ጳጉሜን እና ኢትዮጵያዊነት

ጊዜ በተፈጥሮ አስገዳጅ ምህዋር ላይ እየተሽከረከረ ይሄዳል..ይመጣል። የሰው ልጅም በዚህ የጊዜ እሽክርክሪት ውስጥ መሪ ተዋናይ ሆኖ ከዘመን ወደዘመን ይመላለሳል። ከመስከረም እስከ ነሀሴ። እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ከዚህ ብዙሃነ እውነታ ተለይተን በራሳችን የዘመን አቆጣጠር ሠልጥነን በአስራ ሶስት ወር ጸጋ ያማርን ነን። ከሌላው የሰው ልጅ በተለየ መልኩ የምንረግጠው፣ የምንነካው፣ የምንደርስበት ሌላ የዘመን እውነት አለን..ጳጉሜ የሚባል።

ጳጉሜን ሲነሳ አብሮ የሚነሳ አንድ ታላቅ ስም ፤ ኢትዮጵያዊነት ነው። በዓለም ፊት በዚህ ስም የሚጠራ ሌላ ሀገረ መንግሥት የለም። በዚህ አንድ አይነት በሆነ ዓለም ውስጥ ለየት ብለን እንድንቆምና እንድንታይ ካደረጉን ሀገራዊ ትውፊቶቻችን መካከል ጳጉሜን ያቀፈ ባህረ ሃሳባችን ይጠቀሳል። የዘመን አቆጣጠር ስሌታችን ከታላላቅና ካስደናቂ የክብር ስሞቻችን መሃል አንዱን ሆኖ ከትውልድ ትውልድ የተመመ ነው። በባህረ ሃሳብ ቀመር መሠረት ጳጉሜ ኢትዮጵያዊነትን የተፈጠረበት የድንቅ እውነት ታዛ ነው። በዚህ ድንቅ እውነት ከዓለም ሁሉ ሌላ ነን። በዚህ ድንቅ እውነት ከዓለም ሁሉ ፊተኞች ነን። በዚህ ድንቅ እውነት ከሰው ልጅ ሁሉ ባለታሪክ ነን።

ይህ ድንቅ እውነት ዓይኖች ሁሉ ኢትዮጵያን እንዲያዩ፣ ጆሮዎች ሁሉ ኢትዮጵያን እንዲያደምጡ ለዘመናት ያስገደደ ታሪካዊ እሴት ነው። እኔና እናተ የዚህ እውነት፣ የዚህ ፍጹምና ነፍስና ስጋ ነን። በዚህ የጥበብ ፈር ላይ ከእኛ በቀር ማንም አልተራመደም። በዘመን ስሌት ውስጥ ዓለም ይሄን ያክል ታሪካዊ ክስተት የላትም። እኛም ብንሆን ጳጉሜ እንደሰጠን፣ ከጳጉሜ እንዳገኘንው አይነት የወራት ገጸ በረከት የለንም።

አብዛኞቹ በረከቶቻችን ከጳጉሜ ማህጸን ውስጥ የሚመዘዙ ናቸው። ነሀሴን ተሻግረው በአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ የሚጀምሩ ናቸው። ዓለም እንኳን ሲጠየቅ ‹ኢትዮጵያ እንዴት ሆና ነው አስራ ሶስት የወራት ጸጋዎች ያሏት? በምን አይነት የዘመን አቆጣጠር ሕግ ነው አንድ ወር አምስትና ስድስት ቀን ብቻ ሊኖረው የሚችለው? ብሎ ነው። አዎ እውነት ነው ገና ዓለም ስለኢትዮጵያ የሚጠይቀው፣ የሚመራመረው ብዙ እውነት ይኖረዋል። ኢትዮጵያዊነት ያልተደረሰ፣ ያልተነገረ፣ ያልተደረሰበት ሩቅ ማንነት ስለሆነ።

በዘመን አቆጣጠር ሥርዓታችን ውስጥ እንደ ጳጉሜ አይነት ዘመነ አጭር ግን ደግሞ የታሪክ ሀብታም የለም። እንደ ሀገር ከከበርንባቸው እና እንድ ህዝብ ከተደነቅንባቸው ወራቶቻችን መካከል የዘመን አቆጣጠራችን ቀዳሚው ነው። ሌላ ሌላውን ትተን ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ፣ ጥንታዊው ትውልድ ምን ያክል ከዓለምና ከሥልጣኔ እንደቀደመ ጳጉሜን ማሰቡ ብቻ በቂ ነው። ዓለም ጊዜንና ዘመንን በአስራ ሁለት ወራት ሲከፍል ኢትዮጵያ አባቶቻችን በአስራ ሶስት ወራት የከፈሉበት ሚስጢር በራሱ ዓለም ያልተረዳው ምስጢር ነው።

ያለምንም ጥርጥር ጳጉሜን ውስጥ ኢትዮጵያዊነት አለ። ጳጉሜን ውስጥ ጥበብና እውቀት፣ ዘመናዊነትም ነፍስ ዘርተው አሉ። ጳጉሜን ውስጥ ድሮነት ከነወዙ ተቀምጧል። ጳጉሜን ውስጥ የጥቁር ሕዝቦች ትናንትናዊ አውድ፣ ትናንትናዊ እውቀትና ማስተዋል፣ ታሪክና ሥልጣኔ፣ ባህልና ቅርስ፣ ወግና ሥርዓት፣ ጀግንነትና አልሸነፍባይነት ሞልቶና ተትረፍርፎ አለ።

ጳጉሜን ውስጥ የአባቶቻችን ብልሀት ከዓለም ሁሉ በላይ ገኖ አለ። ለዚህም ነው ጳጉሜና ኢትዮጵያዊነት ስል የተነሳሁት። ለዚህም ነው የጳጉሜን መባቻ በሆነው የነሀሴ ወር ላይ ቆሜ አጭሯን ወር የማስቃኛችሁ። ይህ ወር ኢትዮጵያን ለዓለም ያስተዋወቀ፣ ብኩርናዋንም ቀድሞ የተናገረ ወራችን ነው። ጳጉሜና ኢትዮጵያዊነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽ ዘውድና ጎፈር ናቸው።

ከታሪክ አብራክ የበቀሉ የእውነትና የጥበብ ግንድ። ከአባቶች የዘመን ፍሬ ውስጥ የጸደቁ የጥቁርነት ሰምና ወርቅ። ጳጉሜና ኢትዮጵያዊነት መለኮታዊ ሃይልን የዋጁ የአበው የሊቃውንት ድጓ ልሳን ናቸው። ከተንስኦ የጣሙ፣ ከታሪክ የላሙ ጸዐዳ ቀለሞች። ከእውቀትና ከማይመረመው የጥበብ ኩሬ ውስጥ ዓለም ያልተረዳው፣ የሰው ልጅ ያልደረሰበትን የወራት ማለቂያ ፈልጎ ማግኘት አጀብ ብሎ ከማለፍ በቀር ምን ሊባል ይችላል?

ዓለም አንድ አይነት ነው። እኛን የሚያስንቅ ምንም የለውም። አስራ ሁለት ወራትን ሲያከብር እኛ ግን በራሳችን እውነት ተረማምደን አስራ ሶስት ወራትን እናከብራለን። ዓለም አስራ ሁለት ወራትን እንደ አንድ ዓመት ሲቆጥር እኛ ግን በራሳችን እውቀትና ጥበብ ተመርተን አስራ ሶስት ወራትን አንድ ዓመት እንላለን። ዓለም አንድን ወር ሃያ ስምንትና ሃያ ዘጠኝ ቀን ሰላሳም አድርጎ ሲቆጥር እኛ ግን በአባቶቻችን የጥበብ እውነት ልቀንና መጥቀን ጳጉሜን አምስትና ስድስት እንላለን ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ደግሞ ሰባት ብለን እናከብራለን። ታዲያ ልዩዎች አይደለን? ከዚህ በላይ ምን ጥበብ ምን ልቀት ይመጣል? በዘመን አቆጣጠራችን ዓለም ቢቀና ምን ይገርማል? ኢትዮጵያዊነት ያልተደረሰበት ጥበብ፣ ያልተደረሰበት ሚስጢር ነው ያልኳችሁ በምክንያት ነው።

በጣም የሚገርመው ደግሞ አሁን የምነግራችሁ ነው..አብዛኛው የዓለም ሀገራት ሕይወቱን፣ ዘመኑን የሚቆጥረው በሌላ ሀገር የዘመን መቁጠሪያ ነው። አብዛኛው የዓለም ሕዝብ አዲስ ዓመቱን የሚያከብረው በተወራረሰና የራሳቸው ያልሆነን የዘመን መቁጠሪያ ካላንደር በመጠቀም ነው። ዓለም ላይ በራሷ የቀን መቁጠሪያ የምትተዳደር የፕላኔታችን ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ እንደሆነች ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ?

የራሱን የዘመን መቁጠሪያ ባህረ ሃሳብ የሚጠቀም ብቸኛው ሕዝብ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነስ ይሄንንስ ደርሳችሁበታል? በዚህ እውነት ውስጥ መኖር ደስ አይልም ትላላችሁ? እልልልል…ክብር ለአባቶቻችን ይሁን። እንግዲህ ይቺን ነው ኢትዮጵያ የምላችሁ። ክብር ለነዛ ገናና ማንነትን ለሰጡን ሻካራ እጆች..ጠያይም ክንዶች፣ ሻንቅላ ፊቶች። ክብር ይሁን ለነዛ..ፊተኛ ላደረጉን ኋለኞች፣ ያልተደረሰበትን ኢትዮጵያዊነት ላወረሱን አስተዋይ ነፍሶች።

ከወራት ባለፈ ጳጉሜን የብዙ ነገር መጀመሪያችን ናት። የብዙ ህልሞች፣ የብዙ ተስፋዎች ማቆጥቆጫ አጸዳችን ናት። ከሰኔ ጉሩምሩምታ ሽረን፣ ከሀምሌ ጭጋግ ወጥተን፣ ከነፍራቃው ከነሀሴ እዬዬ ወደ ብሩህና ለምለሙ መስከረም የምናዘግምበት የንሰሀ ጎዳናችን ናት። የአደይ አበባ መፈጠሪያ፣ በዓመት አንድ ጊዜ የምትወጣው የመስቀል ወፍ ቀጠሮዋ ጳጉሜን ታካ ነው።

ጳጉሜን ወደ ላቀ እውነት፣ ወደ በለጠ ማንነት መንደርደሪያችን ናት። ወደ ትንሳኤ፣ ወደ ከፍታ፣ ወደ አዲስ ዓመት፣ ወደ አዲስ ተስፋ፣ ወደ አዲስ ብስራት መሸጋገሪያ ናት። አሮጌውን አስተሳሰብና አሮጌውን ዓመት ትተን ወደ ከበረ ሰዋዊ እውነት የምንሳብበት ሃይላችንም ናት። ከፊታችን ላሉት አስራ ሁለት ወራቶች ሞገስ ሆናን የምትቆም፣ ኢትዮጵያዊነት በተነሳ ቁጥር ከፊት የምትመጣ የወራት ቅንጣቢ ግን ደግሞ የታሪክ ባለጸጋችን ናት።

ዘመን የራሱ የሆነ የታሪክ ገጽ አለው። እንደ ኢትዮጵያውያን ያሉ አንዳንድ ጠቢባኖች በዚህ የዘመን ገጽ ላይ ታሪክ የሚያወሳውን ታሪክ ጽፈዋል። አንዳንዶች ደግሞ ሌሎች በጻፉት ታሪክ ማጌጥን ምርጫ አድርገው ተቀብለዋል። ዓለም በታሪክ ገጹ ላይ ከጻፈው እውነትም ይሁን ጀብድ የሚልቀው የእኛ የኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር ነው። ለዚህ ደግሞ አንድ ጊዜ አለምን ማሰብ በቂ ነው።

በአንድ አይነት ታሪክ፣ በአንድ አይነት እውነት፣ በአንድ አይነት አስተሳሰብ ውስጥ ናት። ወደእኛ ስንመጣ ግን ከዓለም ልዩ የሆነ በርካታ ነገሮችን ማየት እንችላለን። የምናነበው፣ የምንጽፈው፣ የምንማረው፣ ከዘመን ዘመን የምንሻገረው አባቶቻችን በዘመን ገጽ ላይ በከተቡት እውነት ነው። የምንቀምረው፣ የምናሰላው በራሳችን ፊደልና ቁጥር ነው።

ጳጉሜን ለሁላችንም የለውጥ ሀሁ ናት። ሁሉን ትተን ወደ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ የምናቀናበት የሰላማችን መዳረሻ ናት። ወደ አዲስ ተስፋ ፣ ወደ አዲስ ተፈጥሮ የምናዘግምበት የለውጥ ጅማሬ ናት። እንደ እድሜዋ የሆነ አጭር በረከት የላትም። በመስከረም መንደርደሪያ ጳጌሜን ላይ ቆመን ተስፋ የምንሰንቅ፣ መታደስ የሚጎበኘን፣ አሻግረን ነገን የምንመለከት ብዙ ነን። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፖለቲካና የማህበራዊ ተልዕኮዎች ማስፈጻሚያ እየሆነች የመጣችበት ሁኔታም እያየለ ነው።

መንግሥት እንኳን ጳጉሜን ዝም ብሎ ማለፍ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። የጳጉሜን ወር የመልካም ምኞት መሸጋገሪያ፣ የበጎ ተስፋና፣ የበጎ ህልም ጅማሬ በማድረግ እየተጠቀመበት ይገኛል። ከጳጉሜ አንድ ጀምሮ እስከ አምስትና ስድስተኛው ቀን ድረስ ፍቅርን፣ ሰላምን፣ አንድነትን እየሰበክን መጥተናል። ይቅርታን፣ መቻቻልን፣ ኢትዮጵያዊነትን እየተናገርንበት መጥተናል። ዘንድሮም በአዲስ አስተሳሰብ ጳጉሜን ጳጉሜን 1 የመሻገር ቀን፣ ጳጉሜን 2 የሪፎርም ቀን፣ ጳጉሜ 3 የሉዓላዊነት ቀን፣ ጳጉሜን 4 የህብር ቀን፣ ጳጉሜን 5 ደግሞ የነገ ቀን በመሆን ተሰይመዋል።

ጳጉሜን ከወራት ባለፈ የአዲስ ነገር መጀመሪያችን ናት። ከጥበብ፣ ከታሪክ፣ ከሥልጣኔ ባለፈ ፍቅርና አንድነትን የምንመሰክርበት፣ ጥላቻና ክፉ ነገርን የምንጸየፍበት፣ ያለፈውን ትተን የኢትዮጵያዊነት ቃል ኪዳን የምናስርበት የወራት ጌጣችን ናት። ኢትዮጵያዊነት ከዘመን፣ ከሥልጣኔ፣ ከታሪክ፣ ከሥርዓት፣ ከሕገመንግሥት፣ ከሀገር ግንባታ፣ ከመንግሥት ምስረታ ከዓለም ቀደምት ማንነት ነው።

ጳጉሜን የሁላችን መልክ ናት። ኢትዮጵያዊነትን ተቀልማ ጥቁርነትን ተነቅሳ ዓለምን አጀብ የምታሰኝ የበረከት ወራችን ናት። ብዙዎቻችን እንደምንለው የሚወደድ፣ የሚናፈቅ የሆነ ውብ ገጽ አላት። ከደስታ የዘለለ፣ ከፍሰሃ የተለቀ ጸጋን በጉያዋ ሸጉጣለች። የአስራ ሁለት ወር ማብቂያ፣ የአስራ ሁለት ወራት መጀመሪያ ስለሆነች የራሷ የሆነ የትዝታ ቀለም አላት።

የብዙ ታሪኮች መጀመሪያ፣ የብዙ ትዝታዎች ፍጻሜ ስለሆነች በመምጣቷ ውስጥ እንኖራለን በመሄዷ ውስጥም እንተክዛለን። ጳጉሜን የትዝታችን መጀመሪያና ማብቂያ ወር ጭምር ናት። ኢትዮጵያዊነትን በአጭር ቁመት በጠባብ ወርድ ይዛ በእያንዳንዳችን ነፍስና ስጋ ውስጥ የበቀለች የትዝታችን ፈርጥ ናት ።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን  መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You