንያም ይህን የዋሽንግተን ውሳኔ ልትከተል እንደምትችል ተነግሯል፡፡ ይህን ተከትሎ ነው ፑቲን ምዕራባውያን ጦርነቱን ቀጣናዊ ከሚያደርግ ድርጊት እንዲቆጠቡ ያስጠነቀቁት፡፡
በተጨማሪም ሞስኮ ተገቢ ነው ያለችውን እርምጃ ሁሉ እንደምትወስድ ዝተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ ለኪዬቭ የረዥም ርቀት ሚሳኤሎችን የሚያቀርቡ ሀገራትን በቀጥታ ወደ ጦርነቱ ይጎትታል ነው ያሉት፡፡
ምክንያቱም ዩክሬን የሳተላይት ኢላማ መረጃ እና የሚሳይሎቹ አካሄድ የሚከታተል መሰረተ ልማት ስለሌላት በኔቶ አባል ሀገራት የሚከወን ይሆናል፤ ይህም በቀጥታ መሳተፋቸውን የሚያረገግጥ ነው ብለዋል፡፡
ስለሆነም ጉዳዩ ለዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳይል የመፍቀድ እና ያለመፍቀድ ሳይሆን የኔቶ አባል ሀገራት በቀጥታ የሚኖራቸውን ተሳትፎ የሚወስን ነው ሲሉ ዝተዋል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮልደሚር ዘለንስኪ የሞስኮን የማጥቃት አቅም ይቀንሳሉ ያሏቸውን በሩሲያ ውስጥ የሚገኙ ኢላማዎችን ለማጥቃት ፈቃድ እንዲሰጣቸው ለወራት ሲወተውቱ ቆይተዋል፡፡
ዩክሬን የምዕራባውያን የጦር መሳሪያ ድጋፍ መዘግየትና ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳይሎችን እንዳትጠቀም የተጣሉባት ማዕቀቦች ለመልሶ ማጥቃቱ አለመሳካት በምክንያትነት ስታቀርብ መቆየቷ ይታወሳል።
የምዕራባውያን ሚሳይሎች በሩሲያ ግዛት ውስጥ ጥቃት ከተፈጸመባቸው የጦርነቱን አድማስ እንደሚያሰፋውና “የኒዩክሌር ጦርነት” ሊጀምር እንደሚችልም ፑቲን ከዚህ ቀደም ገልጸው ነበር።
በአሁኑ ማስጠንቀቂያቸውም ሀገራቸው ጠላቶቿ በዚህ ልክ ሲተባበሩባት ከዳር ቆማ እንደማትመለከት እና ሉአላዊነታቸውን ለማስጠበቅ መውሰድ የሚጠበቅባቸውን እርምጃ ያለማመንታት እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2017 ዓ.ም