የየትኛውም ሀገር እጣ ፈንታ የሚወሰነው በዜጎች ማህበረሰባዊ ማንነት ነው። ይህ ማንነት ዜጎች በዘመናት ካካበቷቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እሴቶች የሚገነባ ፤ በየዘመኑ በሚፈጠሩ የለውጥ እሳቤዎች እየታደሰ እና እያደገ ዘመኑን በሚሸከም ሁለንተናዊ አቅም እየጎለበተ የሚሄድ ነው።
ይህ ማህበረሰባዊ ማንነታቸው አሁን ላሉበት እድገትም ሆነ ውድቀት፤ በታሪክ ሂደት ውስጥ ለነበራቸው የትርክት ከፍታም ሆነ ዝቅታ፤ ከዛም ባለፈ ነገዎቻችው ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ ተናጋሪ ልሳን ነው። በብዙ መልኩ እንደ ሀገር ሊኖራቸው የሚችለውን መልክ በትክክል ማሳየት የሚችል መስታወትም ነው።
ዘመኑን በሚዋጅ የአስተሳሰብ መሠረት ላይ የተገነባ ማህበረሰብ ዛሬን ጨምሮ ነገዎቹ ብሩህ ስለመሆናቸው፤ የተገነባበት የአስተሳሰብ መሠረት በራሱ ማስተማመኛ ነው። በተቃራኒው በትናንት አስተሳሰብ ዛሬ ላይ ቆሞ ነገን የሚጠብቅ ማህበረሰብ ዛሬን ጨምሮ ነገዎቹ በትናንት ጥላ ውስጥ ማደራቸው የማይቀር ነው።
በትናንት ጥላ ውስጥ መገኘት ፍጥረታዊ ከሆነው የለውጥ /የመለወጥ/ ሂደት ውጪ የሚያደርግ፤ ትናንቶችን ደጋግሞ ወደመኖር የሚያመጣ ፤ ከሠብዓዊ መሻት ጋር በተቃርኖ መቆምን የሚያስከትል ነው። ይህ ደግሞ ከዘመን ጋር አብሮ ካለመጓዝ ጋር በተያያዘ ሊፈጠር ለሚችል ማህበራዊ ቀውስ የሚዳርግ ነው።
በትናንት ጥላ ውስጥ የመኖር ችግር የድህነት እና የኋላቀርነት ዋነኛ ምክንያት ከመሆን ባለፈ፤ ትናንቶች ከሚፈጥሩት መለመድ ጋር በተያያዘ ፤ማህበረሰባዊ ድንዛዜን ያመጣል፤ነገን በተሻለ ተስፋ አስቦ መንቀሳቀስ የሚያስችል ማህበረሰባዊ መነቃቃትን ያሳጣል። ድህነትን እና ኋላቀርነት እጣ ፈንታ አድርጎ በመቀበል የጠባቂነት መንፈስን ያበረታታል።
እኛ ኢትዮጵያውያን ከትናንቶች ጋር በነበረን ጠንካራ ቁርኝት በብዙ መንገድ ዛሬዎቻቸውን ካጡ፤ ነገዎቻቸው ካባከኑ ሕዝቦች ጎራ የምንሰለፍ ነን። ከትናንት መማር ባለመቻላችን በተመሳሳይ ትናንቶች ውስጥ ብዙ ዋጋ እየከፈልን ኖረናል። በዚህም ድህነት እና ኋላቀርነት እጣ ፈንታችን ሆነው ዘመናት አልፈዋል።
በአንድ የታሪክ ምእራፍ ዓለምን ያስደመመ፤ ከታላላቆቹ ጎራ ያሰለፈ፤ ከዘመኑ በቀደመ አስተሳስብ የተገራ ማህበረሰብ እንዳልነበርን፤ የተቃርኖ አስተሳሰቦችን አቻችሎ መሄድ የሚያስችል ማህበራዊ ስክነት አጥተን፤ የተሻሉ ትናንቶቻችንን አጥፍተን፤ ነገዎቻችንን ባጠቆሩ ዛሬዎች ውስጥ ለመኖር ተገደናል።
ለየዘመኑ አስተሳሰቦች ባይተዋር ሆነን፤ በብዙ ማህበረሰባዊ ድባቴ ውስጥ በብዙ ቁዘማ አልፈናል። መሆን በምንፈልገው እና እየሆንን ባለው እውነታ መካከል የተፈጠሩ ልዩነቶችን ማስታረቅ የሚያስችል ማህበረሰባዊ የእውቀት መነቃቃት /ተሃድሶ/ አጥተን በድንግዝግዝ ዛሬን ብቻ አሸንፎ በመውጣት የሕይወት መርህ ዘመናትን አስቆጥረናል።
ዛሬ ግን ከዚህ ሁሉ የዘመናት የትናንቶች የጥላ ትርክት ወጥተን፤ ዛሬ ላይ ብሩህ የሆኑ ነገዎቻችንን አይተን፣ መሥራት በምንችልበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፡፡ የራሳችንን እጣ ፈንታ ብሩህ አድርጎ በሚያይ ማህበረሰባዊ የእውቀት መነቃቃት /ተሃድሶ ውስጥ ነን። ትናንቶችን ለትናንት ጥለን ዛሬዎችችንን ነገን ብሩህ በሚያደርጉና ዘመኑን በሚዋጁ የለውጥ እሳቤዎች እያነጽን ነው።
ከለውጥ ማግስት ጀምሮ በቁጭት ‹‹ድህነት እጣፈንታችን አይደለም፤ ትልቅ ነበርን ትልቅ እንሆናለን፣ ከትናንት እንማራለን እንጂ በትናንት አንኖርም፣ ድህነትን ታሪክ እናደርጋለን…›› እያልን ከፍ ባለ ድምጽ የምናሰማቸው ከለውጥ መንቃታችን የተወለዱ አሻጋሪ እሳቤዎቻችን የዚህ እውነት ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው።
በእነሱ ላይ ቆመን የጀመርነው አዲስ የታሪክ ምእራፍ ግንባታ ብዙ ዋጋ ቢያስከፍለንም፤ ከፍ ያለ ትጋት እና ቁርጠኝነት ቢጠይቀንም፤ የለውጥ መነቃቃቱና መነቃቃቱ የፈጠረው የአስተሳሰብ ተሀድሶ፤ ብዙ ትውልዶችን ታሳቢ የሚያደርግ፤ ለብሩህ ነገዎች መሠረት የሚጥል እና የሚያጸና ነው። ከዚያም በላይ አዲስ ተራማጅ ማህበረሰባዊ ማንነት መገንባት የሚያስችለን ነው።
አዲስ ተራማጅ ማህበረሰባዊ ማንነታችን ከትናንት አንገት አስደፊ ታሪኮቻችን የሚታደገን፤ ለቀደሙ ደማቅ ታሪኮቻችን ተጨማሪ ድምቀት የሚያላብስ፤ የከሰርንባቸውን ብዙ ዘመናት በይቻላል መንፈስ በብዙ መካስ የሚያስችል የፍጻሜ ጅማሬ ነው።
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም