ሶማሊያውያን የራሳቸው ያልሆነ ጦርነት ወደ ሀገራቸው ከመጋበዝ እንዲቆጠቡ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፡- ሶማሊያውያን የራሳቸው ያልሆነ ጦርነትን ወደ ሀገራቸው ከመጋበዝ እንዲቆጠቡ የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የሶማሊያ ክልል የሀገር ሽማግሌዎችና የህብረተሰብ ተወካዮች በአፍሪካ ቀንድ እየተስተዋሉ ባሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል፡፡

ውይይቱን የመሩት የሶማሌ የሀገር ሽማግሌና የጎሳ መሪው ገራድ ኩልሚዬ ገራድ መሀመድ እንደገለጹት፤ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ ነው፡፡ ጎረቤት ሶማሊያውያን የራሳቸው ያልሆነ ጦርነት ወደ ሀገራቸው በመጋበዝ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ወደ ቀውስ ማስገባት የለባቸውም፡፡

እንደ ገራድ ኩልሚዬ ገራድ መሀመድ ገለጻ፤ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ሁሉ የሶማሌ ክልል ሕዝብ ጉዳት ነው፡፡ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በመሆን የሀገርን ጥቅም ለማስከበር ይሠራል። ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት መብቷን ለማረጋገጥ የምትሠራቸውን ሥራዎች የሶማሌ ክልል ሕዝብ እንደሚደግፍም ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ ሃይሎች ወደ ሶማሊያ መጥተው የአፍሪካ ቀንድን ለማበጣበጥ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴም እንቃወማለን ያሉት ገራድ ኩልሚዬ፣ በሶማሊያ ያሉ የተለያዩ ሃይሎች ለሶማሊያ ሕዝብ ጥቅም ብለው ሳይሆን ጦርነት በመክፈት ችግር የመፍጠር ዓላማ ያላቸው መሆናቸውን በመገንዘብ ሕዝቡ ሊቃወማቸው እንደሚገባም ተናግረዋል።

የሶማሌ ክልል ሕዝብንና የሶማሊያ ሕዝብን ድንበር ቢለያቸውም ወንድማማቾች ናቸው ያሉት የጎሳ መሪው፤ የአብሮነት ታሪካቸውን ሊጠብቁት ይገባል ብለዋል።

የባህር በር ጥያቄው አብሮ ለማደግ የሚረዳ እንጂ የሚያራርቅ አጀንዳ አይደለም ያሉት የሀገር ሽማግሌዎቹ፤ የኢትዮጵያ ጠላቶች ላለፉት 40 ዓመታት የሶማሊያ ሕዝብ ሲቸገር አላስታወሱትም፣ ከሽብር ጥቃትም አላዳኑትም፡፡ ዛሬም ከአልሻባብ ጋር ለመዋጋት ፍላጎት የሌላቸው በመሆኑ የሶማሊያ ሕዝብ ሊቃወማቸው ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ለሶማሊያ ባለውለታ መሆኑን የጠቆሙት የሀገር ሽማግሌው፤ የሶማሊያ መንግሥትም ውሳኔውን እየተቃወሙ ያሉ ሕዝቦችን ሊያደምጥ ይገባዋል ብለዋል፡፡

የሀገር ሽማግሌው እንደገለጹት፤ በአሁኑ ጊዜ ከ500 ሺህ በላይ የሶማሊያ ስደተኞች በኢትዮጵያ ይኖራሉ፡፡ እንዲሁም ባለፉት 40 ዓመታትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች መጠለያቸውን ኢትዮጵያ አድርገው ሀብት አፍርተው እየኖሩ ነው፡፡ በአዲስ አበባና በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲዎች በርካታ ሶማሊያውያን በኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ እየተማሩ ነው፡፡

የሶማሊያ ሕዝብ ውለታ መላሽ ነው ያሉት ገራድ ኩልሚዬ ገራድ መሀመድ፤ ጥቂት ግለሰቦች ሥልጣንን ተገን በማድረግ ወንድማማች ሕዝቦችን ጠላት ለማስመሰል እየሞከሩ ነው፡፡ ይህ አይሳካላቸውም፤ ሕዝቡም እየተቃወማቸው ነው፡፡ ከሀገራቸው የኢትዮጵያን መውጣት አይፈልጉም፡፡ የኢትዮጵያና የሶማሊያ ሕዝብ ሽብርተኝነትን አብሮ ተዋግቷል፤ በሁለቱ ሰላም ወዳድ ሕዝቦች መካከል ችግር የሚፈጥር የውጭ ሃይልን መቃዎም ይገባል ብለዋል፡፡

ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ ኡጋዝ አሊ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ሶማሊያ ከሩቅ ሀገራት ይልቅ ከጎረቤቶቿ ጋር በመወያየት የሚፈጠሩ ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ አግባብ ልትፈታ ይገባል፡፡ ከውጭ የሚመጡ ኃይሎች የኢትዮጵያንና የሶማሊያን ጉርብትና ከማበላሸት ያለፈ ዓላማ አይኖራቸውም ያሉት ኡጋዝ አሊ፤ ሶማሊያውያን ችግር ሲገጥማት ቀድማ የምትደርሰው ኢትዮጵያ በመሆኗ በሀገራቸው የሚደረግ የጦርነት ቅስቀሳን መቃወም አለባቸው ብለዋል፡፡ የሶማሊያና ኢትዮጵያ ሕዝቦች የአፍሪካ ቀንድን በእጅ አዙር ችግር ውስጥ ለማስገባት የሚጥሩ ኃይሎች በመከላከል ረገድ አንድነታቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

ሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You