ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ ደረጃ አንገታችንን አቅንተን እንድንሄድ ያደረጉ የብዙ አኩሪ ታሪኮች ባለቤቶች ብንሆንም፣ ከግጭት ጋር የተያያዘው ታሪካችን እንደ ሀገር ሕዝባችንን ብዙ ዋጋ ከማስከፈል ባለፈ ወደ ምንፈልገው ሀገራዊ ብልጽግና እንዳንሻገር ትልቁ ተግዳሮት ሆኖብን ዘመናት ተቆጥረዋል።
በአብዛኛው በውጪ ኃይሎች ፍላጎት ላይ የሚመሰረቱት እነዚህ ግጭቶች ፣ በየዘመኑ የነበረውን ትውልድ ዋጋ ከማስከፈል ባለፈ፣ በሀገሪቱ አጠቃላይ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ሕይወት ላይ አሉታዊ ተጽእኖዎችን በመፍጠር፣ ከግጭት አዙሪት ወጥተን በሙሉ ኃይላችን ወደልማት እንዳናተኩር አድርገውናል።
እንደ ሀገር ልዩነቶችን በውይይት፣ በንግግርና በሽምግልና የመፍታት ዘመናትን ያስቆጠሩ ብዙ ማህበረሰባዊ እሴቶች እያሉን፤ እነዚህን እሴቶች የሀገራዊ ፖለቲካ እሳቤያችን አካል ማድረግ አቅቶን ‹‹ሸክላ ሰሪ በገል ይበላል›› እንደሚባለው ከግጭት መውጣት ሳንችል ብዙ ያልተገቡ ዋጋዎችን እየከፈልን ነው።
በኃይል ላይ የተመሰረተው የፖለቲካ ባህላችን እንዲሁም በተዛባ ፣ ዘመኑን በማይመጥን ‹‹የአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት›› የተገዛው መሠረታዊ የፖለቲካ አሳቤያችን ፤ በውስጥ ጉዳያችን የውጪ ኃይሎች ጣልቃ በመግባት የራሳቸውን ፍላጎት እንዲያስፈጽሙ መልካም የሚባሉ አጋጣሚዎችን ፈጥሮላቸዋል፤ በእድሎቹም ተጠቅመውባቸው ሀገራችንን በብዙ ተጎጂ አድርገዋታል።
ሰላም ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ መተኪያ የለውም፤በተለይም እንደኛ ላለ በግጭት አዙሪት ውስጥ ዘመናትን ለማሳለፍ ለተገደደ ሕዝብ እውነታው ብዙ አስረጂ የሚፈልግ አይደለም። ላሳለፍናቸው አስቸጋሪ ትናንቶችም ሆነ ዛሬ ላይ ፈተና ለሆኑብን ችግሮቻችን ዋንኛ ምክንያት ነው።
እንደሀገር ሕዝባችን ሰላም ወዳድ ሕዝብ ነው፤ ስለሰላም ጠንካራ አቋም ያለው፤ ስለ ሰላም ዋጋ እንዲከፍል ሁሌም ዝግጁ የሚያደርጉ ሰፊ ማህበራዊ እሴቶች ባለቤት ነው። ባህላዊ፣ መንፈሳዊ እና ማህበረሰባዊ አስተምሮዎቹም ስለሰላም አብዝተው የሚናገሩ፣ስለሰላም አብዝተው የሚያዜሙ፣ ሰላም ከግለሰብ ህይወት ጀምሮ እስከሀገር የሚኖረውን ጠቀሜታ የሚዘክሩ ናቸው።
ይህ በሆነበት ተጨባጭ ሀገራዊ እውነታ ውስጥ በግጭት አዙሪት ውስጥ መኖራችን፤ከግጭት ጋር ተያይዞ የምንከፍለው ያልተገባ ዋጋም ሆነ ስለሰላም ባለን ሰፊ አስተምሮ ያልተቃኘው የፖለቲከኞቻችን የፖለቲካ እሳቤ ለብዙዎች በቀላሉ ሊመለስ ያልቻለ ግራ አጋቢ የዘመናት እንቆቅልሽ ነው።
በርግጥ ከእያንዳንዱ የግጭት ትርክት በስተጀርባ የውጪ ኃይሎች ፍላጎት ጎልቶ የመታየቱ እውነታ፣ ችግሩ ማህበረሰባዊ ከመሆን ይልቅ ግለሰባዊ እና ቡድናዊ ስለመሆኑ አመላካች ሊሆን ይችላል። ይህም ቢሆን፣ ማህበረሰቡ ይህንን የውጪ ኃይሎች ፍላጎት በሚገባ አለመገንዘቡ በራሱ የችግሩ አካል የሚያደርገው ነው።
በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የሕዝብ ውክልና አለን የሚሉ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ከሁሉም በላይ እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝብ ማህበረሰባዊ እሴቶች መገዛት ይጠበቅባቸዋል። የውክልናቸው ትክክለኛነት አንዱ ማረጋገጫ ይኸው ነው። ከዚህ እውነት በተቃርኖ ሲጓዙ ‹‹ተሳስታችኋል፤ ተመለሱ›› ማለት የሕዝቡ ኃላፊነት ነው።
በዚህ መልኩ ማህበረሰባዊ ሰላሙን ማስከበር ካልቻለ መቼም ቢሆን ከግጭት አዙሪት ሊወጣ አይችልም። ከግጭት አዙሪት መውጣት ካልቻለ ፤ እንደ አንድ ስልጡን ማህበረሰብ ከድህነትና ኋላቀርነት ወጥቶ ዘመኑን በሚመጥን የአኗኗር ሥርዓት ውስጥ ሊገኝ አይችልም።
የእኛም የወደፊት እጣ ፈንታ ከዚሁ እውነት ጋር የተሳሰረ ነው። ሕዝባችን ስለሰላም ከማዜም ወጥቶ፤ ሰላሙን ወደማስከበርና ወደመጠበቅ ታሪካዊ ምእራፍ መሸጋገር አለበት። ያልተጠበቀ ሰላም የቱን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍለው የገዛ ልጆቹ በየዘመኑ በሚፈጥሩት የሰላም እጦቶች በተጨባጭ መመልከት ችሏል።
ለሰላሙ ጠንቅ የሆኑ፣ የሰላም መሻቱን፣ ስለ ሰላም ያሉትን ከፍ ያሉ ማህበረሰባዊ እሴቶች የማያከብሩ፣ ከሰላም ወዳድነቱ ጋር የተሳሰረ ማህበረሰባዊ ማንነቱን የሚያደበዝዙ የትኛውንም አይነት እሳቤዎች ማውገዝ እና ተጨባጭ የጥፋት ምንጭ እንዳይሆን ፈጥኖ መንቀሳቀስ ይኖርበታል።
የውጪ ጠላት ሲመጣ ሁሉን ትቶ በአንድነት ሆ ብሎ እንደሚነሳ፤ በከፍተኛ የተጋድሎ ትርክት በጠላቶቹ ላይ ድል እንደሚቀዳጅ፤ ይህንንም ለትውልድ እንደሚያወርስ ሁሉ፤ ከግጭቶች በስተጀርባ ያሉት እነዚያው በጦር ግንባር የተፋለምናቸው እና ድል የነሳናቸው ጠላቶቻችን መሆናቸውን በመገንዘብ፤ ለውስጣዊ ሰላሙም በተመሳሳይ መልኩ መነሳሳትና መንቀሳቀስ አለበት።
እንደ አንድ በትናንት ቁጭት ውስጥ እንዳለ ትልቅ ማህበረሰብ፤ የበረታ የአንድነት ክንድ የሚፈልገውን ሀገራዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ ለሰላሙ በሁለንተናዊ መልኩ ዘብ መቆም ይጠበቅበታል። ለሰላም ማጣቱ ምክንያት የሆኑትን ‹‹በቃችሁ›› ሊላቸው እና በሚገባቸውና በተገቢው ቋንቋ ሊያወግዛቸው ይገባል።
አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም