አዲስ አበባ፦ ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ እንድትቀጥል ሕይወታቸውን ለገበሩ ጀግኖች ከፍ ያለ ክብር መስጠት ይገባል ሲሉ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።
የሉዓላዊነት ቀን በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም ትናንት ሲከበር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንደገለጹት፤ ለነፃነታችን ለማንደራደር ለእኛ ኢትዮጵያውያን የሉዓላዊነት ቀን ልዩ ስሜት አለው።
የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት ለመጠበቅ በደምም በላብም የሚጸና ሉዓላዊነት ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዚህ ትውልድ አባል የሆን ዜጎች ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ሲሉ ውድ ዋጋ የከፈሉ ኢትዮጵያውያን ዕዳ አለብን ብለዋል።
አቶ ተመስገን እንዳመለከቱት፤ ዕዳውን ዘመኑ በሚጠይቀው ልክ ለመክፈልና የተረከብነውን አደራ ለመወጣት ቁርጠኝነታችንን በተግባር ማሳየት ይገባል።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በደም ማጽናት የተቻለውን ያክል በኢኮኖሚው መስክ የተሟላ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ አርበኝነትን ተላብሶ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሀገር ነፃነት፣ ዳር ድንበርና ወገንን መጠበቅ የሚቻለው በመስዋእትነት ነው ያሉት አቶ ተመስገን፤ የፖሊሲ፣ የኢኮኖሚ፣ የእውቀት፣ የቴክኖሎጂና የበጀት ሉዓላዊነት ማስከበር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
የደም መስዋዕትነት ከፍለን ያስገኘነውን የግዛት ሉዓላዊነት ደካማ ያደረገብን ላባችንን አፍስሰን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነታችንን ማስከበር ስላልቻልን ብቻ ነው ብለዋል። ነፃነት ከልመና ጋር፣ ጥንታዊነት ከኋላቀርነት ጋር፣ ክብር ከተረጂነት ጋር አብረው የሚሄዱ ጉዳዮች አለመሆናቸውን ጠቁመዋል።
በፓናል ውይይቱ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ረዥም የሀገረ መንግሥት ታሪክ ዋናው መሠረታዊ መገለጫ ለዘመናት የቆየ ነፃነትና የማይደፈር ሀገራዊ ሉዓላዊነት ባለቤት መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ታሪካዊ ፀጋ ከራሳችን አልፎ ለሌሎች የአፍሪካና የጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት የሆነ የኩራት ምንጭ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ታዬ፤ የሉዓላዊነት ታሪካችን መሠረት ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ያስመዘገቡት ድል ነው። ይህንን ድልና መንፈስ በየተሰማራንበት ዘርፍ ሁሉ በመድገም ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ የአሁኑና የመጪው ትውልድ ተልዕኮ መሆን አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
አምባሳደር ታዬ እንዳስታወቁት፤ ሉዓላዊነት ራስን በራስ የማስተዳደር ፍፁማዊ የሥልጣን መገለጫ ነው። የሉዓላዊነት ባለቤት ሕዝብ ነው። ሕዝብ ደግሞ በፍላጎቱ የሚያቋቁመው መንግሥት በሀገር ውስጥና በውጭ ጉዳዮች ያለአንዳች ተፅዕኖ መወሰንና መበየን ይኖርበታል።
በሀገር ሉዓላዊነት የሚያምንና የበረታ ሕዝብ ለእድገት ያለውን ራዕይና ትልም ያሳካል ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ የሀገር ውስጥ ሰላምና ደህንነትን እንዲሁም በዓለም አቀፍ መድረኮች ሁሉ እውቅና አግኝቶ ብሔራዊ ጥቅሙን ያስከብራል ብለዋል። ተለዋዋጭ በሆነ ዓለም ውስጥ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሉዓላዊነትን ማስከበር እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር)፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ፣ የተለያዩ ሚኒስትሮች፣ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም