ፈተናዎቻችን ትውልዱ ከአባቶቹ ከወረሰው ጀግንነት እና ለሀገር ክብር ካለው ቀናኢነት አይበልጡም!

ሉዓላዊነታቸውን በከፍተኛ ተጋድሎ ለዘመናት አስጠብቀው ከቆዩ ጥቂት የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ ሀገራችን ኢትዮጵያ ነች። በየዘመኑ ሉዓላዊነቷን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች ቢያጋጥሟትም፣ ሕዝቦቿ ለነጻነታቸው እና ለብሄራዊ ክብራቸው ከነበራቸውና ካላቸው ቀናኢነት አኳያ ሉዓላዊነታቸውን አስጠብቀው መቆየት ችለዋል።

የሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ በኢትዮጵያ ረጅም ዘመናትን ማስቆጠሩ ፣ ሀገሪቱ በነዚህ ሁሉ ዘመናት ሉዓላዊነቷን አስከብራ መኖሯ፤ ለአንዳንዶች የመገረም እና የመደነቅ ፤ ለሌሎች ደግሞ የነጻነት ፤ የአልገዛም ባይነት እና የይቻላል መንፈስ መነቃቃት ምንጭ ሆኗል።

ይህ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣ ሉዓላዊነትን አስጠብቆ የመሄድ ማህበረሰባዊ እሴት በየዘመኑ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለመገዳደር የተነሱ ሃይሎች ከፍ ባለ ውርደት አንገታቸውን ደፍተው እንዲመለሱ፤ ከዚህ ባለፈ በዓለም የሃይል አሰላለፍ ላይ የነበረውን የተዛባ አመለካከት መግራት አስችሏል።

ሀገራችን ካለችበት ቀጣና ስትራቴጂክ ጠቀሜታ አኳያ በየዘመኑ የተነሱ ሃያላን መንግሥታት የትኩረት ማእከል ሆና ቆይታለች፤ በዚህም ሀገሪቱን በሃይል በማንበርከክ ለዓላማቸው ተገዥ ለማድረግ ረጅም ርቀቶችን ሄደዋል። በብዙ ዝግጅት የጦርነት ነጋሪት አስጎስመው ባህር ተሻግረው መጥተዋል።

በተሳሳተ ስሌት በተለያዩ የጦር ግንባሮች የሀገሪቱን ሕዝቦች ገጥመው፤ የሕዝቡን የነጻነት እና የአልገዛም ባይነት መንፈስ መቋቋም አቅቷቸው ፤ በመጡበት መንገድ በተሰበረ ልብ፣ በሽንፈት አንገታቸውን ደፍተው ለመመለስ ተገድደዋል። ይህም በብዙ የአሸናፊነት ገድል ለደመቀ የቀደመ ታሪካቸው ስብራት ሆኗል።

የቀደሙት አባቶቻችን ለሀገር ሉዓላዊነት የከፈሉት ውድ ዋጋ ከነሱ አልፎ፣ ዘመን ተሻግሮ የዚህ ትውልድ የብሄራዊ ክብር እና የማንነት ምንጭ ሆኗል። እንደ ሀገር በዓለም አቀፍ ደረጃ አንገታችንን ቀና አድርገን የምንሄድበትን የአኩሪ ታሪክ እና የከበረ የማህበረሰባዊ ማንነት ትርክት ባለቤት አድርጎናል።

የቅርቦቹ ትውልዶችም የቀደሙ አባቶችን የተጋድሎ ታሪክ ከመተረክ እና ትርክቱ በሚፈጥረው የማንነት ከፍታ ውስጥ ከመኖር ባለፈ፣ ሀገሪቱ የህልውና አደጋ ውስጥ በገባችባቸው ወቅቶች ሁሉ እንደ አባቶቻቸው በሀገር ህልውና እና ሉዓላዊነት ጉዳይ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ከፍ ባለ የሀገር ፍቅር እና የተጋድሎ ትርክት የራሳቸውን ታሪክ መሥራት ችለዋል።

ለዚህም ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት እንደሀገር በሉዓላዊነታችን እና በህልውናችን ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን በብዙ መስዋእትነት እና ከፍ ባለ ጀግንነት በአሸናፊነት መወጣት ችለዋል። በዚህም የአባቶቻቸው ልጆች መሆናቸውን፤ የሀገሪቱ ማሕጸን ጀግኖች ማፍራቱን እንዳላቆመ ለጠላትም ለወዳጅም በተጨባጭ አስመስክረዋል።

የዛሬውም ትውልድም ቢሆን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆኖ፤ የትኛውም ፈተና ከሀገሩ ሉዓላዊነት በልጦ ሊፈትነው እንደማይችል ባለፉት ሶስት ዓመታት በተጨባጭ አሳይቷል። ስለ ሀገሩ ሆ ብሎ በአንድነት በመነሳት፤ ከፍ ባለ መስዋእትነት የሀገርን ህልውና ከስጋት መታደግ ችሏል።

የሀገሪቱን ሉዓላዊ ክብር ሙሉ ለማድረግ በሀገራዊ ትርክታችን ላይ መጥፎ ጥላ ያጠላውን ድህነት እና ኋላቀርነትን ታሪክ ማድረግ በሚያስችል አዲስ የታሪክ ምእራፍ ውስጥ ይገኛል። አዲሱ የታሪክ ምእራፍ በብዙ ፈተናዎች የሚናጥ ቢሆንም ትውልዱ ለብሄራዊ ክብሩ ካለው ቀናኢነት፤ ተግዳሮቶችን ተሻግሮ ሀገርን የተሟላ ክብር ባለቤት እንደሚያደርግ ይታመናል።

ትውልዱ የሀገርን ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን መወጣት ብቻ ሳይሆን፤ የሀገርን ክብር ሙሉ ለማድረግ በጀመርነው ሀገራዊ ንቅናቄ ላይ በውስጥም በውጪም እያጋጠሙን ያሉ ፈተናዎች የሚጠበቁ፤ በዘመናት እንደ ጥላ ሲከተሉን የኖሩ፤ ዛሬ ላይ ላለንበት ድህነት እና ኋላቀርነት በአንድም በሌላም ተጠቃሽ የሆኑ ምክንያቶች መሆናቸውን ይገነዘባል።

እነዚህ ፈተናዎች ትናንት ግልጽ በሆኑ የተለያዩ የጦርነት ግንባሮች ገጥመን በሽንፈት የመለስናቸው ጠላቶቻችን ሴራ አካል ናቸው። ፈተናዎቹ አሁን ያለው ትውልድ ከአባቶቹ ከወረሰው ጀግንነት እና ለሀገሩ ክብር ካለው ቀናኢነት፤ ከዛም ባለፈ ከድህነት ጋር አብሮ ላለመኖር ከፈጠረው ቁርጠኝነት አንጻር በየትኛውም መመዘኛ ከአቅሙ በላይ ሊሆኑ የሚችሉ አይደሉም።

እነዚህ ፈተናዎች አሁን ላይ የገዘፈ አቅም ተላብሰው በትውልዱ ፊት ቢቆሙም፤ ትውልዱ ዘመኑን እና በዘመን ውስጥ የተገነባ አሁናዊ ማንነቱን የሚመጥን የራሱን ታሪክ ሰርቶ እንዲያልፍ በታሪክ ሄደት ውስጥ የተፈጠሩ ክስተቶች ተደርገው የሚወሰዱ፤ ሊሠራው ላለው ታሪክም ‹‹እንደ መልካም አጋጣሚ›› የሚታዩ ናቸው።

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You