የአፍሪካን አህጉር እግር ኳስ የሚመራው ካፍ ስፖርቱን ለማሳደግ መሰረቱ በታዳጊዎች ላይ መሆኑን ሲናገር ይሰማል። ካፍ ይሄንን መሰረት በማድረግ ታዳጊዎች ላይ መሰረት ያደረገ ተግባር እያከናወነ ይገኛል። ታዳጊዎችንም ማዕከል ያደረጉ የውድድር መርሃ ግብሮችን እየቀረፀ እየሠራ ይገኛል። የካፍ የታዳጊዎች ውድድር ዋና አላማ ዋንጫ ማሸነፍ ሳይሆን ተተኪዎችን ማፍራት ነው፡፡
በአፍሪካ ውስጥ ግን የታዳጊዎች ውድድር ውጤት ፍላጋ ላይ ብቻ በማተኮር ፌዴሬሽኖች እና ክለቦች በአህጉሪቱን እምቅ ችሎታ ያላቸውን ታዳጊዎች እንዳይፈሩ እንቅፋት ሆነዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን፤ የዕድሜ ማጭበርበር በጉልህ በሚታይበት የአህጉሪቱ እግር ኳስ ውስጥም በታዳጊዎች ላይ ከመሥራት መቦዘን አልፈለገም። ማህበሩ የኮካ ኮላ አፍሪካ አገራት ከ16 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድርን ይፋ በማድረግ ይሄንኑ አስመስክሯል።
ፌዴሬሽኖች እና ካፍ በዕድሜ ማጭበርበር ላይ ያለቸው አመለካከት ስለመቀየሩ የሚተማመኑ ቢሆንም፤ የአዘጋጅነት ዕድሉን ኬኒያ በመውሰድ በሰሜን ምዕራብ ናይሮቢ በምትገኘው ናኩሩ አስተዳደር ከትናንት በስቲያ ውድድሩ ተጀምሯል። የውድድሩ ግብ «አፍሪካን የሚያስጠሩ ኮከብ ተጫዋቾች ማፍራት» ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአህጉሪቷ የነገ የእግር ኳስ መስታወት የሆነ ውድድር ተደርጎ ተቆጥሯል።
የአፍርካን የነገ ተስፋ በመሰነቅ 12 አገራት ማለትም፤ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ኢትዮጵያ፣ ሞዛምቢክ፣ ዛምቢያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ዚምባቡዌ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ሴኔጋል በውድድሩ እየተሳተፉ ይገኛሉ። በሰባት የውድድር ቀናት ቡድኖቹ በአራት ምድብ የተከፈሉ ሲሆን በምድብ ሀ አዘጋጇ ኬኒያ ኢትዮጵያ ተደልድለዋል።
ውድድሩ ከትናንት በስቲያ በምድብ ሀ በሚገኙት ኬኒያ እና ኢትዮጵያ የተጀመረ ሲሆን፤ አዘጋጇ አገር ኬኒያ በድል በመውጣት ጅማሮውን በሰመረ መልኩ አድርጋለች። የኬኒያ ታዳጊዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን አንገት ባስደፋ መልኩ 11 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፋለች። የኢትዮጵያ ከ16 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የደረሰበት አስደንጋጭ ሽንፈት የአገሪቱ ስፖርት ከጊዜ ወደጊዜ እያሳየ ያለውን የቁልቁለት ጉዞ የሚያመለክት ነው። የዚህ ብሔራዊ ቡድን 16 ተጫዋቾች የኮካ ኮላ ኩባንያ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ባካሄዳቸው የኮፓ ኮካ ኮላ ከ15 ዓመት በታች አገር አቀፍ የታዳጊ ውድድር ላይ የተሳተፉ ናቸው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የታዳጊ ተጫዋቾቹን ምልመላና መረጣ ያካሄደ ሲሆን የተመረጡት ተጫዋቾችም በአገር አቀፉ ውድድር ላይ ጥሩ ብቃት ያሳዩ ናቸው።
በአገሪቱ የእግር ኳስ አቅም አላቸው የሚባሉትን ታዳጊዎች በመመልመል ይህ አይነቱ የሽንፈት ቅሌት መድረሱ የእግር ኳሱ መሰረት እንደተናጋ እንደማሳያ የሚወሰድ መሆኑን የተለያዩ የስፖርት ቤተሰቦች በሰጡት አስተያየት ገልፀዋል። ባለድሎቹ ኬኒያውያኖች በእግር ኳሱ ምስራቅ አፍሪካን ብቻም ሳይሆን በአህጉር ደረጃ ያላቸውን ውጤታማነት ለማሳደግ የሚያስችል ተግባራት እያከናወኑ መሆኑን የትናንት በስቲያው ጨዋታ የሚያመላክት ነው። የምድቡን ሁለተኛ ጨዋታ በዛሬው ዕለት ከቦትስዋና የሚያደርገው የኬኒያ ብሔራዊ ቡድን ካሸነፈ ወደ ግማሽ ፍፃሜ በቀጥታ መቀላቀሉን እንደሚያረጋግጥ ታውቋል።
በሌላ በኩል፤ በምድብ ለ የሚገኙት ናይጄሪያ እና ዛምቢያ ጨዋታቸውን አከናውነዋል። በሁለቱ ቡድኖች መካከል በተደረገው ጨዋታ የአፍሪካ እግር ኳስ ክዋክብት መፍለቂያዋ ናይጄሪያ ድል ሳይቀናት አልቀናትም። ይልቁንም የነገው ተስፋዋን ይዛ የቀረበችው ዛምቢያ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት በመርታት ጅማሬዋን አሳምራለች። ጥሩ የእግር ኳስ እንቅስቃሴ በታየበት በዚህ ጨዋታ ለአህጉሪቷ እግር ኳስ ተስፋ ሰጪ ታዳጊዎች መኖራቸውን ያሳዩ መሆናቸውን የተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ዘግበውታል።
ጨዋታውን በአሸናፊነት ያጠናቀቁት ዛምቢያዎችም ሆኑ ተሸናፊዎቹ ናይጄሪያዎች የምድብ ቀሪ ጨዋታዎችን በተጠናከረ መልኩ ማከናወን እንዳለባቸው የቤት ሥራ ለመውሰድ የተገደደበት ነበር ተብሏል። ከትናንት በስቲያ የተጀመረው ይህ ውድድር አፍሪካን የሚያስጠሩ ኮከብ ተጫዋቾች ማፍራትን ግቡ ማድረጉን ተከትሎ ፤ በአጀማመሬ እንደታየው መድረኩ የአህጉሪቷ የነገ የእግር ኳስ መስታወት ሆኖ መንፀባረቁ ተነግሯል።
የኮካ ኮላ አፍሪካ አገራት ከ16 ዓመት በታች እግር ኳስ ውድድር በሰሜን ምዕራብ ናይሮቢ በምትገኘው ናኩሩ አስተዳደር እየተካሄደ እስከ ቀጣዩ ቅዳሜ የሚዘልቅ ሲሆን ዛሬና ነገ የምድብ ጨዋታዎች ይደረጋል።
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 3/2011
ዳንኤል ዘነበ