ዩክሬን ኢራን ለሩሲያ የባለስቲክ ሚሳይል አስታጥቃለች የሚለው ሪፖርት እንዳሳሰባት አሳወቀች

ዩክሬን ኢራን ለሩሲያ የባለስቲክ ሚሳይል አስታጥቃለች የሚለው ሪፖርት እረፍት ነስቶኛል አለች።

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢራን የባለስቲክ ሚሳይሎች ተላልፈው ወደ ሩሲያ እጅ ሊገቡ ነው የሚለው ሪፖርት እረፍት እንደነሳው ሰሞኑን አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ለጋዜጠኞች በላከው የኢሜል መልእክት በቴህራንና በሞስኮ መካከል ያለው ጥልቅ ግንኙነት ለዩክሬን፣ ለአውሮፓ እና ለመካከለኛው ምሥራቅ ስጋት መሆኑን ገልጾ፤ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ በኢራን እና በሞስኮ ላይ ጫና እንዲያሳድር ጥሪ አቅርቧል።

የአሜሪካው ሲኤንኤን ቴሌቪዥን እና ዎልስትሪት ጆርናል ኢራን የአጭር ርቀት ሚሳይል ለሩሲያ አስተላልፋ ሰጥታለች የሚል ሪፖርት ማውጣታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ሩሲያ ፋዝ-360 የተባለውን የኢራን የአጭር ርቀት ሚሳይል ለመቀበል እየጠበቀች መሆኑን እና ሩሲያም የሚሳይሉን አጠቃቀም እንዲያውቁ በደርዘን የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ለስልጠና ወደ ኢራን መላኳን ሮይተርስ ባለፈው ነሐሴ ወር ዘግቦ ነበር።

ባለፈው አርብ የዩክሬን ዋነኛ አጋር የሆነችው አሜሪካም ኢራን ሚሳይል ለሩሲያ አሳልፋ ልትሰጥ ትችላለች የሚል ስጋቷን ገልጻለች።

የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ሲአን ሴቭዋት ማንኛውንም የኢራንን ሚሳይል ለሩሲያ አስተላልፎ የመስጠት ሂደት ኢራን በዩክሬን ላይ ወረራ እያካሄደች ላለችው ሩሲያ የምትሰጠውን ድጋፍ ከፍ የሚያደርግ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You