ኢትዮጵያ የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ቻምፒዮናን ታስተናግዳለች

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ቻምፒዮናን እንደምታስተናግድ የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡ ከውድድሩ ቀደም ብሎ የውድድር አመራር ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን፤ የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ጠቅላላ ጉባኤም ይካሄዳል፡፡

የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ቻምፒዮና ከጥቅምት 2 እስከ 9/2017 ዓ.ም ሲካሄድ፣ ከሁሉም የአፍሪካ ዞኖች በማጣሪያ ውድድር አንደኛ የወጡ ሀገራት ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡ በ7 የውድድር ዓይነቶችና በሁለቱም ጾታዎች (በነጠላ፣ ቡድን፣ ድብልቅ እና በጥንድ) ከ100 በላይ ተጫዋቾች የሚወዳደሩም ይሆናል፡፡

በፉክክሩ አሸናፊ የሚሆኑ ተጫዋቾችም አፍሪካን በመወከል በዓለም የጠረጴዛ ቴኒስ ቻምፒዮና የሚወዳደሩ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን በኢትዮጵያ በሚካሄደው ቻምፒዮና አሸናፊ ለሚሆኑ ብድኖች የ25 ሺ ዶላር ሽልማት ያዘገጀ ሲሆን በነጠላ ውድድር 1ኛ ለሚወጡ 5 ሺ ዶላር፣ 2ኛ ደረጃን ለሚይዙ 2 ሺ 500 ዶላር እንዲሁም 3ኛ የሚሆኑ 1 ሺ 250 ዶላር ይበረከትላቸዋል፡፡

ከውድድሩ ቀደም ብሎ የውድድር አመራር ስልጠና እንዲሁም የአህጉሪቱ የጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ሲካሄድ፣ ሶስቱንም ሁነቶች በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድም ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራ እንደ ጀመረና ዝግጅቱም በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ ፌዴሬሽኑ የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማቋቋም መሰራት የሚገባቸውን ስራዎች እያከናወነ ሲሆን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር ለውድድሩ የሚመጡት ልዑካንን የ15 ከመቶ የጉዞ ቅናሽ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በውድድሩ ብቁ ሆኖ እንዲቀርብ ከዓለም አቀፉ የጠረጴዛ ቴኒስ ጋር በትብብር ከውጪ በመጣ አሰልጣኝ ስልጠና እየወሰደ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ዝግጅቱን ከጀመረ ከ15 ቀናት በላይ የሆነው ብሔራዊ ቡድኑ በቀን ሁለቴ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ጂምናዚየም እየሰራ ይገኛል፡፡ በተለያዩ ውድድሮች ያሸነፉ ተጫዋቾች፣ የውስጥ ውድድር በማድረግ ለብሔራዊ ቡድን የተመረጡ ሲሆን 8 ወንድ እና 8 ሴት ተጫዋቾች በአጠቃላይ 16 ተጫዋቾች በሁለት አሰልጣኞች ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ኤደን ተስፋዬ፣ ቡድኑ ከውጪ በመጣው አሰልጣኝ በቀን ሁለት ጊዜ ጥሩ የሆነ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ተጫዋቾቹ ስልጠናው ላይ ያላቸው ተነሳሽነት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና አሰልጣኙም ተፎካከሪ ለመሆን የሚያስችል ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች አህጉር አቀፍ ውድድር ላይ ተሳትፎ ያደረጉና ልምድ ያላቸው እንደመሆኑ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ዝግጁ ናቸው። በቀሪው ጊዜም የቴክኒክና ታክቲክ ስልጠና በመስጠት ለውድድሩ ዝግጅት እንደሚደረግ ጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ብዛኔ፤ ቡድኑ ዝግጅት ከጀመረ እንደቆየና በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ቡድኑ በሚዘጋጅበት ጂምናዚየም ደረጃውን የጠበቀ መብራት እንደሚሰራ ከአካዳሚው ቃል ተገብቷል፤ በዓለም አቀፉ መመዘኛ የቴኒስ ኳስ ትንሽ በመሆኑ በቀላሉ መታየት ይገባዋል። የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ጂምናዚየም ካለበት የመብራት ችግር ውጪ ውድድሩን በተሟላ ሁኔታ ያስተናግዳል፡፡ ለውድድሩ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች በቅርቡ ከዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን በአውሮፕላን ተጓጉዘው እንደሚገቡም ተጠቅሷል፡፡ ከዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን ለውድድሩ ከሚደረጉ ድጋፎች መካከል ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ያልገባና በዓለም አቀፍ የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር ላይ አገልግሎት የሚሰጥ 1 ሺ ካሬ ሜትር ምንጣፍ፣ የመጫወቻ ጠረጴዛ፣ መከለያ፣ ኳስ እና ራኬት ይገኝበታል።

ኢትዮጵያውያን ሲሚንቶ ላይ ተጫውተው ወደ ውጪ ሄደው ምንጣፍ ላይ ሲጫውቱ ውጤታማነቱ ላይ የራሱ ተጽዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ የሚደረገው ድጋፍ ለውድድሩ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም ጥሩ ጠቀሜታ እንዳለው ተመላክቷል፡፡ ከዝግጅት ጋር በተያያዘ የመጀመርያው ዙር ሪፖርት ታይቶ ለሁለተኛ ዙርም ከውጭ አሰልጣኝ በማስመጣት ስልጠና የሚሰጥበት እድልም ይኖራል፡፡ ኢትዮጵያ ውድድሩን በማስተናገዷ በአፍሪካ ጠንካራ የቴኒስ ተጫዋቾች የሚመጡ በመሆኑ ለስፖርቱ መነቃቃት እንዲኖርና ልምድ ለመውሰድ ይረዳል፡፡

ውድድሩ አህጉር አቀፍ በመሆኑ ለኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የበጀት ድጋፍ እንዲያደርግ ጥያቄ ቀርቦ እየተጠበቀ ሲሆን በሚለቀቀው በጀት ልክ ጥሩ ውድድር ለማዘጋጀት ይሰራል፡፡ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንዲሁም አጋር አካላት የተሳካ ውድድር ለማዘጋጀት የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ፕሬዚዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You