አዲስ አበባ:- በፍርድ ቤቶችና ሌሎችም የፍትህ አካላት ሥራዎቻቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ በቃላት አተረጓጎም የሚያጋጥማቸውን ችግሮች ሊፈታ የሚችል የአማርኛ የሕግ መዝገበ ቃላት መዘጋጀቱን የፌዴራል ሕግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡ የኦሮሚኛ የሕግ መዝገበ ቃላት 25 በመቶ ተጠናቅቋል፡፡
የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ፤ በፍትህ ሂደት በቃላት አተረጓጎም ችግሮች እንደነበሩ እና የፍርድን ሂደት የሚያዛቡ አጋጣሚዎች መስተዋላቸውን ጠቁመዋል፡፡
ፍርድ ቤቶች፣ በሌሎች የፍትህ አካላት እና ክልሎችም ሕጉን መሰረት አድርገው በሚሰሩበት ሂደት በቃላት አተረጓጎም ችግሮች መኖራቸውን በተደረገው ግምገማ ግንዛቤ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡
ከሦስት ዓመታት በፊት ሥራው የተጀመረው የአማርኛው መዝገበ ቃላት ኢንስቲትዩቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከጄስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሽፕ ጋር በጋራ የተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ እንደሚመረቅም ተናግረዋል፡፡
አሁን የተዘጋጀው ‹‹ኢንሳይክሎፒዲክ ሎው›› ከብላክ ሎው፣ ከኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ጋር በተቻለ መጠን ተቀራራቢነት ያለው እና በአማርኛ፣ በኦሮሚኛና በሌሎቹም ቋንቋዎች እንዲዘጋጅ ከሦስት ዓመታት በፊት ሥራው የተጀመረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፍትህ አካላት ሥራዎቻቸውን በሚሰሩበት ጊዜ ለምሳሌ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ፣ የፍትሐ ብሔር ሕግ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም የሕግ ትምህርት ቤቶች ያጋጥማቸው የነበሩ የአተረጓጎም ችግሮችን የሚፈታ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
የሕግ መዝገበ ቃላቶች ተዘጋጅተው ሊሆን ይችላል ያሉት አምባሳደር ደግፌ፤ አሁን በተዘጋጀው ልክ በኢትዮጵያ የተዘጋጀ የሕግ መዝገበ ቃላት የለም፤ የመጀመሪያው ነው ማለት ይቻላል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቋንቋዎችና ባህል ጥናት ክፍል ለስራው ትኩረት በመስጠት በጋራ ስንሠራ ቆይተናል፣ ለዳኞች፣ ለዐቃቤ ሕጎች ፣ ለጠበቆች፣ ለሕግ ትምህርት ቤቶችና ለአጠቃላይ ለፍትህ ዘርፉ የሚጠቅም ነው ብለዋል፡፡
የኦሮሚኛ የሕግ መዝገበ ቃላት ዘግይቶ በመጀመሩ እስካሁን ባለው ሂደት ቃላት ተለይተው ትርጉም እየተሠራ ሲሆን፤ አፈጻጸሙም 25 በመቶ መድረሱን አመልክተው፤ በሁለት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡
ዳኞች፣ ዐቃቤ ሕጎችና ሌሎች የፍትህ አካላት ፍርድ የሚሰጡት የሚያሳልፉት በሰው ንብረት እና ሕይወት ላይ ነው፡፡ ነገር ግን በአንድ ቃል ልዩነት እና ግድፈት ምክንያት ያልሆነ ውሳኔ ወይንም ፍርድ ሊያስተላልፉ ይችላል፡፡
በመሆኑም በሁኔታው ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የሚሆን አንድ የሕግ መዝገበ ቃላት መዘጋጀት እንደሚገባው በመስማማት ወደ ሥራ መገባቱን አውስተዋል፡፡
በዝግጅቱ የሕግ ምሁራን፣ በቋንቋ (ሊንጉዊስቲክ) የተሻለ ብቃት እና ችሎታ ያላቸው ሰዎች እንዲሳተፉ መደረጉንም አመልክተዋል፡፡
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን እሁድ ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም