እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሰን፣ አደረሳችሁ!

በሽርፍራፊ ሰከንዶች ልኬት፣ በቀናት እና ወራት ስሌት፣ በዓመታት ተቀምሮ ዘመን ዘመንን ሲተካ፤ የሰው ልጆችም ሕልምና ርዕይ፣ ተስፋና መንገድ አብሮ ይታደሳል፤ ቃልን በተግባር ለውጦ ለስኬት እንዲበቃም ይተጋል። ኢትዮጵያውያን ደግሞ በዚህ ረገድ ልዩ የሚሆኑበት አያሌ ጉዳዮች አሏቸው። አንዱ ዘመንን በራሳቸው ቀመር ለክተው መለወጣቸው ሲሆን፤ የዘመን ስሌታቸው በሚሰጣቸው አዲስ ዓመት፣ በአዲስ ተስፋና መንገድን ለተሻለ ነገር መትጋታቸውም የዚሁ አንድ አካል ነው።

አዲስ ዓመት ሲመጣ፣ ከእንኳን አደረሰህ/ሽ ከመባባል ባለፈም፤ ዘመኑ የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የመለወጥ፣ የስኬት እና የተሻለ ነገር ማግኛና ማሳኪያ እንዲሆን መልካም ምኞትን መግለጽም ሌላኛው የኢትዮጵያውያን ከፍ ያለ የመተሳሰብና መተሳሰራችን አስኳል ነው። ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን ለሌሎች መልካምን በመመኘት ውስጥ ለራሳችን መልካም ነገርን እንደምናገኝ እናምናለን። ቸር በማሰብ ውስጥ ቸር ማግኘትን፤ ስኬትን በማለም ውስጥ ስኬታማ መሆንን፤… በወጉ እንገነዘባለን።

እናም እንኳን አደረሳችሁ በማለት ውስጥ፣ ምስጋናን፤ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የስኬት፣ የጤና፣ የመተሳሰብ፣… ይሁንላችሁ በማለት ውስጥ፣ መልካም ነገርን ለሌሎችም፣ ለራሳችንም እንጋብዛለን። ምክንያቱም፣ አመስጋኝ ሰው ለተሻለ ስኬት የሚንደረደርበትን ዕድልም አቅምም ያገኛል። በተመሳሳይ፣ መልካም ነገርን የሚመኝ ሰው በተመኘውና ባሰበው ልክ እንዲደርስ የሚያስችለውን የትጋትም የጽናትም ልዕልናን ይጎናጸፋል።

ከዚህ አኳያ የ2016 ዓመተ ምሕረትን የበዙ ፈተናዎች ተሻግሮ፣ የበዙ መልካም ተግባራትንም ከውኖ ወደ 2017 ዓመተ ምህረት የተሸጋገረን ሕዝብና ወገን፣ እንኳን አደረሰህ ማለቱ፤ ያለፈውን መልካምም ክፉም ነገር አሳልፎ አዲሱን ዓመት እንድናይ ላደረገ ፈጣሪ የምስጋና ቃል ማውጣት ነው። አመስጋኝነት ደግሞ መባረክን ያመጣል። በመባረክ ውስጥ ደግሞ መተሳሰብ፣ ፍቅርና አንድነት፣ ሰላምና ይቅር ባይነት፣… የመሳሰሉ ከፍ ያሉ የሰው ልጅ እሴቶች ባለቤት መሆንን ይወልዳል።

ይሄን የሚያውቁ ኢትዮጵያውያን ታዲያ፣ ከእንኳን አደረሰህ/ሽ የምስጋና ቃላቸው ቀጥለው፤ አዲሱ ዓመት የመልካም ነገሮች ማግኛና መፈጸሚያ እንዲሆን ይመኛሉ። ይሄ ምኞታቸው ታዲያ በአመስጋኝነት ውስጥ የሚገኝን የሰው ልጆች ከፍ ያለ የሰብዕና እሴቶች ስለሚገነዘቡ ነው። ምክንያቱም፣ የሰው ልጅ ሰላም ሲሆን ሃሳቡም መንገዱም ሰላማዊ ነው። ይሄ የግለሰቦች ሰላማዊነት ሲደመር ደግሞ እንደ ማኅበረሰብም፣ እንደ ሕዝብና ሀገርም የሚፈለገውን ሰላም ያዋልዳል።

ሰላም ሲወለድ ደግሞ፣ ፍቅር፣ አብሮነት፣ መተሳሰብ፣ መረዳዳት፣ ለጋራ ሕልምና ራዕይ በጋራ መቆም፣ ስለ ሀገርና ሕዝብ ሁለንተናዊ ብልጽግና መትጋት ተከትለው ይወለዳሉ። እነዚህ ሲደመሩ ሀገር እንደ ሀገር፣ ሕዝብም እንደ ሕዝብ ካለፈው ዓመት የተሻለ እንዲያስብ፣ እንዲያቅድ፣ እንዲተገብር እና እቅድና ሕልሙንም እንዲያሳካ የሚችልበትን ከፍ ያለ ትጋትን፣ ቁርጠኝነትና ጽናትን ያጎናጽፉታል። እንደ ሀገር ሉዓላዊነትና ነጻነትን፤ እንደ ሕዝብም ክብርና አይበገሬነትን፤ በጥቅሉ ከፍ ያለውን የሀገርም የዜግነትም ልዕልና ለመጎናጸፍ አቅም ይሰጣሉ።

በመሆኑም፣ ዛሬ ላይ አሮጌ ያልነውን 2016 ዓ.ም ሸኝተን፣ አዲስ ያልነውን 2017 ዓ.ም ስንቀበልና አዲሱን ዓመት አንድ ብለን ስንጀምር፤ ከእንኳን አደረሳችሁ የምስጋና መግለጫ በኋላ፣ የመልካም ምኞት መግለጫዎቻችንን የምናስከትለው። ይሄ መልካም እሴት፣ መልካም መተሳሰብ ነው። ዋናው ጉዳይ ግን፤ ይሄ የምስጋና እና የመልካም ምኞት ቃላችን፤ ከቃል ያለፈ ሆኖ እንዲገለጥ በማድረግ ውስጥ የእኔ ድርሻ ምንድን ነው፣ በምን መልኩስ ልወጣ ይገባኛል፣ የሚለውን በልኩ ተገንዝቦ በመሥራት መግለጥ መቻሉ ነው።

ምክንያቱም፣ ብዙዎች የሚናገሩትን አይኖሩም፤ የሚመኙትን ለማግኘት አይተጉም፤ የሚራመዱበትን መንገድ እንኳን በቅጡ ሳይገነዘቡ ከፍጻሜ የማይደርሱበት አካሄድ ይስተዋላል። ይሄን መሰሉ አካሄድ ደግሞ እንደ ሀገርም ሆነ ሕዝብ በአዲሱ ዓመት ልንሆን ከምናቅደውም፣ ልንደርስበት ከምንጓዘውም አኳያ ጎታች ሆኖ የሚገለጥ ነው። በመሆኑም አዲሱን ዓመት በምስጋና ስንጀምር፤ ዓመቱንም በመልካም ምኞት ስንዋጅ፣ በተናገርነው ልክ ሆኖ መገኘትን ታሳቢ ማድረግ አለብን።

ለምሳሌ፣ ዓመቱ የሰላም እንዲሆን ስንመኝ፣ ለሰላም የድርሻችንን በመወጣት ሊሆን ይገባል። የመተሳሰብና የመደጋገፍ እንዲሆን ስንመኝም፣ ሠብዓዊነትን በመግለጥ ሊሆን ይገባል። የፍቅርና የይቅርታ እንዲሆን ስንመኝም፤ ፍቅርን እና ይቅርታን በተግባር እየገለጥን ሊሆን ይገባል።

ዓመቱ የብልጽግና እንዲሆን ስንመኝም፤ አንድ ሀገርና ሕዝብ ሁለንተናዊ ብልጽግናቸው እውን የሚሆንበትን መንገድ አቅዶ ለዛ እቅድ መሳካት የድርሻችንን በመወጣት ሊሆን ይገባል። በመሆኑም የአዲሱን ዓመት የእንኳን አደረሰን፣ አደረሳችሁ መልዕክት ስናስተላልፍ፤ የዓመቱንም ጉዞ የመልካም ነገር መከወኛ እንዲሆን ስንመኝ፤ ምስጋና እና ምኞታችን በተግባር የሚገለጥበት ሠብዓዊ እሴትን በመላበስ ሊሆን ይገባል!

አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You