“የምናጋራው ማዕድ ብቻ ሳይሆን ለወገኖቻችን ያለንን ፍቅርና አክብሮት ጭምር ነው” – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፦ የምናጋራው ማዕድ ብቻ ሳይሆን ለወገኖቻችን ያለንን ፍቅርና አክብሮት ጭምር ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትናንት ከ500 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የመዲናዋ ነዋሪዎች ማዕድ አጋርቷል።

በእለቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት፤ ማዕድ የምናጋራው አቅመ ደካሞች እና የሀገር ባለውለታዎች እንዲሁም አነስተኛ ገቢ ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞች አዲሱን ዓመት በደስታ እንዲቀበሉ ለማድረግ ነው። በዚህም የምናጋራው ማዕድ ብቻ ሳይሆን ለወገኖቻችን ያለንን ፍቅርና አክብሮት ጭምር ነው ብለዋል።

ማዕድ የማጋራቱ ተግባር በሁሉም ክፍለ ከተማዎች እንደሚከናወን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፤ ከከተማችን ልማት ሁሉም ተቋዳሽ እንዲሆን ለማድረግ እየጣርን ነው ብለዋል፡፡ ለመዲናዋ ነዋሪዎች ያለንን ክብር ለመግለጽ እና ለማሳየት ሁል ጊዜ ታትረው እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

አዲሱ ዓመት የሀገር ባለውለታ መሆናችሁን ታሳቢ አድርገን እንደምናገለግላችሁ የምናሳይበት ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ በኅብር ሆነን በርካታ ፈተናዎችን ተሻግረን ድል አስመዝግበናል። ከዚህ ውስጥ ጠያቂና ደጋፊ የሌላቸውን ወገኖች ዝቅ ብለን በማገልገል የማዕድ ማጋራት፣ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት እና በኑሮ ውድነት የተፈጠሩ ጫናዎችን የማቃለል ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በበጎ ፈቃድ ሥራዎቻችን የነዋሪውን እርስ በእርስ የመደጋገፍ እና የመረዳዳት ባህል እንዲጎለብት እያደረግን ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ በዚህም የበለጠ ሀገራችሁን እየባረካችሁ መጪው ትውልድ የበለፀገች ሀገር መረከብ እንዲችል እንዲሁም ፈጣሪ እንዲረዳን የእናንተ ደስታ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በዓሉ የሰላም፣ የፍቅርና የበረከት ይሁንልን በማለት ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የመንግሥትን የሰው ተኮር ፖሊሲ፣ አቅጣጫ እና ጥሪ በመቀበል ሠርተው ካገኙት ለወገኖቻቸው ማካፈልን ባሕል ላደረጉ የከተማችን ልበ ቀና ባለሀብቶች እና በጎ ፈቃደኞች እንደሁልጊዜው ሁሉ መስጠት አያጎድልምና ለወገኖቻችሁ ለምታደርጉት በጎነት ሁሉ በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም አመሰግናለሁ ብለዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You